Merera-dawid
Articles

የመረራ ጉዲና እና የዳውድ ኢብሳ ነገር

በሰማነህ ጀመረ

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ምንም ሳይኖራቸው አስተምረው ለትልቅነትና ለኩራት ባበቋቸው ምሁሮች ተክደዋል ። ሕዝባችን ሳይማር ልጆቹን አስተምሯል፤ እየተራበ መግቦ አኑሯ

። ጎኑን መደብ እየጎረበጠው፤ የእንጨት አልጋ ጀርባውን እየላጠው እኛን በአላጋና በፍራሽ አስተኝቷል።

ካለመጫሚያ እግሩን ለጠጠር፤ ገላውን ለአሩር አጋልጦ እየተጓዘ ምሁሩ በመኪና እንዲንፈላሰስ አድርጓ

። በኩራዝና በጫቅማ መብራት እራቱን እየበላ ምሁሩን በኮረንቲ ብርሃን አንደላቋል። የኢትዮጵያ እናቶች ማገዶ ለቅመው፤ እህል ፈጭተው፤ እንስራና ልጅ ተሸክመው፤ ምግብ አብስለው፤ ምርት አምርተው የኢትዮጵያን ምሁር አሳድገውታል። ይህ ሁሉ የተደረገለት የተማረ ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍሎ የማይዘልቀው የውለታ እዳ እንዳለበት አያጠያይቅም።

ምሁሩ ግን ይህን ውለታ መክፈል ሲገባው የኢትዮጵያን ሕዝብ ሰቆቃና ስቃይ በማባባስ ላይ ተጠምዶ ይገኛል። የዘገየ ፍትሕ እንደተነፈገ ይቆጠራል እንዳይሆን እስካሁን የተጓዝንበትን መንገድ መርምረን ያልተከፈለውን ውለታ በክብር ለመመልሰ መነሳት ያስፈልጋል። ውለታ የመክፈያው ጊዜ ነገ ሳይሆን አሁን ነው። ለስልጣን በመቋመጥ፤ በተጨበጠውና ባልተጨበጠው የፖለቲካ ፍልስፍናና አቃቂር እየተሟገትን ሕዝቡን አርስ በርሱ ስናባላው ግማሽ ምእተ ዓመት ስለባከነ ይበቃል። በወገኖቻችን መከራ ላይ ተምረን ፕሮፌሰር፤ መሐንዲስ፤ ዶክተር፤ ጠበቃ፤ ፖለቲከኛ፤ ወታደር፤ ወዘተ ሆነናል። በበቂ ደረጃ እውቀት ገብይተናል። ይህን የትምህርት ክህሎት እና እውቀት ለሕዝባችን እድገት፤ ለሃገራችን ሰላም መፍጠሪያ እናድርገው።

ለዚህ ሁሉ መነሻ የሆኑኝ በረእሱ እንደተጠቀሰው ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እና ኦቦ ዳውድ ኢብሳ ናቸው። ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ. ም. ኢትዮጵያዊያን ለመጪው አምስት ዓመት የሚአስተዳድሯቸውን መሪዎች መርጠዋል። ምርጫው በሰላም የተጠናቀቀ ብቻ ሳይሆን በዓይነቱም ፍትሐዊና ታማኒነትን የተላበሰ ሆኖ በማለፉ ሁሉም አሸናፊ ሆኗል። ሃገሪቱ ካለችበት የፖለቲካ ምህዳር አንፃር ሲታይ ሰላማዊነቱ እጅግ አስገራሚ ነው። በኢትዮጵያ ላይ መአቀብ ለመጣል የሚራወጡት ሃያላን ሃገራት ዛሬ የምራጫውን ሰላማዊነት አድንቀው ውጤቱን ተቀብለዋል።

በአንጻሩ የእኛ ምሁራንና ፖለቲከኞች የጭቃ ጅራፋቸውን ቀጥለውበታል። ለዚህ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናን እና ኦቦ ዳውድን የሚገዳደር የለም። እነዚ ፖለቲከኞች በተላያየ ጊዜ የሚአደናግር እና አፍራሽ አስተያየት ሲሰጡ ተስተውሏል። ዓለም ያደነቀውን ምርጫ ሲአበሻቅጡና ሲአጣጥሉ ተደምጠዋል። ምርጫውን ሃገራዊ ቲአትርና እና ድራማ የሚል የክርስትና ስም እንደሰጡትም ይነገራል። የሕዝብን ምርጭ ማጣጣል ሳያንሳቸው ዛሬ ደግሞ በኦሮምያ ጊዚአዊ መንግስት እንዲቋቋም ጠይቀው አገር ጉድ አስብለዋል። አለቃቸው ጃዋርና ልደቱ የሽግግር መንግስት ይቋቋም ብለው ያስተጋቡትን በተዛዋሪ አቅርበውልናል። በምርጫው ስላልተሳተፉና ከዴሞክራሲው ምህዳር ውጪ ስለሆኑ ተበሳጭተዋል። ይህች የሽግግር መንግስት ጥያቄ በአቋራጭ ወደ ስልጣን መምጫ ፖለቲካዊ ዘዴ መሆኗ ነው። እንኳን ይህን የመሰለ እቃቃ ጨዋታ ቀርቶ የዝም ጠንጋራም እናውቃለን ይላል ያገራችን ሰው።

የእነዚህ ሰዎች በዘረኝነትና በጎሰኝነት እሳቤ የታሸገ ፖለቲካን መስማት ሰልችቶናል። በኋላቀርና በአደገኛ የዘር ፖለቲካ እሳቤአቸው ሃገራችንን ለአደጋ እያጋለጡ ስለሆነ በቃችሁ ሊባሉ ይገባል። የኢትዮጵያ ሕዝብ አስተዋይነት ባይኖር ኖሮ ሃገራችን ሩዋንዳን ሊአስንቅ ወደሚችል የጎሳ እልቂት ሊከቷት ይችሉ እንደነበር የሚአውቅ ያውቀዋል። ምክንያቱም እነርሱን የመሰሉ ምሁራን በሌሎች ሃገራት የፈጸሙት ትምህርት ሊሆነን ይገባል።

ለምሳሌ እ. ኤ. አ. በ1992 በሩዋንዳ ገዢው የሁቱ ፓርቲ ባለሥልጣን አባል የነበሩት ሙጌዜራ ከ1,000 በላይ ለሚሆኑ የፓርቲ አባሎቻቸው ቱትሲዎችን በመግደል እሬሳቸውን ወንዝ እንዲጥሉ የቀሰቀሱት ሕያው ምስክር ነው። የዚህ ቅስቀሳ ውጤት ነው በሩዋንዳ በመቶ ቀናት ውስጥ አንድ ሚሊዮን ንጹሃን ዜጎች የተጨፈጨፉት።

የመረራና ዳውድ ወላጆች በምን ሁኔታ ኖረው ለፕሮፌሰርነትና ፖለቲከኝነት እንዳበቋቸው የምንገምተው ሐቅ አለ። የነርሱ ወላጆች ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ ጋር ተጋብተው፤ ተዋልደው፤ ተጎራብተውና ተፋቅረው መኖራቸውን ለማውቅ ጠንቋይ መቀለብ አያስፈልገንም። የነኝህ ኢትዮጵያዊ ልጆች ናቸው አሁን ምርጫውን እያጣጣሉና ጊዚያዊ መንግስት ይቋቋም በሚል ሃገራችንን ቀውስ ውስጥ ለማስገባት ድፍት ቀና የሚሉት። በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የፖለቲካ ቲያትርና ድራማ መስራት አቁሙ ሊባሉ ይገባል። የንግግራቸው አንደምታ አንድ እና አንድ ነው። ይሄውም ኢትዮጵያዊያንና ዓለም የምርጫውን ውጤት እና የዶ/ር ዓብይን መንግስት ለመጣል የሚደረገ የአመጽ ቅስቀሳ ነው።

ያልተረዱት ጉዳይ ቢኖር የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ ሰሪ እንጅ እንደነሱ ቲያትር አቅራቢ የኪነጥበብ ተዋናኝ አለመሆኑን ነው። ቲያትረኞቹ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እና ኦቦ ዳውድ እንጅ ሌላ የለም። እባካችሁ ምሁራን ለሕዝባችን ያልከፈልነው ብዙ እዳ ስላለብን እጅ ለእጅ ተያይዘን ፕሮፌሰር መረራንና ኦቦ ዳውድን ጨምሮ ሕዝባችንን ለመታደግ እንስራ። መከላከያ መቀሌን ጥሎ ስለወጣ የተሸነፈ መስሏችሁ ከሆነ ተሳስታችኋል፤ ይህ ከሆነ የፖለቲካና የውትድርናን ሃሁ ከማኦሴቱንግ እንድትማሩ እንመክራለን። መንግስትም የመረራ ጉዲና እና የዳውድ ኢብሳን ነገር መርምሮ አደብ ሊያስይዛቸው ይገባልና ይታሰብበት።

አመሰግናለሁ

ሰማነህ ጀመረ፤ ኦታዋ፤ ካናዳ፤ ሰኔ 25, 2013

Source: https://amharic.zehabesha.com/

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *