News

የብልፅግና ፓርቲ ‘የሚዲያ ሠራዊት’ አባላት በሐሰተኛ መረጃ ሥርጭት እና አሳሳች የፌስቡክ ዘመቻዎች ላይ መሳተፋቸውን የቢቢሲ ምርመራ አረጋገጠ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅህፈት ቤት ህንጻ ከዋትስአፕ ስክሪንሻት ከተደረጉ ምስሎች ጋር

  • ፀሐፊ,አማኑኤል ይልቃል
  • የሥራ ድርሻ,ቢቢሲ አማርኛ
  • ዘገባው ከናይሮቢ

በገዢው ብልፅግና ፓርቲ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ስር የሚንቀሳቀሱ እና ‘የሚዲያ ሠራዊት’ የሚል መጠሪያ ያላቸው የፓርቲው አባላት፤ መንግሥትን በሚተቹ እና በሚቃወሙ ግለሰቦች ላይ በፌስቡክ በተደረጉ የሐሰተኛ መረጃ እንዲሁም ‘የጥላቻ ንግግር’ ተብለው ሊቆጠሩ የሚችሉ ጽሑፎች እና ምስሎች ሥርጭት ላይ እንደተሳተፉ ቢቢሲ ያደረገው ምርመራ አረጋገጠ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወረዳ አመራሮችም በፓርቲው የወረዳ መዋቅሮች ትዕዛዝ በተለይም የመንግሥትን ገፅታ በሰው ሰራሽ መንገድ ለመገንባት ፌስቡክ ላይ በሚደረጉ አሳሳች ዘመቻዎች ላይ እንደሚሳተፉም ምርመራው አሳይቷል። ቢቢሲ ለዚህ ዘገባ በአዲስ አበባ ከተማ የወረዳ አመራር፣ የፓርቲ አባል እንዲሁም በከተማዋ እና በፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሰሩ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች አነጋግሯል።

ቢቢሲ፤ የአዲስ አበባ ከተማ ሰባት ክፍለ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ የፓርቲው የወረዳ መዋቅሮች በዋትስአፕ እና ቴሌግራም ግሩፖች ውስጥ ለሶሻል ሚዲያ ዘመቻዎች የተለዋወጧቸውን መልዕክቶች ተመልክቷል። በግሩፖቹ ውስጥ ለወረዳ አመራሮች እና ሚዲያ ሠራዊት አባላት የሚሰጡ ትዕዛዞችን እና አፈጻጸማቸውን ተከታትሏል። የፌስቡክ ዳታዎችን በመውሰድም ተንትኗል።

የፌስቡክ እናት ኩባንያ ሜታ፤ ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ “ሐሰተኛ አካውንቶችን” በመጠቀም “በኢትዮጵያ መንግሥት” የፌስቡክ ልጥፎች ላይ “ብዛት ያላቸው አዎንታዊ አስተያየቶች” መሰጠታቸውን በምርመራ እንደደረሰበት አስታውቋል። ሜታ፤ በዚህ ድርጊት ላይ በተሳተፉ ሐሰተኛ አካውንት እና ገፆች ላይ እርምጃ መውሰዱን የገለጸ ሲሆን፣ ቢቢሲ ሲከታተላቸው የነበሩ አካውንቶችም እንዲወገዱ ተደርገዋል።

የብልፅግና ፓርቲ በበኩሉ ‘የሚዲያ ሠራዊት’ የሚባል አደረጃጀት “አለመኖሩን” በመግለፅ ለቢቢሲ በሰጠው የፅሁፍ ምላሽ ጉዳዩን አስተባብሏል። የፓርቲው ዋና ፅህፈት ቤት፤ “በተለይ ‘ሐሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግር ተብለው ሊቆጠሩ የሚችሉ ጽሑፎች እና ምስሎች [ተሠራጭተዋል]’ በሚል የተገለጸው ፍጹም ተቀባይነት የሌለው አገላለጽ ነው” ብሏል።

ቢቢሲ፤ የብልፅግና ፓርቲ ‘የሚዲያ ሠራዊት’ አባላት ፌስቡክ ላይ የሚያደርጓቸውን ዘመቻዎች በተመለከተ ለሦስት ወራት ያካሄደውን ምርመራ ውጤት፤ በዚህ ዝርዝር ዘገባ አጠናቅሯል።

line

ከሦስት ወራት በፊት ጥር 2/2016 ዓ.ም. ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ጀምሮ “አቡነ ጴጥሮስ ከሀገር ኮበለሉ” የሚሉ ልጥፎች በበርካታ የኢትዮጵያውያን የፌስቡክ አካውንቶች እና ገጾች መሠራጨት ጀመሩ።

በፎቶ እና ጽሁፍ ከተቀናበረ ምስል ጋር የተሠራጩት እነዚህ ልጥፎች ፌስቡክ ላይ የወጡት፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊ አቡነ ጴጥሮስ ከአዲስ አበባ ወደ አሜሪካ መጓዛቸውን ተከትሎ ነበር።

የኒው ዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት አቡነ ጴጥሮስ ከሀገር የወጡት፤ “ይፋዊ የሆነውን መደበኛ የአሠራር ሥርዓት ተከትለው” እንደሆነ ቢቢሲ ከቤተ ክርስቲያኗ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

በዕለቱ የተሠራጩት ሦስት ዋነኛ ጽሁፎች “ሰበር መረጃ፤ አቡነ ጴጥሮስ ከሀገር ኮበለሉ”፣ “አሜሪካዊው አቡነ ጴጥሮስ ከሀገር ኮብልለዋል!” እና “ከአሜሪካዊ አቡነ ጴጥሮስ ኩብለላ ጀርባ ያሉ እውነታዎች!” የሚል መግቢያ ያላቸው ናቸው።

ጽሁፎቹ አቡነ ጴጥሮስን፤ “በቤተ ክህነት ውስጥ ህቡዕ የፖለቲካ አደረጃጀት በመምራት” እና “የቤተክህነት ሃብት የሆነ በርካታ ገንዘብ እና ንብረት ይዞ በመጥፋት” ይከስሳሉ።

ከሦስቱ ጽሁፎች ውስጥ በብዛት የተሠራጨው “ሰበር መረጃ፤ አቡነ ጴጥሮስ ከሀገር ኮበለሉ” የሚለው ሲሆን፣ ይህ ጽሁፍ በጥር 2 እና 3/2016 ዓ.ም. ብቻ ቢያንስ 1,004 ጊዜ በተለያዩ የፌስቡክ አካውንት እና ገጾች እንደተለጠፈ ቢቢሲ አረጋግጧል። ከግራፊክስ ምስሎች ጋር የተለጠፈው ይህ ጽሁፍ፤ ጥር ሁለት ቀን ብቻ ይህ ቢያንስ 898 ጊዜ ፌስቡክ ላይ ተጋርቷል።

አቡነ ጴጥሮስ “ኮብልለዋል” በሚል ፌስቡክ ላይ ከተሰራጩት ልጥፎች ውስጥ አብዛኛዎቹ “#ፅንፈኝነት_ይውደም” እና “#መከላከያ_የሀገር_ጋሻ” የሚል ሀሽታግ ተያይዞባቸዋል።
የምስሉ መግለጫ,አቡነ ጴጥሮስ “ኮብልለዋል” በሚል ፌስቡክ ላይ ከተሠራጩት ልጥፎች ውስጥ አብዛኛዎቹ “#ፅንፈኝነት_ይውደም” እና “#መከላከያ_የሀገር_ጋሻ” የሚል ሀሽታግ ተያይዞባቸዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን “የማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየተናፈሰ ያለው ወሬ እጅግ የተሳሳተ” መሆኑን በመጥቀስ ጉዳዩን ያስተባበለችው በማግስቱ ነበር። ቢቢሲ ስለጉዳዩ ጥያቄ ያቀረበላቸው አቡነ ጴጥሮስ፤ አስተያየት መስጠት እንደማይፈልጉ ገልጸዋል።

ይህ መልዕክት ከተሰራጨ ከአንድ ወር ገደማ በኋላ “ኮብልለዋል” የተባሉት አቡነ ጴጥሮስ ወደ ኢትዮጵያ ቢመለሱም ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ወደ መጡበት እንዲመለሱ ተደርገዋል።

በዕለቱ ስለ ሲኖዶሱ ዋና ፀሐፊ “መኮብለል” ፌስቡክ ላይ የተሠራጩት ልጥፎች፤ በመደበኛ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች የተሰራጩ የተለመደው ዓይነት የሐሰተኛ መረጃ አልነበሩም። ቢቢሲ ባደረገው ክትትል፤ የመረጃዎቹ ሥርጭት ካለፈው ዓመት ጥር ጀምሮ ከቤተክርስቲያኒቱ ጋር ቅራኔ ውስጥ የገባውን መንግሥት ከመሠረተው ገዢው ብልፅግና ፓርቲ ጋር ግንኙት እንዳለው የሚያሳዩ ማስረጃዎችን አግኝቷል።

መንግሥት ጥር 2015 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ላፈነገጡ የሃይማኖት አባቶች “ድጋፍ ሰጥቷል” በሚል ጎልቶ የወጣው የሁለቱ አካላት መቃቃር፤ አንዳንድ የቤተክርስቲያኗ አባቶች ታጣቂዎችን ደግፈው ያደረጉትን ንግግርን ተከትሎ በዚህም ዓመት ጥር ወርም ቀጥሎ ነበር።

የሲኖዶስ ዋና ፀሐፊው አቡነ ጴጥሮስ መኮብለላቸውን ከሚገልጹት ጽሁፎች ጋር የተያያዙት ምስሎች ምንጮች መካከል የገዢው ብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ፅህፈት ቤት የወረዳ መዋቅሮች የዋትስአፕ ግሩፖች እንደሚገኙበት ቢቢሲ ባደረገው ክትትል አረጋግጧል።

የዋትስአፕ ግሩፖቹ የፓርቲው የወረዳ መዋቅሮች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በዘመቻ መልክ እንዲሰራጩ የሚፈልጉ መልዕክቶችን ‘ለሚዲያ ሠራዊት’ አባላት የሚያስተላልፉባቸው ናቸው።

ቢቢሲ፤ ከእነዚህ የዋትስአፕ ግሩፖች መካከል በአንዱ በሚዲያ ሠራዊት አባላቱ እና በኃላፊዎቻቸው መካከል የሚደረጉ የመልዕክት ለውውጦችን፣ የሚተላለፉ ትዕዛዞችን እና የሚደረጉ ዘመቻዎችን ይዘት ለወራት ሲከታተል ቆይቷል። የዋትስአፕ ግሩፑ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ስር በሚገኝ በአንድ ወረዳ የፓርቲ ፅህፈት ቤት የሚተዳደር ነው።

ምንጭ፡ ቢቢሲ አማርኛ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *