News

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ( አብን ) የጠራው ሰልፍ

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ( አብን ) የጠራው ሰልፍ በመንግስት መከልከሉ የብልፅግናን ከልክ ያለፈ አንምባገነናዊነት ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው ሲል የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ( መኢአድ ) ገለፀ።

አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ
ጥቅምት 17 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ ሸዋ

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ( መኢአድ ) ማንኛውም ዜጋ ሀሣቡን በነፃነት የመግለፅ እና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ሕገ መንግሥታዊ መብቱ ሊከበርለት ይገባል ብሎ ያምናል።
“ማንኛውም ሰው ያለ ማንም ጣልቃገብነት ሐሳቡን የመግለጽ ነፃነት አለው። ይህ ነፃነት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በሕትመት፣ በስነጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ፣ ማንኛውም ዓይነት መረጃ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጫ ነፃነቶችን ያካትታል።”

ሲል የኢፌዴሪ ሕገመንግሥት አንቀፅ 29 ንዑስ አንቀፅ 2ን ጠቅሷል።
መኢአድ በተጨማሪም አንቀፅ 30 ንዑስ አንቀፅ 1″ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሳሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው” የሚል ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ እንዳለም አመልክቷል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ በተለይም በኦሮሚያ ክልል ፣ በደቡብ ክልል እና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል እየተፈፀመ ያለውን ዘር የማጥፋት ተግባር የሚያወግዝ ሠልፍ በአማራ ክልል ከተሞች እና በአዲስ አበባ ከተማ ዜጎች ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ሰላማዊ ሰልፍ መጥራቱ ያወሳው መኢአድ አንምባገነኑ የብልፅግና መንግስት ይህን ሠልፍ እንዳይካሔድ ከልክሏል ነው ያለው።

በሕገ መንግሥቱ ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው ይህ መብት ፈቃጅና ከልካይ የሌለው መብት ሆኖ ሳለ መንግሥት እራሱን ፈቃጅ እና ከልካይ አድርጎ ይህን በሕገ መንግሥቱ የተደነገገ መብት መጣሱ አግባብ ካለመሆኑም በተጨማሪ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች በአማራው ላይ እየደረሰ ላለው ዘር የማጥፋት ተግባር ተባባሪ እንደሆነ ይቆጠራል ሲልም መኢአድ በመግለጫው አስታውቋል።
ሰሞኑን ገዢው ፓርቲን በመደገፍ በአዲስ አበባና በተለያዩ የክልል ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎች በተከታታይ እየተደረጉ ባሉበት ሁኔታ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ለሚመለከተው የመንግሥት አካል በግልፅ በደብዳቤ ያሳወቀውን ሰላማዊ ሰልፍ መንግሥት በሚዲያ ወጥቶ መከልከሉ ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው ብሏል።

Source: zehabesha.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *