loret Tsegaye G
Opinion

የህወሀት የምርጫ ውሳኔ፣ የሀገ መንግስት ጥሰትና የፌደሬሽን ምክር ቤቱ ውሳኔ

በ ባቴሮ በለጠ

 

ጳጉሜ 2፣ 2012 (ሲፐተምበር 7,2020)

ህወሀት በክልል ፓርላማው ቀጥሎም በቱባ ባለስልጣኖቹ በኩል የኢትዮጰያ ምርጫ ቦርድ እንደተቋም የዘንድሮው ምርጫ በኮቪድ ውረርሽኝ ምክንያት እንዲተላለፍ ያቀረበውን ውሳኔ ቀጥሎም በሀገሪቱ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ስብሳቢ በመሩት ሂደት የተሰጠውን የህግ ትርጓሜ፣ ሁሉ በመጣስ ምርጫ እናካሂዳለን በማለት ሲናገር ቆይቷል። በመቀጠልም ፌደራል ፓርላማውና መንግስት የወስኑትን የምርጫ መራዘም፣ አልቀበልም ብሎ በግልጽ ካወጀ ሰንብቷል።

ይህ ብቻም አይደለም ህወሀቶች ከቃላት ተቃውሞና ዘለፋ አልፈው በይፋ የምርጫ ዝግጅት ሲያካሂዱ ከርመው የመራጮችን ምዝገባ ጨርስው ወደ ድምጽ መሰጠቱ ለመግባት ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርቷቸዋል። አሁን ደግሞ የውጭ ሙገሳንና እውቅናን ለማገኘት በሚመስል መልኩ የውጭ ጋዜጠኞችንና አንዳንድ አለም አቀፍ ተቋሞችንም እንደጋበዙ ተስምቷል።

ይህን በተመለከት መንግስት የተምታታ መልእክት በለሆሳስ ሲያስተላልፍ ቆይቶ ባለፈው ሳምንት ባለቀ ሰአት የፌደዴሽን ምክር ቤቱ የሀወሀት ውሳኔም ይሁን ተግባር ሀገምንግስቱን የጣስ ነው ካለ በኹላ ምርጫ ቢካሄድም፣ ውጤቱ ተቀባይነት እንደማያገኝ ይታወቅ የሚል ውሳኔ ወስኖ ተበትኗል።

ልብ በሉ ምርጫውን ማካሄድ ህገ መንግስቱን ይጻረራልና አታካሂዱም ሀገ መንግስቱን የሚጻረረ ተግባር ማካሂድ አይፈቀድም ስለዚህም የጀመራችሁትን አቁሙ አይደለም ያለው። ወይም ይህን የሀገመንግስት ጥስት በሚያቀናብሩና በሚመሩ ላይ ትልቅ የህግ ጥስት አካሂደዋልና ተገቢውን ሀጋዊ እርምጃ እንወስዳለን አይደለም የሚለው። ብቻ እንደ ተራ የፖለቲካ ውይይት ወጤቱን አንደማንቀበል ከወዲሁ እወቁት ነው።

ለ28 አመታት ያየነውና የምናውቀው ኢሀአዴግ የህገ መንግስቱን አንድ ጸጉር መንክት ትልቁ ሀጢያት ነው ሰለሆነም ከፍተኛ ቅጣት ያስከትላል፡ይህን ማድረግ ሀገርን ማፍረስ ያስከትላል ሲል የኖረው ኢሀአዴግና ወራሹም ብልጽግና፣ ታዲያ አሁን ለዚህ ክፍተኛ የሀገ መንግስት ጥሰት የሚሰጡት ምላሽ “ምርጫ ቢካሄድም፣ ውጤቱ ተቀባይነት እንደማያገኝ እውቁ” በሌላ እባባል ሀገ መንግስትቱን ብትጥሱም አኛ ደግሞ እንደ ቁም ነገር አንቆጥረውም የሚል መሆኑ ምን ማለት ነው? ለመሆኑ የህገ መንግስት ጥሰትን በተመለከት “ቀይ መስመሩ” የት ላይ ነው? መንግስት ህወሀትን ከተግባሩ እንዲቆጠብ የሚያስገድደው እርምጃ አለመውሰዱስ በዚች ቋፍ ላይ በምትገኝ ሀገር ውስጥ የሚያስተላልፈው መልእክት ምን ይሆናል? ዛሬ ከፌደራል መንግስቱና ህገመንግስቱ ውጭ ምርጫ እንደፈለጉ ማስኬድ ከተቻለ ነገና ከነገ ወዲያስ አንድ ክልል ከኢትዮጰያ ለመገነጠል በፈለገበት ጊዜና ሂደት (ዩኒላተራሊ) እርሱ እንደፈለገ የሚያደርግበት እውነታ በር ከፋች ሊሆን አይችልምን የሚሉትን ጥያቄዎች ማንሳትና መነጋገር አግባብ ያለው ጉዳይ ነው።

በኔ እይታ የህወሀትም ሆነ የመንግስት አካሂድ እጅግ ሰፊ አደጋን በሀገር ህልውና እና በህዝብ ደህነነት ላይ የሚያጠላ ነው።

ሀገ መንግስቱን ለመናድ ሞክረዋል፣ ሀገ መንግስቱን የሚጻርረ ተግባር ፈጽመዋል ወዘተ በሚል ስበብ ብልት በተኮላሽባት፣ ብዙዎች ለቶርቸር በተዳረጉባት ፣ ተሰደው ከሀገር እንዲጠፉ በተደረገበት ሀገር አሁን ሀገምንግስት ጣሹ ራሱ ሀወሀት ሲሆን “የፈለጋችሁት ብታደርጉም አኛ ደግሞ ወጤቱን አንቀበልም” የሚል አካሄድ በዚች ሀገር ውስጥ በሀገ አይን ሁሉም እኩል ናቸው የሚባለው ላይ አሁንም ትልቅ ጥያቄ ያስነሳል። ህግ የሚጸናባቸውና፣ ከህግ በላይ የሆኑ ዜጎች እሉ፣ በዚህች ሀገር ውስጥ አድልኦ ይካሄዳል የሚለውን ክስ ያጠናክራል።

በዶከተር አብይ የሚመራው መንግስት ላይ የሚሰነዘረው አንዱና ዋነኛው ቅሬታ ሀግ ማሰከበር አልቻሉም የሚል ነው።

ሰው ሲታረድ፣ ሀዝብ ሲፈናቀል፣ ንብረት ሲጋይ ወዘተ “ የወንጀል መከላከልና ማስከበር ሰራ ወንጀሉ ከመፈጸሙ በፊት፣ በተፈጸመበት ጊዜም ሆነ ከተፈጸመ በኹላ አልተካሂደም የሚል ነው። ለዚሀ ደግሞ እጅግ በዙ መረጃዎች ይቀርባሉ፡: ይህ ህወሀትን የተመለከት እጅግ አስተዛዛቢና ደካማ ወሳኔ በጠቅላይ ሚኒሰቴሩና በመንግስታቸው ላይ በተደጋጋሚ የሚነሳውን ይህንኑ የሀዝብ ቅሬታ አሁንም ይበልጥ ያጎላዋል።

ከአሁን በፌት በፌደራል መንግስቱ ወደ መቀሌ የተላኩ የጸጥታ ሀይሎች መቀሌ አይሮፐላን ማረፊያን ሳይሻገሩ በሀወሀት ፖሊስ ትጥቅ እንዲፈቱ ተደርገው ለአንድ ወር ያክል በቁም እስር ሲታገቱ መንግስት ፣ ይህን ሀገ ወጥ ተግባር ለማስቆምና ሀግን ለማስከበር ምንም ማድረግ አልቻለም፤ ነበር። ህዝብ ይህን ጉደ ምናልባት አዲሰ ሰልሆኑ ይሆናል በሚል አይቶ እንዳላየ አልፎት ነበር።

በፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ሀግ የገንዘብ ዝርፊያና የስብአዊ መብት ጥሰት የተከሰሱ ግለስቦች በሀወሀት ጉያ ውስጥ ተደብቀው እንዳሉ እየታወቀ በየፍርድ ቤቱ “አድራሻቸው ስላልታውቀ “ ወዘተ በሚል የልጅ አይነት ፌዝ “በዚሀ ቀን አዲሰ አባባ ድርስ ካልመጥችሁ ጉድ ይፈላል” የያሉ በጋዜጣ ማውጣትና ራሰን ማታለል ከተጀመረ ድፍን ሁለት አመት አለፈው። ህዝብ ይኽንንም ወይ ጉድ እያለ በትዝብት አልፎታል።

በተደጋጋሚ ሀወሀትና ምከር ቤቱ በይፋ ፌደራል መንግስቱን “አምባገነን ነው፣ ሀዝብ ሊነሳበትና ሊያስወግደውም ይገባል” እያለ በመግለጫና በቃለምልልስ መንግስትን ለመገልበጥ ሲንቀሰቅስ ሰራዊቱን መፈንቀለ መንግስት እንዲያካሂድ ሲያበረታታ በፌደራል መንግስቱ ባለስልጣናት በኩል አንድም እርምጃ አልተወስደም።እነ ለደቱ፣ አያሌው የታሰሩት ከመስከረም 30 በሗላ መንግስት የመግዛት መብት የለውም ብለው ሰለተናገሩ እንደሆነ የሚያውቀው ህዝብም “ አየ የኛ ነገር “ እያለ ማጉረምረሙን ቀጥሏል፡

አሁን በመጨረሻ ሕወሀት ምርጫውን ማካሄድ ብቻ ሳይሆን ፊደራል መንግስቱን ያስብነውን ምርጫ ልታደናቅፉ ብትሞክሩ ጦርነት አንዳወጃችሁ እንቆጥረዋለን ሰለዚሀም ጠቅላይ ሚኒሰቴር አብይን ራሳቸውን በግል በሀላፊነት እንጠይቃለን በማለት ማስፈራሪያቸውን በአዋጅ በነገሩን ማግስት ታዲያ ይህ የፌደረኤሽን ምክር ቤት ውሳኔ ከህግ ማስከበር አንጻር ምን ያሳያል?፡

በርግጥ ጠቅላዩም ሆኑ መንግስታቸው ህግ የማሰከበር ፍላጎትም ችሎታም አንዳላቸው ወይስ አሁንም በተለያየ ምክያት ህግን ማስከበር እንዳልቻሉ? የዚህስ እንደምታ ምን ይሆናል?

መንግስት በጉልበተኛና በሚያስፈራራ ቡድን ላይ ሁሉ ሀጋዊ እርምጃ መውስድ የማይቻል ከሆነ ህዝብስ በማንና በምን ላይ ተስፋውን ይጣል?

ጠቅላይ ሚኒሰቴር አብይ ሆይ ድፍረት አይሁንብኝ እና በድጋሜ ለማንሳት ህዝብ በርስዎና በበልጽግና ላይ የሚያነሳው አንዱና ትልቁ ቅሬታ ያለ አድልኦ ሀግን ማስከበር አልቻሉም የሚል ነው።

የፌደረሽኑ ምክር ቤቱ የሀወሀትን የምርጫ ውሳኔ በተመለክት ያሳለፈው “ ምርጫ ቢካሂድም ውሳኔው ተቀባይ አይሆንም “ የሚለው ቀልድ ከላይ የጠቀስኩትን ቅሬታ የሚያጠናክር ብቻ ሳይሆን ሀግ የማስከበር ሀላፊነትንም የዘነጋ ነው።

በዚሀ አኳያ ገዥው ፓርቲም ሆነ የፌደሬሽን ምክር ቤቱ በህወሀት የተፈጸመውን የህገምንግስት ጥስት ቆፍጠን ብሎ በጊዜ ሊያስቆም ባለመቻሉ ይህን ተግባር የሚያቀነባብሩትንም ተጠያቂ የሚያደርግ ምንም ነገር ባለመደረጉ በሀገርና በህዝብ ላይ ለሚያሰክትለው ቀጣይ አፍራሽ ተጸእኖ ከባድ ይሆናል ለዚህም ተጠያቂነት እንደሚኖር መገንዘብ ይገባል።

ዲፋክቶ ሀገር ከተመሰረተ በኹላ ሌላ ምስቀልቀል ውስጥ ከመገባት ሁኔታውን ቀድሞ ማምከን ሳይሻል አይቀርም። ጊዜው ከመሪዎች ቆፍጠን ፈጠን ማለትን ይጠይቃል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *