TPLFChildSoldure
News

የታጠቁ ታዳጊዎች በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ውስጥ መታየትና ያስነሳው ጥያቄ

የ11 ዓመቱ ታዳጊ ከእንጨት እና ብረት የሰራውን መሳሪያ ይዞ የወታደር መለዮ አድርጎ። ሰኔ 25 2013 ዓ.ም. መቀለ።

የፎቶው ባለመብት,GETTY IMAGES/YASUYOSHI CHIBA

የምስሉ መግለጫ,የ11 ዓመቱ ታዳጊ በመቀለ ከተማ እራሱ ከእንጨት እና ብረት የሰራውን መሳሪያ ይዞ እና የወታደር መለዮ አድርጎ። ሰኔ 25 2013 ዓ.ም.።

“እኛ መንደር ይኖር የነበረውን የገደልኩት ልጅ ዛሬም ድረስ በህልሜ አየዋለሁ ‘ዝም ብለሽ እኮ ነው የገደልሽኝ’ እያለ በህልሜ ያነጋግረኛል።”

ይህን ለአሜሪካው ቀይ መስቀል ያለችው በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊካ ጦርነት ውስጥ እንድትሳተፍ የተመለመለች የ16 ዓመት ታዳጊ ሴት ናት።

በሰሜን ኢትዮጵያ በተቀሰቀሰው ጦርነት ውስጥ ታዳጊ ልጆች ተሳታፊ ስለመደረጋቸው በስፋት እየተነገረ ነው። በተለይ የፌደራሉ መንግሥት የትግራይ ኃይሎች ሕጻናት በጦርነቱ ውስጥ ሰለማሳተፋቸው በተደጋጋሚ ከሷል።

ትናንት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የትግራይ ኃይሎች ኮረም እና አላማጣን መያዛቸው ከተሰማ በኋላ የመንግሥታቸውን አቋም ይፋ ባደረጉበት ጽሑፋቸው ህወሓት “ሕጻናትና ወጣቶችን በአደንዛዥ ዕጽ እያሳበደ ወደ ጦርነት እየማገደ ይገኛል” ብለው ነበር።

በተለይ ከሰሞኑ ኒው ዮርክ ታይምስ ‘የትግራይ ኃይሎች የፌደራሉን መንግሥት ጦር ከትግራይ ያስወጡበት መንገድ’ ብሎ በሰራው ዝርዝር ዘገባ ውስጥ የተካተቱት መስሎች በርካቶችን አነጋግሯል።

የኒው ዮርክ ታይምሱ ፎቶግራፍ አንሺ እድሜያቸው ከ15 ዓመት የማይዘል የሚመስሉ ሁለት ታዳጊዎች ኤኬ-47 የተሰኘውን ጠመንጃ አንግበው በሌሎች ታዳጊ ሕጻናት ተከበው ሲራመዱ እንዲሁም በሌላኛው ፎቶ ጉዳት የደረሰበት የሚመስል ሰው በቃሬዛ ተሸክመው የሚሄዱ ሰዎችን ሁለት ኤኬ-47 አንግቦ የሚጓዝ ታዳጊን የሚያሳይ ፎቶግራፍ ትግራይ ክልል ውስጥ አንስቷል።

የ Twitter ይዘትን ይለፉት, 1

የ Twitter ይዘት መጨረሻ, 1

ቢቢሲ እነዚህ በፎቶግራፎቹ ላይ የታዩት ታዳጊዎች በጦርነት ቀጠና ውስጥ የጦር መሳሪያ ይዘው ፎቶግራፍ ስለመነሳታቸው ከፎቶ አንሺው አረጋግጧል።

ታዳጊዎቹ የጦር መሳሪያ ይዘው በጦርነት ቀጠና ውስጥ መታየታቸው ግን በርካቶችን ያስቆጣ ሲሆን የህወሓት ኃይሎች ታዳጊዎችን በጦርነት ማሳተፋቸው “የጦር ወንጀል ፈጽመዋል” ያሉም አልጠፉም።

ህወሓት በጉዳዩ ላይ ምላሽ አልሰጠም።

ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ሕጻናትን ለጦርነት መመልመለ እና ማሳተፍ የጦር ወንጀል ነው ይላል። ፍርድ ቤቱ ከዚህ ቀደም የዲሞክራቲክ ኮንጎ ዜግነት ያለውን እና ቶማስ ሉባንጋ ዳይሎ የተባለ የጦር መሪ እድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችን በጦርነት ውስጥ በማሰለፉ ጥፋተኛ ተብሎ የ15 ዓመት እስር በይኖበታል።

ሕጻን ወታደር ሲባል ምን ማለት ነው?

በተባበሩት መንግሥት የሕጻናት መብት ኮንቬንሽን መሠረት ህጻን ወታደር (ቻይልድ ሶልጀር) ማለት እድሜው ከ18 ዓመት በታች ሆኖ ሳለ በጦርነት ውስጥ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ተሳታፊ እንዲሆን የተመለመለ ማለት ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ እአአ 1949 ላይ ተሻሽሎ ሥራ ላይ የዋለው የጄኔቭ ኮንቬንሽን አንድ ወታደር እድሜው ከ15 ዓመት በታች ከሆነ ሕጻን ወታደር ይባላል ይላል።

ጠመንጃ የያዙ ታዳጊዎች

የፎቶው ባለመብት,SOCIAL MEDIA

የምስሉ መግለጫ,በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ሲዘዋወሩ ከነበሩት ምስሎች መካከል

አንድ ታዳጊ “ሕጻን ወታደር ወይም ቻይልድ ሶልጀር” ነው ለማለት ግዴታ ያ ታዳጊ ጦር መሳሪያ አንግቦ በጦነት ውስጥ በቀጥታ መሳተፍ ብቻ አይጠበቅበትም።

አንድ ታዳጊ የጦር ቡድን ውስጥ ምግብ ማብሰል፣ እቃ መሸከም፣ መላላክ እና ከዚያ የጦር ቡድን ጋር አንዳች ግንኙነት መኖር “ሕጻን ወታደር” የሚለውን ትርጓሜ ሊያሰጥ ይችላል።

እአአ 2002 ላይ በሥራ ላይ የዋለው እና ኢትዮጵያ ፈርማ ያጸደቀችው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕጻናት መብቶች ኮንቬንሽን፤ አገራት እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊዎች በጦርነት ውስጥ ተሳታፊ አለመሆናውን ማረጋገጥ አለባቸው ይላል።

ሕጻናት እንዴት እና ለምን የጦር አባል ይሆናሉ?

ታዳጊዎች በተለየ ሁኔታ በቀላሉ የጦር አባል ተደርገው ለመመልመል ተጋላጭ ናቸው። ለዚህም ምክንያቱ ታዳጊዎች በጦርነት ውስጥ እየሆነ ያለው ነገር እና ውጤቱን በቀላሉ መረዳት ሊሳናቸው ስለሚችል በቀላሉ ተታለው ወደ ጦርነት ሊገቡ ይችላሉ።

የዝቅተኛ ደረጃ ቤተሰብ ልጆች፣ ከወላጆቻቸው የተለያዩ፣ ተፈናቅለው የሚገኙ፣ በጦር ቀጠና ውስጥ ያሉ እና በትምህርት ገበታ ላይ የማይገኙ ልጆች አብዛኛውን ጊዜ በጦርነት ተሳታፊ እንዲሆኑ የመመልመል እድላቸው ሰፊ ነው።

Source: https://www.bbc.com/

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *