የኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ሲቪክ ካውስል
News Press Release

የፍትህ ዋጋ ምን ያህል ነው? – የኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ሲቪክ ካውስል እና የኢትዮጵያ አድቮከሲ ኔትወርክ

የኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ሲቪክ ካውስል እና የኢትዮጵያ አድቮከሲ ኔትወርክ አባላት እና ደጋፊዎች በተለያዩ የአለም ግዛቶች የምንገኝ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የአገር ተቆርቋሪዎች ስብስብ ነን። ድርጅታችን በሀገራችን የተከሰተውን አሳሳቢ ጉዳይ መንግስት ህግ ያስከብር ዘንድ መጠየቃችን ይታወቃል። ኢትዮጵያዊው ድምጻዊ ሃጫሉ በሴረኞች መገደልን መነሻ አድርጎ የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው አካላት ጥላቻን መሰረት ያደረገ ቅስቀሳን ቀጥለውበት ሰሞኑን የተነሳው ግድያ፣ ዘረፋ፣ ንብረት ማውደም እና ሽብር እጅግ አድርጎ አሳዝኖናል!!

ተከባብሮና ተፋቅሮ ከሚኖር መልካም ባህላችን የማይጠበቅ በመሆኑም እጅግ አፈረናል። ህዝባችን ይህን የጥፋት ድርጊት እንዲበረታ፣ እንዲቀጥል ከሚጥሩ እኩይ አካላት በመራቅ ድርጊቱን በጋራ ማውገዝ ይኖርበታል። ኢትዮጵያ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ነች። ይህን ያደረጉ ወገኖች ለፍትህ እንዲቀርቡ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅብናል።

ምስኪኑ ህዝባችን ዘወትር እንደ አይን ብሌን የሚጠብቃትን እናት አገሩን ላፍታም ቢሆን በመከራም በደስታም ሁሌ ከሃሳብ ተለይታ የማታውቀው ኢትዮጵያ፣ ዛሬ የህግ ያለህ ኤሎሄዋን እያሰማች ነው። ሀገራችን ከውስጥም ከውጭም ሊቦጭቋት የሚጮሁትን አውሬዎች እየታገለቻቸው ትገኛለች። እኛም የትላንቱ ታሪክ እንዳይመጣ ከሚጥረው አካል እና ከምስኪኑ ህዝባችን ወገን ቆመን ድርሻችንን በቻልነው መጠን ሁሉ ልንወጣ ዝግጁ ነን። ዜጎች በሰላም ገብቶ የመውጣት መብታቸውን ማንም ከቶ ሊነጥቀው አይገባም። መንግስት የጀመረውን ህግ የማስከበር ሂደት ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እየሰራ እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሳይከሰቱ ህግን ሙሉ በሙሉ የማስክበር ግዴታ አለበት። ምንም አይነት የፖለቲካ ፓርቲ ጥላ ከለላ አንሻም።

ያለፉትን ሁለት ዓመታት ብቻ ብናይ ኢትዮጵያ አንዱን ፈተና ተከትሎ የሚመጣውን ድንጋጤ ስታልፍ ሌላው ደግሞ ይከተላል። በኢትዮጵያ ብርሃን ሆነ ሲባል ጨለማዎች እየተባበሩ ጨለማን ይፈጥሩብናል። ከዳር ቆመው የሚያሟርቱባት እነዚሁ ቡድኖች ኢትዮጵያ ገደል አፋፍ ደረሰችም፣ ፈረሰችም እያሉ የበጎ ዘመንን ማምጣትን ተስፋ አጥብቀው ይቃወማሉ። በአንፃሩ ህዝባችን ደግሞ ኢትዮጵያ ታብፅህ እደዊሃ ይላል በእለተ ፀሎቱ።

ኢትዮጵያ በድሃ ህዝቦቿ የእምነት ፅናት እና ጸሎት እየተጠበቀች በማእበል ታውካ ወዲህ ወዲያ እንደምትል ከባህር ያለች ጀልባ ሆና የለውጥ ጉዞዋ ሳይገታ መንገዷን ቀጥላ መገኘቷ ለኛ ደስታ ሲሆን ለሀገራችን ጠላቶች ደግሞ ራስምታታቸው ነው።

ከ27 ፈታኝ ዓመታት በኋላ ሰላም ሰፍኖ የደስታ ሲቃ ሁላችንንም ይዞን እንዳልነበር ሁሉ ትንሽም ሳይቆይ እርቁም፣ ሰላሙም ያልጣማቸው የስልጣን ጥማት እንጂ ለህዝብ ፍላጎት፣ ለህግ የበላይነት ፋይዳ የማይሰጡ አካላት፣ በደስታና በመልካም የተስፋ እምነት ደማቅ ስጋጃ አንጥፎ በተሸናፊነት የተቀበላቸውን መንግስት እንደመንግስት እንዳይቆም የጥላቻና የዘር ጦራቸውን በመስበቅ ሀገር ያለተረጋጋች እንድትሆን የሚሰሩትን አጥብቀን እናወግዛለን።

የዘመኑን ወረርሽኝ በሽታ ከምንም ሳይቆጥሩ የራሳቸውን የስልጣን ጥያቄ ብቻ የሚመለከቱ፣ የዓለም ወረርሽኝ በአንድ በኩል፣ በውጭ ደግሞ በአባይ ግድብ ከግብጽና ጋሻ ጃግሬዎች ጋር በሌላው የሚፋለመውን መንግስት ሌት ተቀን ፈታ እያሳጡት ነው። በዚህም የመንግስት ቸለኝነት የልብ ልብ የሰጣቸው አካላት ይሄው እያባሉንም ይገኛሉ።

እውነት ነው ብዙ አስደንጋጭ ክስተቶችን አሳልፈናል። ንፁሃን ታርደዋል፣ የለውጥ ታጋዮች ያመጡትን ለውጥ ሳያጣጥሙ ተሰውተዋል። በእውቁ ኢትዮጵያዊ አርቲስት አጫሉ ሁንዴሳ ሞት ደግሞ ሌላ በኦሮሚያ የመቶዎች ሞትና

የአገር ሃብት ንብረት ውድመት ተከተለ። የተሰማው ይዘገንናል።በደል የደረሰባቸው ሲናገሩ መስማትም ራሱ ያስጨንቃል።

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ፣ የወረርሽኙ፣ የአባይ ግድብ፣ የጥላቻ ሴራ ጉዳይ ተዳምረው የአገር ህልውናን መፈታተን ላይ ደርሷል እና መንግስት አገርን አድኖ ለነገ የማስቀጠል ትልቅ ሃላፊነት አለበት ብለን እናምናለን። ይህን ስንል ተጠርጥረው የሚታሰሩ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ሰብአዊ መብታቸው በተከበረ መልኩ ፍትህ እንዲያገኙ መደረግ አለበት። ይህም ህዝብ በፍትህ ተቋም ላይ ያለውን እምነትና ገለልተኝነት የሚፈትንበትን እድልም ይሰጠዋል።

በህወሃት ብቻ ይዘወር በነበረው የጭካኔ መንግስት ዘመን በሀገራችን ኢትዮጵያ የሰው ክብሩ ተዋረደና ሰበአዊ መብቱ ተደፈረ እያልን የጮህን ኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ሲቪክ ካውስል እና የኢትዮጵያ አድቮካሲ ኔትወርክ አባላት እና ደጋፊዎች ዛሬም እንደወትሮው ለሰበአዊ መብት እና የዜጎች ክብር እንቆማለን። በህወሃት ዘመን ስንሰማው ይዘገንነን የነበረው ተመልሶ እውን እንዳይሆን የምንግዜም መሰረታዊ ዓላማችን ነው።

አገር የሚድነው በመንግስት ጥረት ብቻ ነው የሚል እምነት የለንም። መንግስት በወንጀል ጠርጥሬ ያዝኳቸው የሚለውን ዓለም አቀፍ በደነገገው ህግ መሰረት ክርክራቸው ተሰምቶ በአግባቡ ፍርዳቸውን እንዲያገኙ ያድርግም እንላለን። ማንም ዜጋ ከህግ በላይ አለመሆኑንና መንግስትም ሳይፈራ ሁሉንም እኩል ማስተናገድና ፍትህ አሸናፊ እንድትሆን ማድረግ አለበት።

በውጭ የምንኖር ለሰባዊ መብት እና የዜጎች ክብር የምንታገለው ለሀገራችንና ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ባለን ፍቅር እና አክብሮት ነው። በዲያስፖራው የምንገኝ ኢትዮጵያውያን፣ አገር ለማዳንና የህግ የበላይነት እንዲኖር የሚደረገውን ጥረት እንደግፋለን። በሁከት ፈጣሪዎች፣ በዘረኞችና እንዲሁም ተማርን ነን ባዮች የሃገራቸንን መልካም ታሪክ አንሸዋረው በሚያዩ እኩዮች አንሸበር እንላለን።

በመጨረሻ የውጭ መንግስታት፣ የሰበአዊ መብት ድርጅቶችም የኢትዮጵያ መንግስት የገጠመውን ፈተና ቀረብ ብለውና መልክ ባለው መንገድ መረጃን ይዘው እንዲዳኙት እንጂ ውጭ የሚገኙ የጥፋት ሃይሎች በሚነዙት የሃሰት ወሬ እንዳይዳኙም እናሳስባለን።

ፈተናውን በጋራ ታግለን ሰበአዊ መብት እና የዜጎች ክብር በህግ የሚጠበቅባትን ዴሞክራሲያዊት አገርን በአንድነት እንገነባለን!

ቸሩ አምላክ ኢትዮጵያን እንዲጠብቅ ጸሎታችን ነው!

የኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን ሲቪክ ካውስል እና የኢትዮጵያ አድቮከሲ ኔትወርክ July 12, 2020

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *