ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ የስልጣን መንበሩን ከተቆጣተሩ ጀምሮ ለበርካታ ጊዜያት የልባቸውን ስሜት በውብ ቃላት አጅበው ለህዝብ በንግግር አቅርበዋል። ለዚህም ህዝቡ ከመቀመጫው ተነስቶ በተደጋጋሚ አክብሮቱን ገልጿል።
በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን በተረከቡ ሰሞን ፓርላማ ቀርበው አሸባሪ የነበርነው እኛ ነን በማለት የህወሃት እንደራሴዎች በታደሙበት የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ ሲጠይቁ ከመቀመጫዬ ተነስቼ ማጨብጨብ ብቻ ሳይሆን በደስታ አንብቻለሁ። “ስንጠብቀው የነበርውን መሪ አሁን ገና አገኘን፤” በማለት ለብቻዬ በሲቃ ጮህኩ። ያቺ ንግግር ነበረች ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመደገፍና የተጀመረው ለውጥ ከዳር እንዲደርስ መልካም ከሚመኙ መሃል ያደረገችኝ።
ያ ሁሉ ቀረና ዛሬ ግን ጠቅላዩ የመከላከያ ሚኒስቴር ዋና መስሪያ ቤት ህንፃ ምረቃ ስነስርአት ላይ ያደረጉትን ንግግር ስስማ በአድናቆት ከመቀመጫዬ ተነስቼ ከማጨብጨብ ይልቅ ዝምታቸውን ተመኘሁ። ለእነ ስብሃት ነጋ መፈታት የደረደሩት ምክያትት እንኳንስ ሌላ ሰው እርሳቸውንም ማሳመኑን እጠራጠራለሁ። ፈጽሞ ያልተዋጣለት ንግግር!
ምህረት ያደረግነው ስላሸነፍን ነው ይላሉ፤ የእነ ስብሃትን እድሜና ጤንነትን ያነሳሉ፤ እነ ስብሃት በህወሃት ውስጥ ወሳኝ አለመሆናቸውን ይጠቅሳሉ፤ የእነ ሚኒሊክ ዘመንን ታሪክ ያትታሉ፣ ጉዳዩን ስንሰማ እኛም ደንግጠን ነበር ይላሉ። ይህን ሁሉ እርስ በርሱ የሚጣረስ ዝርዝር እየደራረቡ ጠቅላዩ መክሊታቸውንና በቀላሉ የማይገኝ ጸጋና ህዝባዊ አመኔታ እንደ ተራ ሸቀጥ አደባባይ ላይ ቆመው ሲያባክኑት በማየቴ ሃዘን ሰውነቴን ወረረው።
እርሳቸው የሚወክሉትን የኢትዮጵያ ህዝብ እና እስከ እዚች ደቂቃ ህዝብን በሚያሸብሩ፣ በሚገድሉ፣ በሚያፈናቅሉ፣ በሚዘርፉና በሚያተራምሱት ህወሃቶች መካከል ያለውን ስሜት በህሊናዬ ቃኘሁት። የህወሃቱ ጎራ የታባታቸው እያለ በህዝብ ሲዘባበት የወንጀሉ ሰለባ የሆነው ፍትህ ናፋቂው ህዝብ በዜሮ ውሳኔውን እንደ ኮሶ ቢመርህም ጭልጠው ሲባል መስማት ግፍ ሆኖ ነው ተሰማኝ።
ጠቅላዩ ኢትዮጵያን የጸና መሰራት ላይ ለመገንባት ተወሰደ ያሉት እርምጃን አሉታዊ ግዝፈትን ጠንቅቀው የተረዱት አይመስልም። ከተረዱትም ምንም አያመጡም የሚል ስሜት ውስጥ የገቡ ይመስለኛል።
ባለፈው ጥቅምት የሁለተኛው ያለም ጦርነት ከተጠናቀቀ ከ76 አመታት በሁዋላ በጀርመን ለፍርድ የቀረበው የመቶ አመት እድሜ ባለጸጋ የሆነው ጆሴፍ ኤስ የተባለው የናዚ ፓርቲ አባል ከእነ ስብሃት አንጻር ሲታይ ወንጀሉ በጣም ቀላል ነው። ግለሰቡ የእስር ቤት ጠባቂ በነበረ ጊዜ እስረኞችን በመግደል ተባባሪ ነበር የሚል ክስ ነው የቀረበበት። ጠበቆቹ ደግሞ ትእዛዝ ፈጸመ እንጂ ወንጀሉ የአዛዞቹ ሃላፊነት ነው ባይ ናቸው። ጀርመንን የመሰለ የሰለጠነ አገር ሊሞት አንድ ሃሙስ የቀረውን የመቶ አመት አዛንውንት ፍርድ ቤት ማቅረቧ ሰብአዊ ርህራሄ ስለጎደላት ወይንም የግለሰቡ ጤንነት ሳያሳስባት ቀርቶ ነው ብሎ ማለት አይቻልም። የናዚም ፓርቲ ከተሸነፈና በህግ ከታገደ ዘመናት ተቆጥረዋል። ለድርድር የማይቀርብ የፍትህ ጉዳይ ስለሆነ ህግ መከበር ስላለበት እንጂ ይህ ግለሰብ በአስራ አንደኛው ሰአት ቅጣት መቀበሉ ትርጉም ስላለው አይደለም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህወሃት ትጥቅ ባልፈታበት ጦርነት እያኬሄደና ለበለጠ ጥፋትና እልቂት እየተዘጋጀ ባለበት በዚህ ጊዜ ስላሸነፍን ምህረት አወረድን ማለታቸው በራሱ አግባብነት የጎደለው ክርክር ነው። ከሰርን እንጂ አላተረፍንም። እንደ እገር ተሸንፍን እንጂ አላሸነፍንም። አምስት ሺ የሚያህሉ ትምህርት ቤቶች፣ በርካታ ሆስፒታሎች፣ አስር ሺ በላይ የጤና ጣቢያዎች፣ መጠነ ሰፊ ዝርፊያና ውድመት በህወሃቶች ደርሶብን ስላሸናፊነት ማውራት ከንቱ ጨዋታ ነው። ያለቀውን ሰራዊትና ታጋይ ቤት ይቁጠረው።
እኔና አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ የሚያሳስበው በጥጋባቸው ጦርነት አውጀው በረሃ ወርደው ምሽግ ውስጥ በብዙ መስዋትነት የተማረኩ ፋሺስቶች ጤንነትና እድሜ ሳይሆን የተደፈሩት አዛውንቶችና መነኩሴዎች ጤንነት ነው። እኛን የሚያሳስበን እነ ስብሃት አደራጅተው ለጥፋት ባሰማሯቸው የህወሃት ታጣቂዎች በአባቷ ፊት ለአራት የተደፈረችው የ12 አመት እንቦቀቅላ ጤንነት ነው። እኛን የሚያሳስበን በህወሃት የእብሪት ሰራዊት ቤት ንብረቱ ወድሞበት በየጢሻው የተበተነውና የሚበላውና የሚቀምሰው የሌለው በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብና ህጻናት ጤንነት ነው።
እኔ በበኩሌ እነ ስብሃት ከህዝብ የዘረፉትን እየበሉ በአሽከርና ደንገጡር እንክብካቤ እየተደረገላቸው ሸራተን እንደ ለመዱት እያጨሱና እየጠጡ አስረሽ ምቺው ሲሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምስኪኖች ከቀዬቸውና ከቤታቸው ተፈናቅለው ልጆቻቸውን የሚያበሉት አጥተው የሚያነቡባትን ኢትዮጵያ ፈጽሞ ማየት አልፈልግም። ኢትዮጵያም ትርጉሟ ይሄው ከሆነ ለዘላለሙ ትቅርብኝ። እንዲህ አይነት አገር ኢንዲኖነኝ ፈጽሞ አልፈልግም።
ጠቅላዩ በረዱትም ባይረዱትም ስብሃት ነጋ የህወሃት ክፋት ቁንጮ፣ አርማና ምልክት ነው። ስብሃትን ይቅር ብለህ ህወሃትን መወንጀል በህግም በሞራልም ፈጽሞ አይቻልም። የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት የከፈለው መስዋትነትና ያደረገው ትግል መደምደሚያው የስብሃትን ንጽህና ለማረጋገጥና ለመመስከር የሚመስለው ካለ የዋህ ነው። ትግላችን መሰረቱ ፍትህ ፍለጋ ነው። ፍትህ ዋስትና ሳያገኝ አገርም ይሁን ሰላም ትርጉም አልባ ነው።
ይሄ ስህተት በምላስ ታሽቶ የሚስተካከል ተራ ስህተት አይደለም። ማንም ለድርድር ሊያቀርበው የማይገባውን የፍትህ ጥያቄን ከመሰረቱ የሚንድና ጥልቅ ትርጉም ያለው ብዙ ጣጣ የሚስከትል ጉዳይ ነው። ውሳኔው ህዝብና መንግስትን ፊትና ጀርባ ከማድረጉም በላይ በዱር ሸንተረሩ መስዋእትነት የከፈለውንና እየከፈለ ያለውን ታጋይና ወታደር ደም ደመ ከልብ የሚያደርግ ነው ታሪካዊ ስህተት ነው።
እነ ስብሃትን ነጻ ብሎ ሸኝቶ ከህወሃት ጋር መፋለም የሞራልም የስነልቦናም የበላይነትን የሚያሳጣ ግዙፍ ስህተት ስለሆነ እነ ፌልትማን ለዘላለሙ ቢያኮርፉ ይመረጣል። ለመንግስት የሚያዋጣው ህዝብ እንጂ የውጭ ሃይሎች አይደሉም። አሁንም በድጋሚ በጊዜ ይሄንን ታሪካዊ ስህተት ማረሙና ማስተካከሉ የተሻለ ነው። ሳይቃጠል በቅጠል!
Source: