2021 ed alfetir
News

ከሜክሲኮ እስከ ባንቢስ በተዘረጋው ጎዳና ላይ “የኢፍጣር ስነ-ስርዓት”

ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– 1442ኛ የረመዳን ጾምን አስመልክቶ በአዲስ አበባ ከተማ የጎዳና ላይ የኢፍጣር ስነ-ስርዓት እየተካሄደ ሲሆን፣ የኢፍጠር ፕሮግራሙ በሰላም እንዲከናወን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል፡፡

ከ10ሺህ በላይ ሰዎች ተሳታፊ የሚሆኑበት የኢፍጣር ፕሮግራም ከመከናወኑ አስቀድሞ ከተለያዩ ቤተእምነቶች የተውጣጡ የሀይማኖት አባቶችና ወጣቶች የጎዳና ላይ ኢፍጣር የሚካሄድበትን ቦታ አጽድተዋል።

https://youtu.be/4zwvJrarQD4?list=RDCMUCgkxWsjCpOKdZ-uewAedovg

በጽዳት ዘመቻው ላይ የሀይማኖት አባቶች ባስተላለፉት መልዕክት በዓላትን በጋራ የማሳለፍ ኢትዮጵያዊ መገለጫችንና አብሮነታችንን ከምናሳይበት እሴቶች አንዱ የሆነው ኢፍጣር ፕሮግራም መሆኑን በመግለጽ “አብሮነታችንንና ሰላማችንን ሊያደፈርሱ የሚፈልጉ ሀይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም” ሲሉ አሳስበዋል።

በአዲስ አበባ በተዘጋጀው ታላቅ የጎዳና ላይ ኢፍጣር መርሀ-ግብር ከሜክሲኮ እስከ ባንቢስ ድረስ በተዘረጋ ዝግጅት በሰላም እየተካሄደ ሲሆን፣ ስነስርአቱ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ከተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች የተውጣጡ ጾመኞችና እና ሌሎች እንግዶች መሳተፋቸውና ከጸጥታ አካላት ባለፈ የመዲናዋ ወጣቶች ታዳሚውን በማስተናበር ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።

የዛሬው የጎዳና ላይ ኢፍጠር ስነ ስርዓት፣ ባለፈው እሁድ ሊካሄድ የነበረ፣ በፀጥታ ሃይሎች የተከለከለና የአዲስ አበባ አስተዳደር ለተፈጠረው ችግር ህዝበ ሙስሊሙን በይፋ ይቅርታ ጠይቆ እንደገና ዛሬ እንዲከናወን የተፈቀደ መሆኑ ይታወቃል።

በተያያዘ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ኡመር እድሪስ፣ ለእስልምና እምነት ተከታዮች ለኢድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን፣

የዛሬውን የአዲስ አበባ የአደባባይ ፊጥራ በተመለከተ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር መመካከራቸውን ገልፀው፣ አብሮነትንና አንድነትን ለማሳደግ በሚደረገው በዚህ ትልቅ የአደባባይ ፊጥራ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም አስገንዝበዋል።

“ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ የተጠራው የጎዳና ላይ የኢፍጣር ፕሮግራም በኛ በኩል እውቅና አልነበረውም፤ የዛሬውን የጎዳና ላይ ኢፍጣር በተመለከተ ግን የተሳካ እንዲሆን ለማድረግ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ እየሠራን ነው” ያሉት ተቀዳሚ ሙፍቲ “እለቱም የኛ አብሮነት እና የወንድማማችነት ጎልቶ የሚታይበት እንዲሆን ሁሉም ለጋራ ስኬቱ በጋራ መቆም አለበት” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

በዓሉ ዛሬ ማታ ጨረቃ ከታየች በ29ኛው ቀን ነገ ረቡዕ እንደሚሆንና ዛሬ ማታ ካልታየች ግን ሐሙስ እንደሚሆንም ሐጅ ሙፍቲ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

አሁን በደረሰን መረጃ በዛሬው ዕለት አዲስ የሸዋል ጨረቃ ሊታይ ባለመቻሉ የዘንድሮው ዒድ አል – ፈጥር የሚውለው ከነገ በስቲያ ሐሙስ ግንቦት 5 ቀን 2013 መሆኑ መረጋገጡን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ማምሻውን አስታውቋል።

ምንጭ፤ https://ethiopianege.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *