ethiomediaInfo
Opinion

በድል እና በይቅርታ አድራጊነት የሚለካ – ኢትዮጵያዊነት!

በ1874 ዓ.ም የጎጃሙ ንጉሥ ተክለሃይማኖት እና የሸዋው ንጉሥ ምኒልክ፤ እምባቦ ላይ ጦርነት አደረጉ። የሞተው ሞቶ ንጉሥ ተክለሃይማኖት ተማረኩ። ድል ያደረጉት ንጉሥ ምኒልክ… የጎጃሙን ንጉሥ አልገደሏቸውም። እንዲያውን ይቅርታን ለማስተማር ሲሉ፤ በደንብ እያስጠበቁ እራት አብረዋቸው እንዲበሉ ያደርጉ ነበር። ምኒልክ ይህን በማድረጋቸው ህዝቡም ወታደሩም አልተቆጣም። በአመቱ በ1875 ንጉሥ ምኒልክ ምርኳቸውን ይዘው፤ ለአጼ ዮሃንስ ለማስረከብ ወደ ትግራይ አቅጣጫ ተጓዙ። ከአጼ ዮሃንስ ጋር ንግግር ሲጀመር ግን፤ ያልታሰበ ነገር ሆነ። “ንጉሡን ነጻ ልቀቅ፤ ከጎጃሙ ንጉሥ የማረከውን ነፍጡንም፣ መድፉንም ጭምር እንድትመልስለት” ተባሉ። ይሄ ለምኒልክ እና ለሸዋ ሰዎች ትልቅ ስድብ እና ውርደት ነበር። ሆኖም በአጼ ዮሃንስ በርካታ ወታደሮች መከበባቸውን ያወቁት የሸዋ ሰዎች ምኒልክን እንዲህ ሲሉ መከሯቸው። “ጀግና ማለት በጦርነት የሚያሸንፍ ብቻ አይደለም። መሸነፉን ሲያውቅ፤ እንታረቅ የሚል ደግሞ የበለጠ ጀግና ነው።” አሏቸው። ምኒልክም የአዛውንቶቹን ምክር ሰምተው፤ በድል ላይ እርቅ አውርደው፤ ያቺን ዘመን አሳለፉ። ያቺን ዘመን በማሳለፋቸው የዛሬዋን ኢትዮጵያ እና የአፍሪቃን ነጻነት አቆዩልን።

በድል እና በይቅርታ አድራጊነት የሚለካኢትዮጵያዊነት!

(ዳዊት ከበደ ወየሳ)

መፈታታቸውን ስሰማ… በመደመም ዝም አልኩ። ምክንያቱም ‘የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር፤ ሰዎቹ በፍርድ ሂደት መፈታታቸው አይቀርም ነበር’ ብዬ አስብ ስለነበር ነው። ለምሳሌ የእስክንድር ነጋን ክስ ብንመለከት፤ “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” አይነት ነው። እነእስክንድር ነጋ ህዝብን አደራጅተው እና አመጽ አንስተው መንግስት የመገልበጥ፤ ፍላጎቱም አቅሙም እንደሌላቸው እየታወቀ፤ በሃሰት ክስ እና ምስክር ለእስር ተዳረጉ። ይህ የክስ ሂደት በተጨባጭ መረጃ ላይ ያልተደገፈ እና ጭብጥ የሌለው በመሆኑ፤ አቃቤ ህጉ ምንም ሲሟገት ቢውል፤ መጨረሻ ላይ… ህሊና ያላቸው ዳኞች እነእስክንድር የተከሰሱበትን ፋይል መዝጋታቸው አይቀርም ነበር።

እዚህ ጋር ከንቲባ ታከለ ኡማን እናስገባቸው። ከአንድ አመት በፊት አዲስ አበባ የነበሩ ጋዜጠኛ ጓደኞቼ፤ ከቀድሞው ከንቲባ ታከለ ኡማ ጋር ተገናኝተው ለመጨዋወት በቅተው ነበር። በወቅቱ ወዳጆቼ ታከለ ኡማን፤ ከእስክንድር መታሰር ጋር እጁ እንዳለበት ገልጸው ሙግት ገጠሙ። በኋላ ላይ ታከለ ኡማ፤ እጁ የሌለበት መሆኑን ብቻ ሳይሆን፤ እስክንድር እንዲፈታ የሚደረግ ጥረት ካለ ተሳታፊ ሊሆን እንደሚችል ገለጸላቸው። ይህ ብቻ አይደለም። “ለእስክንድርም ንገሩት። እስክንድር ምስክር አድርጎ ከጠራኝ… በኔ አስተዳደር ውስጥ ችግር ያልፈጠረ መሆኑን ፍርድ ቤት ቀርቤ ልመሰክር እችላለሁ። ይሄንንም ንገሩት…” በማለት ዛሬም ይህንን በአንደበታቸው መልሰው ለሚመሰክሩ ጓደኞቼ ገለጸላቸው።

እንግዲህ ይሄን የምንናነሳው፤ በእስክንድር ላይ የተመሰረተው ክስ መሰረት የሌለውና በዳኞች የመጨረሻ ውሳኔ ወቅት ፉርሽ ሊሆን ይችል እንደነበር ለማመልከት ነው። ሌላው ቀርቶ ጃዋር መሃመድ ራሱ፤ “በእስክንድር ነጋ ላይ የተመሰረተው ክስ መሰረት የሌለው ነው” ብሎ ነበር። በዚሁ የነጃዋር መሃመድን ጉዳይ እንመልከት። እዚህ ላይ እራሳችንን አረጋግተን ሁኔታዎችን በጥሞና እንመልከት። አንዳንዶች የጃዋር ስም ሲነሳ አይወዱም። ብዙ ምክንያት ሊኖራቸው ወይም ሊኖረን ይችላል። ዳኝነት መስጠት የሚቻለው ግን፤ በእጃችን ላይ በሚገኝ መረጃ ላይ መሆኑን መዘንጋት የለብንም።

ለምሳሌ… ጃዋር መሃመድ እራሱን እንደሁለተኛ መንግስት አድርጎ ሲናገር፤ ቄሮን የሚያደራጀውና የሚያሰማራው እሱ መሆኑን ሲመሰክር፤ ኦሮሚያ ላይ ለሚደረጉ ነገሮች ፈላጭ እና ቆራጭ፤ የድርጊት ስሌት መስሪያ እጁ ላይ ያለ መሆኑን ያለምንም ፍርሃት ሲናገር አይተናል። እነዚህ ሁሉ ነገሮች በቀላሉ ሊያስከስሱት የሚችሉ ጉዳዮች ነበሩ። አቃቤ ህጉ ግን ጃዋር ላይ የመሰረተው ክስ ከዚህ የተለየ መሆኑን ልብ ይበሉ። ሌላው ቀርቶ ከአራት አመት በፊት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተሰርቆ፤ እነሱን ለሚደግፉ የኦሮሚያ ተማሪዎች መልሱን ያሰራጩ መሆኑን፤ እራሱ ጃዋር መሃመድ በአንደበቱ መስክሯል።

ሌላውን ነገር ሁሉ ትተን… የማትሪክ ፈተና ተሰርቆ መልሱን ማሰራጨት ትልቅ ወንጀል ነው። በአገሪቱ ላይ ከሚደርሰው የኢኮኖሚ ኪሳራ በተጨማሪ በተማሪዎች ላይ የሚያሳድረው የስነ-ልቦና ተጽእኖ ቀላል የሚባል አይነት አይደለም። እናም በነጃዋር የክስ መዝገብ እነዚህ እና እነዚህን የመሳሰሉ ጉዳዮች አልተካተቱም። የክሱ ጭብጥ ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ጋር ተያይዞ የተከሰተው ግጭት እና ረብሻ ነው። በመሆኑም ውሳኔ ከመስጠታችን በፊት፤ በእጃችን ላይ ያለውን እውነታ እንመርምር። ይህን ለማድረግ ደግሞ በጃዋር ላይ ያለንን መውደድ ወይም ጥላቻ ለጊዜው ወደ ጎን ተወት ማድረግ አለብን። እናም ትንፋሻችንን ዋጥ አድርገን፤ እነጃዋር የተከሰሱበትን የክስ መዝገብ እንመልከት።

በነጃዋር መሃመድ ላይ ክስ የተሰረተው፤ በሰኔ ወር 2012 ነው። የክሱ ምክንያት ደግሞ ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ጋር የተያያዘ ነው። ይህን ክስ ለማጠናከር ሲባል ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ስለመጠቀም. እና ቴሌኮምን ስለማጭበርበር… በክስ መዝገቡ ላይ ተካቷል። ሆኖም ባለፈው አመት ጥር 14 ቀን፤ የልደታው 1ኛው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ፤ ይሄን ክስ ጨምሮ ሌሎች ስድስት ያህል የአቃቤ ህጉን ክስ ውድቅ አድርጎባቸዋል። ልብ በሉ። በነጃዋር ላይ ጠንከር ያለ ፍርድ እንዲፈረድባቸው፤ “የጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ 1177/2021” የተጣሰ መሆኑ ተሰምሮበት፤ የተመሰረተው ክስ ውድቅ የሆነው ባለፈው አመት ነው።

ነገሮችን በአጭር ቃል ለማስቀመጥ ያህል፤ ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ መሞት ጋር በተያያዘ፤ በነጃዋር መሃመድ ላይ የተመሰረተው ክስ… በቂ መረጃ እና ማስረጃ አልቀረበበትም። ተከሳሾችም በቂ የመከላከያ ምስክሮች አቅርበው፤ መንግስትን ሞግተዋል። ከጦር መሳሪያ እና ከቴሌኮም ማጭበርበር ጋር በተያያዘ የተመሰረቱት ክሶች በፍርድ ቤቱ ውድቅ ሆነዋል። እናም እነጃዋር መሃመድ ነጻ የሆኑት ትላንት ሳይሆን፤ እነዚህ ክሶች በፍርድ ቤቱ ውድቅ የሆኑ እለት ነው። በሂደት እንዳየነው ከሆነ ደግሞ… በፌዴራል መንግስት ውስጥ የሚገኙት ዳኞች እንደወያኔ-ዘመን፤ ትዕዛዝ እየተሰጣቸው በፍርሃት የሚፈርዱ አይነት አልሆኑም። ይህን ግንዛቤ ውስጥ አስገብተን ወደፊት ሊመጣ የሚችለውን የፍርድ ውሳኔ ስንመለከት ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል አስበነዋል?

እንደእውነቱ ከሆነ… በእስክንድር ነጋ ላይ ያለሃጢያቱ እና ያለጥፋቱ የተመሰረተው፤ በነጃዋር መሃመድ ላይ ያለ በቂ መረጃ እና ማስረጃ የተከፈተው የክስ መዝገብ፤ በዳኞቹ አይን ፊት ረብ የለሽ ነበር። እናም ዳኞቹን “በግድ እና በሃሰት ፍረዱ” እስካላልናቸው ድረስ፤ ክሱን በፈለግነው መጠን ብናጦዘው… በመጨረሻው የፍርድ ቀን ላይ፤ እነጃዋርም ሆኑ እነስክንድር የሚሰጣቸው የዳኝነት ውሳኔ ነጻ የሚያደርጋቸው ነበር። ይህ ከሆነ ደግሞ… አንደኛውን በምህረት መፍታቱ ብልህነት እንጂ፤ ጅልነት አይደለም። ስለሆነም ሌላው ሁሉ ረስተን… ከጀርባ አለ የምንለውን የማይታወቅ ምክንያት ትተን፤ ከላይ በጠቀስነው ስሌት ብቻ፤ የዶ/ር አብይ መንግስት መሸነፉን ሲያውቅ የሄደበት ሁለተኛ አማራጭ፤ ባያስጨበጭብለትም በዚህ ደረጃ የሚያናድድ እና የሚያበሳጭ ሊሆን ባልተገባው ነበር።

የነአቶ ስብሃት ነጋ ጉዳይ… እንደዚሁ ከአጀማመሩ ስህተት አለው። በጦር ሜዳ የያዝከውን ሰው፤ ጉዳዩን በጦር ፍርድ ቤት ውስጥ ማየት ሲገባ፤ ወደሲቪል ችሎት መጥቷል። ምናልባትም ስብሃት ነጋ፣ ቅዱሳን ነጋ፣ አባዲ ዘሙ፣ አባይ ወልዱ እነዚህ ሁሉ ሲታኮሱ ሳይሆን ሲሸሹ የተያዙ ናቸው። በእጃቸውም ላይ የተያዘ የጦር መሳሪያ ኤግዚቢት ሆኖ አልቀረበም። ሆኖም በ’ነዚህ ሰዎች ምክንያት፣ በሺዎች ወይም በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ ወድቋል። ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል፤ ትላልቅ የመንግስት አውታሮች ወድመዋል።

ይህ ብቻ አይደለም…. እነዚህ ሰዎች በስልጣን ዘመናቸው ህዝብን አፈናቅለዋል፤ አስረዋል፣ አስገድለዋል። የኢትዮጵያን ሃብት በዝብዘዋል፤ ብዙ ሚሊዮን ዶላር አሽሽተዋል፤ በውጭ አገርም ንብረት አፍርተዋል። ይሄ በእጃችን ላይ ያለ እውነት ነው። ነገር ግን ብዙዎች መታሰራቸውን እንጂ፤ ታስረው የተመሰረተባቸውን ክስ አልመረመርንም። በእነዚህ ሰዎች ላይ የቀድሞ ጥፋታቸው ተዘርዝሮ ክስ አልተመሰረተባቸውም። አሁን ባሉበት የእድሜ እና የጤንነት ሁኔታ ደግሞ፤ በተከስሱበት ጉዳይ ፍርድ ከማግኘታቸው በፊት እነሱ ይቀድሙ ይሆናል። እርግጥ… አቶ ስብሃት ነጋ የህወሃት ቁንጮ ነው። አቶ ስብሃትን ማሰር ማለት ህወሃትን የማሰር ያህል ሆኖ እየተሰማን እንደሰት ይሆናል። ሲፈታ ደግሞ ህወሃት እንደተፈታ በመቁጥር ልንናደድ እንችላለን። ይህ የፖለቲካ ብሽሽቃችን ያመጣብን አንዱ ችግር ነው።

እነሱ ሲያሸንፉ በህዝብ ደም ላይ ሆነው ሲያበሽቁን፤ እኛ ስናሸንፍ ደግሞ፤ እነሱን ስናበሽቅ – በብሽሽቅ አዙሪት ውስጥ ነው ያለነው። አሁን እነአቶ ስብሃት ነጋ በመፈታታቸው፤ እነሱ ያሸነፉን መስሏቸው የበሸቁ አሉ። እውነታው ግን በነዚህ ሰዎች መፈታት ህወሃት ጭምር መብሸቁ ነው። እውነቱን ለመናገር… በነአቶ ስብሃት ነጋ መፈታት ህወሃት አያተርፍም። ከጭካኔያቸው የተነሳ፤ ህወሃቶች የሚፈልጉት የነበረው፤ የአቶ ስብሃትም ሆነ የእህቱ ሬሳ ከእስር ቤት ተጎትቶ እንዲወጣና በነሱ ሞት “ይኸው አማሮች ገደሏቸው!” ብለው፤ ህዝቡን በህዝብ ለማነሳሳት ነበር። ሆኖም እነአቶ ስብሃት በመፈታታቸው፤ የህወሃት ቁማር ከሸፈ። እናስ ይህንን እንደድል ቆጥረን የማንጠቀምበት ለምንድነው? ለምንስ ነው እንደሰለጠነ ህብረተሰብ አንድ እርምጃ እየቀደምን የማንሄደው? ብሽሽቅ ከሆነ ደግሞ የፈለግነው… ለነአቶ ስብሃት ነጋ ይቅርታ ሲደረግላቸው፤ ይቅርታ አድራጊዎቹ እኛ ጭምር መሆናችንን አውቀን፤ “አዎ እኛ እኮ… ሲለን እንደአምላክ ይቅርታ የምናደርግ ነን” ብለን አንኮራም?

አቶ ስብሃት በእርጅና ምክንያት ቆመው መሄድ አቅቷቸዋል። አባይ ወልዱ በሚሰቃይበት የስኳር ህመም ሳቢያ አይኑ እየተጋረደ ነው። እዚህ ላይ መጥቀስ ስለማያስፈልግ እንጂ፤ አንዳንዶቹ ነርሲንግ ሆም ገብተው በሌላ ሰው እየተረዱ ካልሆነ በስተቀር፤ ራሳቸውን ችለው መኖር የማይችሉበት ደረጃ ላይ እየደረሱ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ከእስር ቤት ወጥተው፤ መቀሌ የሚገኘውን የደብረጽዮን ቢሮ የማዘዝ ስልጣን የላቸውም። ወይም ደሞ… ከበላይ መመሪያ ተቀብለው የሚያስፈጽሙ ክንደ ብርቱ አይደሉም። የአባዲ ዘሙ ወይም የአባይ ወልዱን ወይም የሌሎቹን መመሪያ ተከትሎ አዲስ አበባ ላይ ተፈጻሚ የሚያደርግ አንድ ሰው ማግኘት ከባድ ነው። ከዚህ ውጪ ግን የጃዋርንም ሆነ የስብሃት ነጋን ምላስ እና አንደበት በመፍራት፤ “ለምን ተፈቱ?” ማለት አይቻልም። የታሰሩት ሃሳባቸውን በሃሳብ ማሸነፍ ስላቃተን ከሆነ፤ ከመጀመሪያውም የእስሩ ሁኔታ ትክክል አይደለም ማለት ነው። እኛ በኢትዮጵያዊነታችን ቁርጠኝነቱ ካለን፤ “ምላሳቸውንም አንገታቸውንም ሳናስቆርጥ በሃሳብ ማሸነፍ መቻል አለብን”።

ይህን ማድረግ የማይችሉ ሰዎች ናቸው እንደዥዋዥዌ ሃሳባቸውን ወዲያ እና ወዲህ እያደረጉ የሚያስቸግሩት። እናም እመኑኝ… በዘራችን ሳይሆን ኢትዮጵያዊነታችን ጸንተን ከተገኘን – ፈጽሞ አንሸነፍም።

አንዳንድ ጊዜ የማስታወሻ ቅንብቢታችን አጭር እየሆነ ስለተቸገርን አንዳንድ ነገር እናስታውሳቹህ። ደብረጽዮን እና አባይ ወልዱ በምንም አይነት የማይዋደዱ ሰዎች ናቸው። ደብረጽዮን የትግራይ ፕሬዘዳንት ለመሆን፤ በአባይ ወልዱ ላይ የሸረበው ሴራ፤ በመጨረሻም አባይ ወልዱ እንደምን ሆኖ ከስልጣን እንደተወገደ ብዙዎች የምናስታውሰውን ያህል፤ ጥቂቶች ግን ይሄን ዘንግተን፤ በነአባይ ወልዱ መፈታት የምንናደድ አለን። ይሄ ስህተት ነው። የስብሃት ነጋ ቤተሰብ እና ጌታቸው ረዳ በምንም አይነት ተሳማምተው ሰርተው አያውቁም። አሁንም ከእስር ቤት ተፈትተው ከአላማጣው ጌታቸው ረዳ ጋር አብረው ለመስራት የሚችሉበት ሁኔታ የለም። ይልቁንም እንደኛ አላጓሩበትም እንጂ፤ በነአቶ ስብሃት ነጋ መፈታት የተናደዱት የህወሃት ሰዎች ናቸው። እዚህ ላይ ስብሃት ነጋ – ጌታቸው ረዳን በጥፊ ያላሰበትን አንድ አጋጣሚ እንደገና እናስታውሳቹህ።

የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ተሰብስበው ሲያበቁ፤ እረፍት ላይ ሻይ ቡና እየጠጡ ቆመው ያወጋሉ። ወደዚህ ግድም ስዩም መስፍን፣ ስብሃት ነጋ፣ ጌታቸው ረዳ እና አይነስውሩ አስመላሽ ቡና ይዘው ሲያወሩ፤ ጌታቸው ረዳ ለአስመላሽ፤ “ህወሃት እኮ ከኔ ሌላ ወጣት አመራር የለውም። ሌሎቹንም ብታያቸው እንግሊዘኛ እንኳን አይችሉም። የትምህርት ችሎታቸውም ዝቅተኛ ነው።” እያለ ያጣጥልበታል።

አስመላሽ ደግሞ “ምን ለማለት ፈልገህ ነው? አንተ በህግ ማስተርስ ስላገኘህ እንጂ እንደኔው በህግ ነው የተመረከው” ሲለው፤ ጌታቸው ቀበል አድርጎ… “እኔ ግን ብሬል በጣቴ እየቆጠርኩ አይደለም የማነበው። በጣቴ ብር ነው የምቆጥርበት” ይለዋል።

ይሄን ጊዜ አይነስውሩ አስመላሽ ተናዶ፤ ጌታቸው ረዳን በጥፊ ለማለት ሲሰነዝር፤ ጌቾ ደግሞ ግንበስ ሲል፤ የአስመላሽ መዳፍ ስብሃት ነጋ ላይ አርፎ፤ “ጯ” የሚል ድምጽ ተሰማ።

ጌቾ ካጎነበሰበት እየሳቀ ቀና ሲል፤ ስብሃት ነጋ እና ስዩም መስፍን እያከታተሉ በጥፊ አላተሙት። ግራ የገባው ጌቾ… “እኔ ምን አደረኩ?” ሲል፤ አቶ ስብሃት ነጋ ፈጠን ብሎ፤ “አንተ ጎንበስ ባትል ኖሮ አይስትህም ነበር” ብሎ ልብሱ ላይ የፈሰሰውን ቡና ማጸዳዳት ጀመረ።

ይሄ ነገር እንደቀልድ ይወራ እንጂ፤ የህወሃት ሰዎች እንደዛሬው ከመበታተናቸው በፊት የሆነ ነገር ነው። አንድ ነገር ልብ ልትሉ ይገባል። በቃ ህወሃቶች እነዚህ ናቸው፤ እንደዚህም ናቸው። የጋራ ጠላት ከሌላቸው በስተቀር እርስ በርሳቸው የሚጠፋፉ እፉኝቶች መሆናቸውን በተደጋጋሚ የታሪክ አጋጣሚዎች አይተናል። አሁንም የጋራ ጠላት ስላላቸው እንጂ አቶ ስብሃት ነጋ ከእስር ቤት በወጣ ማግስት ከነሱ ተቃራኒ ሆኑ መግለጫ ቢሰጥ፤ የትላንት ውለታውን ረስተው ሊበሉት ይደርሳሉ።

ደግሞስ… በቀደም ደሴ እና ኮምቦልቻ ተይዘው የነበረ ጊዜ፤ እነዚህ ሰዎች ተፈትተው ቢሆን ኖሮ፤ “ፈርቶ ነው! ተገዶ ነው!” እያልን የየራሳችንን መላምት ልናዥጎደጉድ እንችላለን። አሁን ያ ሁሉ ጊዜ ካለፈ እና ድል በእጃችን ከጨበጥን በኋላ፤ አንዳንዶች በቁማቸው ከሞቱ በኋላ፤ ምህረት ብናደርግላቸው እንደምን እንኮነናለን? እንወነጀላለንስ? እውነት እንነጋገር ከተባለ፤ እነዚህ ሰዎች ከተፈቱ በኋላ ወደ መቀሌ አይሄዱም። ሌላው ቀርቶ ለህክምናቸው ሲሉ፤ ቆይታቸውን የሚያደርጉት አዲስ አበባ ነው። በዚህ ቆይታቸው ወቅት የጥሞና ጊዜ ይኖራቸዋል።

ምናልባትም… ከራሱ ከስብሃት ነጋ ልጅ፣ ከአዜብ መስፍን ወይም ከነጄነራል ሳሞራ የኑስ ጥሩ ትምህርት ሊያገኙ የሚችሉበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል። እናም ቀዳሚውን የሚያውቅ አንድ አምላክ ቢሆንም፤ አንድ ሃሙስ ሲቀራቸው ስለተፈቱት ሳይሆን፤ ስላልተፈታችው አገራችን እናስብ።

አንዳንዶች ደግሞ ስለወታደሩ መስዋዕትነት እና የህወሃት መሪ መፈታት እያጋነኑ ያወራሉ። ደግነቱ መለዮ ለባሹ የፖለቲካ ሙቀት በሞቀ እና በቀዘቀዘ ቁጥር፤ ወዲያ እና ወዲህ እያለ አይዋዥቅም። ፌስቡክ እና ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ተጥዶ ጊዜውን የሚያቃጥል መለዮ ለባሽ የለንም። የኢትዮጵያ ወታደር “አላማው እና መሪውን ይከተላል”። ይህ ደግሞ በወታደራዊ ትምህርት ቤት ጭምር የሚሰለጥኑበት ጉዳይ ነው። ለአላማቸው ደም እና ነፍሳቸውን ሰጥተው ይህቺን አገር ለማቆም የሚታገሉ ናቸው። እነአቶ ስብሃት ነጋን የገቡበት ገብተው ሲይዙ፤ ይህ በራሱ አንድ ትልቅ ድል ነው። ጨዋ ወታደራዊ ስርአት ስለነበራቸው እንጂ፤ ሌሎች ቢሆኑ እንዲህ ያለ የጠላት መሪ እጃቸው ሲገባ ስጋውን ቆራርጠው ለአሞራ ከመስጠት ወደ ኋላ የሚሉ አይደሉም።

ህዝባችንም እንደዚሁ ነው። መያዝ፣ ማሰር እና ሲለውም በምህረት መልቀቅን ያውቅበታል። ብልህ ነገስታት እና መሪዎች ለጠላቶቻቸው ምህረት በማድረግ፤ በብዙ ማትረፋቸውን በተመለከተ፤ ከራሳችንም ከአለምም ታሪክ እያጣቀስን ብዙ ማለት እንችላለን። እርግጥ ነው። ሰዎቹ ከመፈታታቸው በፊት፤ አቃቤ ህጉም ሆነ የመንግስት አካላት ህዝቡን አዘጋጅተውት ቢሆን ጥሩ ነበር። ከሆነ በኋላም የነገሮችን አካሄድ አይተው ህዝቡን በሚያረጋጋ መልኩ አፋጣኝ ምላሽ ቢሰጥ ባልከፋም ነበር። ወይንም ደግሞ ሰዎቹ ሲፈቱ በቅድመሁኔታ ተፈትተው ቢሆን፤ ወይም ተመመሳሳይ ጥፋት ሲሰሩ ከተገኙ ወደ ወህኒ ሊመለሱ እንደሚችሉ ተማምነው ቢፈቷቸው ጥሩ ይሆን ነበር። እነዚህ ሁሉ ነገሮች አልተደረጉም። ስለዚህ መቀየር በማንችለው ጉዳይ ጊዜና ጉልበታችንን መጨረስ የለብንም። በዚያ ላይ… ኢትዮጵያ ከታሰሩትም ከተፈቱትም በፊት ነበረች፤ ወደፊትም ትኖራለች።

ስለሆነም… የዚህ ትውልድ ሰዎች አንድ ነገር ከፊታችን ተደቅኗል። ሰዎቹ በይቅርታ በመፈታታቸው ስንበሳጭ እና ስናለቅስ መኖር አንደኛው ምርጫ ነው። ሁለተኛው ደግሞ የድል አድራጊነት እና የይቅርታ አድራጊነትን ኒሻን ደረታችን ላይ ደርድረን በኩራት ቀጥይ ህይወታችንን መቀጠል እንችላለን። ምርጫው የየግል ነው። በኢትዮጵያ የታሰበባት ሳይሆን፤ ያልታሰበ ነገር እየሆነ ተደንቀናል። የመደነቅ ነገሮች ሁሉ የሚሆኑት ለምክንያት ነውና… የሆነውን ሁሉ ወደ በጎ በመቀየር ኢትዮጵያ እና አምላኳ ወደሚወስዱን ቀጣይ ምዕራፍ እየቀዘፍን እንዘልቃለን። በዚያን ጊዜ በድል እና በይቅርታ አድራጊነት ያጠለቅነው ኒሻን ይበልጥ ይደምቃል። ትውልድም ጸባችንን ሳይሆን ይቅርታችንን ይወርሳል። ኢትዮጵያዊነትም… በወርቅ እና በገንዘብ ሳይሆን፤ በድል እና በይቅርታ አድራጊነት የሚለካበት ቀን ይመጣል። እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ይሄም ያልፋል። በአፍሪቃ ጥቁር ሰማይ ላይ የምታንጸባርቀው ኮከብ ግን ፀዳሏም፣ ብርሃኗም ለዘላለም አይጠፋም።

Source: https://www.facebook.com/ethioMediaForum

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *