raya
Opinion

የራያን ሕዝብ ትግል የሁሉም አማራ የማድረግ ተልዕኮ! – ሲሳይ መንግስቴ (ዶ/ር)

August 6, 2022

ከባለፈው አመት አጋማሽ ጀምሮ የራያን ሕዝብ የነጻነት እንቅስቃሴ መልክ በማስያዝ የወሎ ብሎም የሁሉም አማራ ጉዳይ የማድረግ ስራችንን አጠናክረን ቀጥለናል። በዚህም መሰረት አምና የተለያየ ቅርጽና ስያሜ ይዘው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ቡድኖች ያሉበትን ሁኔታ በመገምገም የተጠናከረ ትግል ለማካሄድ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነበረብን።

ይህንን ሀሳባችንን ወደ ተግባር ለመቀየርም መጀመሪያ ከሞላ ጎደል ከሁሉም የራያ ወረዳዎች ማለትም በዋናነት ከራያ-ወፍላ፣ ከራያ-አላማጣ፣ ከራያ ባላ (ጨርጨር)፣ ከራያ-ቆቦ ወረዳዎች፣ ከኮረም ከአላማጣ እና ከቆቦ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ በርካታ ተሳታፊዎች በተገኙበት ቆቦ ከተማ ላይ በሚገኘው ጥላሁን ግዛው አዳራሽ ውይይት በማድረግ ትግሉ መልክ መያዝ እንዳለበት ተማመንን።

በዚህም መሰረት የራያ አማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ በሁለት አመት ቆይታው ውስጥ ያከናወናቸውን ተግባራት የተመለከተ አጭር ሪፖርት አቅርቦ በጥሞና መከርንበት። በመጨረሻም ጥንካሬዎቹን አጠናክሮ ለማስቀጠልና ክፍተቶችን ለመሙላት ይቻል ዘንድ በመጀመሪያ የስያሜ ማስተካከያና የአመራር ለውጥ ማድረግ እንደሚገባም በሁሉም ዘንድ ታመነበት።

ከዛም የኮሚቴውን ስያሜ “የወሎ ራያ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ” በሚል እንዲስተካከል በማድረግ የራያ ሕዝብ ከወሎ ሕዝብ ጋር ያለውን የስነ ልቦና አንድነት፣ የባህል ትስስር፣ ማህበራዊ ግንኙነት፣ የምጣኔ ሀብት መስተጋብር፣ የታሪክ ቁርኝትና የጋራ አስተዳደራዊ እንቅስቃሴ ለማጠናከር ጥረት ተደረገ። ይህም ሁኔታ የተሳታፊዎችን ይሁንታ አገኘ።

ቀጥሎም የአመራሩን ስብጥርና አደረጃጀት ለማስተካከል ቀደም ሲል ወልዲያ ላይ በተደረሰበት ስምምነት መሠረት የቦታ ቅርበት፣ የመምራት አቅምና ፍላጎት፣ ቁርጠኝነትና የማስተባበር ችሎታን ታሳቢ ያደረገ አዲስ ምርጫ ተካሄደ። በዚህም መምህር ኃይሉ አበራ በላይ የኮሚቴው ዋና ሰብሳቢና አዲሱ በላይ ደግሞ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው ተመረጡ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአርባምንጭ ቅስቀሳ በከፊል

የስራ አመራር ቦርዱን ደግሞ በዋነኛነት ሄኖክ አዲሴ፣ መምህር ፋንታ ታረቀ እና ሲሳይ ሰየመ እንዲመሩት ተወሰነ። እንግዲህ በዚህ አመት እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች የዚህ ለውጥ (Reform) ውጤቶች ናቸው ማለት ይቻላል። በዚህም መሰረት ቀደም ሲል በወልዲያና አካባቢው የሚገኙ ራዮችና የወልዲያ ወጣቶች የተሳተፉበት ፍሬያማ ስብሰባ ተካሄደ፣ ከዛም አዲስ አበባ የተለያዩ ስብሰባዎችን በማድረግ እንቅስቃሴውን ለማስፋት የሚያስችሉ ስራዎች ተከናወኑ።

ይህንን ልምድና ተሞክሮ መሰረት በማድረግም ነገ እሁድ ነሀሴ 1/2014 ዓ,ም በወሎዋ መዲና ደሴ ከተማ ላይ በሚገኘው ወሎ ባህል አምባ አዳራሽ ከጧቱ 2:30 ጀምሮ የማይቀርበት ታላቅ ጉባኤ ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን ኮሚቴው አስታውቋል። ይህን ጉባኤ ለየት የሚያደርገው በወሎዋ መዲና ደሴ ላይ መካሄዱ ብቻ አይደለም።

ይልቁንም ከራያ እና ከአዲስ አበባ የሚመጡ ተሳታፊዎችና የራያ-ቆቦ የባህል ቡድንም የሚገኙበትና መላውን የአማራ ሕዝብ ማነቃነቅ የሚቻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር ያለመ መሆኑም ጭምር ነው። እናም በደሴና በኮምቦልቻ አካባቢ የምትገኙ ወገኖቻችን ሁሉ በዚህ ታላቅና ታሪካዊ ጉባዔ ላይ ተገኝታችሁ የበኩላችሁን አስተዋጽዖ ታደርጉ ዘንድ በክብር ተጋብዛችኋል።

ሲሳይ መንግስቴ (ዶ/ር)

ኢትዮጵያ፣ በስምሽ የራያ ህዝብ ሰቆቃ

Source: zehabesha

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *