መቀሌ የሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ ከትላንት ጀምሮ በከተማዋ የነበረው ሁኔታ እንዲህ ዘግቦታል። የሚከተሉትን ፎሮ ግራፎችም ልኮልናል።
ትላንት [ማክሰኞ] እኩለ ለሊት ገደማ መቀሌ ከተማ ተኩስ ይሰማ ነበር።
የከተማው ሰው እየሆነ ባለው ነገር ተደናግጦ ነበር። ይሄኔ ሁኔታውን ለማረጋገጥ ወደ ፀጥታ ኃይል ሰዎች ስደውል ‘አሁን ልናናግርህ አንችልም፤ ቢዚ ነን’ አሉኝ። ከደቂቃ በኋላ የስልክ መስመር ተቋረጠ። ስልኬ ‘ኖ ሰርቪስ’ የሚል ምልክት ያሳየኝ ጀመር።
በመቀጠል የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተቋረጠ። ጥዋት ስንነሳ ከተማዋ የኤሌክትሪክ አገልግሎቷ እንደተቋረጠ ተረዳሁ። መብራት የጠፋው መቀሌ ብቻ ሳይሆን ትግራይ ክልል ሙሉ እንደሆነ ማረጋገጥ ችያለሁ።
ወደ ከተማ ወጣ ስል የሰዎች ፊት ላይ ግራ መጋባት ተመለከትኩ። አብዛኛው ሰው በእግሩ ነበር ሲንቀሳቀስ የነበረው።
ከተማዋ ላይ ያሉ የባንክ ቅርንጫፎች ተዘግተው ነበር። ሁለት የባንክ አስተዳዳሪዎች እንደነገሩኝ አገልግሎት ያቋረጡ የበይነ መረብ [ኢንተርኔት] አገልግሎት ስለሌለ ነው።
ረፋድ ላይ የኢትዮቴሌኮም ሠራተኞች መስሪያ ቤታቸው ደጃፍ ላይ ሰብሰብ ብለው ቆመው ነበር።
ከረፋፈደ በኋላ ከፀጥታ ኃይል ሰዎች እንደተረዳሁት ተኩሱ የተሰማው የትግራይ ክልል ወታደሮች ከሰሜን ዕዝ ጋር በነበራቸው የተኩስ ልውውጥ መሆኑን ተረድቻለሁ።
ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ቢሮና ወደ ሌሎች የጉዞ ወኪሎች አምርቼ ለጊዜው በረራ ሙሉ በሙሉ መቋረጡን መረዳት ችያለሁ።
መቀሌ ከተማ ያሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ሆቴሎች አካባቢ ከበድ ያለ የፀጥታ ኃይል ይታያል።
የክልሉ መንግሥት ክልሉ ውስጥ ምንም ዓይነት ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዳይኖር አግዷል።
የትራንስፖርት አገልግሎትም ሙሉ በሙሉ ቆሟል። የክልሉ የአየር ክልልም ከበረራ ውጭ እንዲሆን ታዟል።
መቀሌ ከተማ አሁን ላይ ሰላማዊ ሁኔታ ላይ ትገኛለች።
Source: bbc amharic
ትግራይ: መከላከያ ሠራዊት በሕወሃት ላይ የኃይል እርምጃ እንዲወስድ መታዘዙ ተሰማ