ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን የተመለከቱ ጉዳዮችን በዘረዘረበት የጥናት ክፍል በመራጮች ምዝገባ ወቅት ስለተስተዋሉ ችግሮች፣ ስለ ምርጫ ጣቢያዎች ተደራሽነት፣ ስለ ምርጫ አስፈጻሚዎች አመላመል ሂደት እንዲሁም የመራጮች መዝገብን ለመመርመር ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ተመልክቷል። ፓርቲው እነዚህን ጉዳዮች የተመለከቱ መረጃዎች ያሰባሰበው “በድፍን አዲስ አበባ” ተዘዋውሮ መሆኑንም አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የምርጫ ካርድ ለማውጣት ችግሮች ገጥመዋቸው እንደነበር የሚጠቁመው የዳሰሳ ጥናቱ፤ በተለያዩ ምክንያቶች “ብዙ ሰው የምርጫ ካርድ አልወሰደም” ሲል ድምዳሜውን አስፍሯል። የምርጫ ጣቢያዎች ተደራሽነት እና የምርጫ ጣቢያዎች ያሉበት ሁኔታ በምክንያትነት ከተጠቀሱት ውስጥ ይገኙብታል። “የምርጫ ካርድ ለመውሰድ የማያስችሉ ሁነቶች መኖራቸውን፤ ቃለ መጠይቅ ካደረግንላቸው የጥናቱ ተሳታፊዎች ለመረዳት ይቻላል” ብሏል ፓርቲው።
በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች “ከሌሎች አካባቢዎች የመጡ ዜጎች ካርድ ያወጣሉ” ሲል የወነጀለው ባልደራስ፤ “የምርጫ ካርድ የሚታደለው የዜጎችን ማንነት መሰረት ባደረገ መልኩ ነው” ሲል ከስሷል። ከመራጮች ምዝገባ ጋር የተያያዙ ችግሮችን በተመለከተ ባካሄደው ጥናት የደረሰበትን ውጤት በሚያዚያ 29 ቀን 2013 ዓ.ም ለምርጫ ቦርድ በጻፈው ደብዳቤ ቢያሳውቅም፤ ከቦርዱ
“ምንም አይነት ምላሽ እንዳላገኘ” ፓርቲው አስታውቋል። ባልደራስ በጥናቱ ተቃውሞ ያቀረበበት ሌላው ጉዳይ የምርጫ አስፈጻሚዎች አመላመል ሂደት ነው። “የምርጫ አስፈጻሚዎች አመላመል መሰረታዊ ችግር” ሲል ቅሬታውን የገለጸው ፓርቲው፤ ለዚህም ዋነኛ መንስኤው አስፈጻሚዎቹ የተመለመሉባቸው ተቋማት ናቸው ባይ ነው።
ፓርቲው ምርጫ አስፈጻሚዎቹ ተመልምለውባቸዋል ባላቸው በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ፣ በሥራ ፈጠራ ኮሚሽን እና በአዲስ አበባ ሴቶች ሥራ ፈጠራ ማህበር ላይ አመኔታ እንደሌለው በጥናቱ አስታውቋል። ባልደራስ ፓርቲ በጥናቱ ካነሳቸው ነጥቦች ውስጥ፤ ለተወሰነ ጊዜ ለታዛቢዎች ክፍት የሚደረገው የመራጮች መዝገብ ምርመራ ጉዳይ አንዱ ነው። “እንደ ምርጫ ህጉ መሰረት አብዛኛዎች የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮችን መዝገብ ለማስመርመር ክፍት አይደሉም” ሲል ፓርቲው ወቅሷል።
የመራጮች ምዝገባ ሂደቱ “በበርካታ ችግሮች የተተበተበ ነው” የሚል እምነቱን በጥናቱ ያንጸባረቀው ፓርቲው፤ የምርጫ ካርድ ማውጫ ጊዜ እንዲራዘም በድጋሚ ጠይቋል። ባልደራስ የመራጮች ምዝገባ ሂደቱ በተጠናቀቀበት ዕለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። የመጪው ምርጫ የድምጽ መስጫ ቀን ሁለት ሳምንት በቀረው በዚህ ጊዜም፤ ባልደራስ አሁንም ይህን አቋሙን አለመተውን አስታውቋል። የፓርቲው የሰብዓዊ መብት እና የህግ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሔኖክ አክሊሉ፤ “የመራጮች ምዝገባ እንደገና እንዲደረግ ባልደራስ ይጠይቃል.
ባልደራስ በተፎካካሪ ፓርቲ እጩዎች፣ አባላት እና ደጋፊዎች ላይ እየደረሰ ነው ያለውን ወከባ በጥናቱ አንስቷል። “የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ እጩዎች፣ አባላት እና ደጋፊዎች ላይ ከፍተኛ ወከባ እንደሚሰነዘር በጥናቱ ለመረዳት ተችሏል” ሲል የሚከስሰው ፓርቲው፤ ለእዚህም ገዢውን የብልጽግና ፓርቲን ተጠያቂ ያደርጋል። “ወከባ፣ ዛቻ እና ማስፈራሪያው” በማህበረሰቡ ላይ ጭምር ይደርሳል የሚለው ባልደራስ፤ “መራጩን ህዝብ ማዋከብ እና ስጋት ውስጥ ማስገባት የብልፅግና ፓርቲ ዋና ተግባር ሁኗል” ሲል ገዢው ፓርቲ ላይ ሌላ ተጨማሪ ውንጀላ አክሏል። ባልደራስ በዛሬው የዳሰሳ ጥናቱ፤ ፓርቲው በቂ የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን አለማግኘቱን በማንሳት ትችቷል።
የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ለሁሉም ፓርቲዎች ፍትሃዊ ተደራሽነት ሊኖራቸው ይገባ ነበር የሚል እምነቱን የገለጸው ባልደራስ፤ “እንደ ኢ.ቢ.ሲ የመሳሰሉት የመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ግን ይሄን ሃላፊነታቸውን ከመወጣት ይልቅ ባልደራስን በተደጋጋሚ ሲያገሉት ይታያሉ” ሲል ወቅሷል። ፓርቲው የብሔራዊ መገናኛ ብዙሃንን ለምርጫ ቅስቀሳ መጠቀም አለመቻሉ ተደራሽቱን እንደገደበ አመልክቷል። ቅስቀሳዎችን ኧእንዲያሰራጭ በተፈቀደለት መገናኛ ብዙሃንም “መረጃዎች እንዳይተላለፉ መከልከል” እንደሚስተዋልም ጠቅሷል። ባልደራስ የመገናኛ ብዙሃን ሽፋንን በተመለከተ “ችግሩ እንዲቀረፍ ደብዳቤ ብጽፍም ምላሽ አላገኘሁም” ብሏል ሲል ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል።
ምንጭ: ግዮን መጽሔት