Press Release

በሕግ ማስከበር ሽፋን የሚፈፀሙ ፀረ-አማራ እርምጃዎች የሚያረጋግጡት የቡድን የበላይነት አይኖርም! – የአብን የሕዝብ ተወካዮች

በሕግ ማስከበር ሽፋን የሚፈፀሙ ፀረ-አማራ እርምጃዎች የሚያረጋግጡት የቡድን የበላይነት አይኖርም!

(በአማራ ክልል ምክር ቤት የአብን የሕዝብ ተወካዮች: ወቅታዊ ኹኔታን በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ)

በዛሬዋ ኢትዮጵያ አመፅ፣ ቀውስ፣ ጦርነት እና ይኼንን ተከትሎ የሚፈጠር ውድመትና ሰብዓዊ ስቃይ የአንድ ቡድን ብሔራዊ አላማ ማስፈፀሚያ መሣሪያዎች ተደርገዋል። በመደበኛና ኢ-መደበኛ መልኩ የሚፈፀሙ የቀውስና ግጭት አዙሪቶች በጥቂቶች የተያዘን የአገራዊ መልሶ-ብየና (Deconstruction) ቡድናዊ ዓላማ ማስፈፀሚያ በማድረግ የዜጎችን ስቃይ አብዝቷል።

ከአማራ ሕዝብ የሚመጣ የሥልጣን ተገዳዳሪነት እንዳይኖር ለማድረግ በሚል ስሌት አማራውን ኹለንተናዊ እረፍት የመንሳት የቀውስ ስትራቴጅ በየጊዜው እየተፈፀመ ቀጥሏል። ሕግ ጥሶ ቀውስ በመፍጠር መልሶ «ሕግ ማስከበር» የሚባል ቀውስ ጠማቂነት ደግሞ የአመፅ ማስፈፀሚያ ሥልት ተደርጓል። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት «ሕግ ማስከበር» ወደረኛን ማውደሚያ መሣሪያ እንጂ የመንግስታዊ ኃላፊነት መገለጫ እንዳልሆነ በሥርዓቱ መዋቅር የሚፈፀሙ አስነዋሪ ሕገ-ወጥ ተግባሮችን አገር ያወቃቸው፣ ፀሐይ የሞቃቸው ናቸው። የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት የማያከብር መንግስት፣ የዜጎችን የመንቀሳቀስ መብት የገደበ መንግስት፣ የዜጎችን ኃብት የማፍራትና በአገራቸው የመረጡት ቦታ የመኖር መብት የነጠቀ መንግስት፣ በይፋ የዘር ማፅዳት የሚፈፀምባትን አገር «እየመራሁ ነው» የሚል መንግስት ስለሕግ መከበር የሚያወራበት ሞራል የለውም።

በመሆኑም እኛ በአማራ ክልል ምክር ቤት የአብን የሕዝብ ተወካዮች:-

1. የተከበሩ ዶ/ር በቃሉ ታረቀኝ
2. የተከበሩ ዶ/ር ተፈሪ አለም
3. የተከበሩ ዶ/ር አስረሳከኝ ብርሃኑ
4. የተከበሩ ሀብታሙ በላይነህ
5. የተከበሩ ወ/ሮ እመቤት ከበደ
6. የተከበሩ ወ/ሮ ሥርጉት በላቸው
7. የተከበሩ ሐውልቱ መለሰ
8. የተከበሩ የሽዋስ መብራቴ
9. የተከበሩ ጌትነት ተስፋ
10. የተከበሩ ኑርልኝ ጋሻው
11. የተከበሩ አየነው ተመስገን
12. የተከበሩ ጥሩነህ አበበ
13. የተከበሩ ያሬድ የኔዓለም

ከዚህ የሚከተሉትን ጥሪዎች ለፌደራሉ መንግስት፣ ለአማራ ክልላዊ መንግስት፣ ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እና ለመላው ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የሰብዓዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ተቋማት ሁሉ እናቀርባለን።

1) የግብርና ግብዓቶች በአስቸኳይ ለአማራ አርሶ አደር እንዲቀርብ እንጠይቃለን፤

በመላው ኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈፀመው ሥርዓታዊና መንግስታዊ ጥቃት የአርሶ አደሮች ሕልውና ላይ ደርሷል። በፌደራልና የክልል መንግስታት ውድቀት በተከሰተ ጦርነት ያለፉትን ሁለት ዓመታት ያለውን ብቻ ሳይሆን የማይተካውን ለጦርነት ሲገብር የከረመው የአማራ አርሶ አደር፣ ዛሬ ለሌላ ዙር ጦርነት ተዳርጎ እንዲሁም የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ተከልክሏል። አርሶ አደሩ በግብርና ግብዓት ችግር የዘር ወቅት እያለፈበት በመሆኑ ጥያቄውን በተደራጀና በሰላማዊ መንገድ ለመንግስት ቢያቀርብም ከሽንገላ ያለፈ ምላሽ አልተሰጠውም። የምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ ብቻ ሳይሆን የትኛውም መንግስታዊ አገልግሎትና ምርት በፍትኃዊነት በወቅቱና በተፈለገው መጠን ለዜጎች ማቅረብ የመንግስት ዝቅተኛ ግዴታ ቢሆንም የመንግስት አገልግሎት ቤተኛ እና ባይታወር የሚፈጠርበት ሆኗል።

በአማራ ክልል ምክር ቤት መጋቢት 1-3 ቀን 2015 ዓ.ም በተካሄደ 6ኛ ዙር 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ የተከበሩ ዶ/ር ኃይለማርያም ከፍያለው ከግብዓት አቅርቦት ጋር ተያይዞ በ2014 የበጀት ዓመት የተፈጠረው ችግር እንዳይፈፀም ምን እተሰራ ነው? በሚል ከተከበሩ የምክር ቤት አባላቱ ለተነሳላቸው ጥያቄ ሲመልሱ «በ2015 በጀት ዓመት ክልላችን የማዳበሪያ ግብዓት እጥረት እንደይገጥመው በወቅቱ እየተጓጓዘና በገበሬዎች ሕብረት ሥራ ማኅበራት አማካኝነት በስርጭት ላይ እንደነበር» ለምክር ቤት አባላት ገልፀው ነበር።

ሆኖም አሁን ላይ ገበሬው «በማዳበሪያ እጥረት መዝራት አልቻልንም!» ብሎ አቤቱታ ሲያቀርብ ደግሞ «ወደብ ላይ ደርሶ እየተጓጓዘ ነው፤ ወረዳዎችም አላሰራጭ ብለው ነው።» የሚል እርስ በእርሱ የሚጋጭ፣ ውኃ የማይቋጥር አሳዛኝ ምላሽ ሰጥተዋል። ይህ የኃላፊው ምላሽ ሕዝብንና የክልል ም/ቤቱን ከመሸንገል እና ከመናቅ በላይ የችግሩን ምንጭ በመሸፋፈን በፌደራልና የክልል መንግስታት ቸልተኝነት እና ደባ የተፈፀመ ለመሆኑ ማሳያ ነው።

በመሆኑም አንድ ሰኔ የነቀለውን አርሶ አደር አስር ክረምት እንደማይመልሰው እየታወቀ የግብርና ግብዓትን በመከልከል የአማራ ገበሬ ላይ የሚፈጸመውን መንግስታዊ ሸፍጥ በጽኑ እያወገዝን የክልሉ ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ በመጥራት በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ ገበሬው ማሳውን ሸፍኖ የሚከርምበትን አፋጣኝ አቅጣጫ እንዲያስቀምጥ ጥሪ እናቀርባለን። የግብርና ሥራ መውደቅና መቋረጥ ዳፋው ለሁሉም የአገራችን ሕዝቦች የሚደርስ በመሆኑ መላ ኢትዮጵያውያን ከአማራ ገበሬ ጎን እንድትቆሙ እናሳሰባለን።

2) «በሕግ ማስከበር» ሽፋን አማራ ላይ የተከፈተው ጦርነት በአፋጣኝ እንዲቆም እንጠይቃለን፤

ለሕግ እና ሥርዓት ያለውን ንቀትና አቅላይነት በተግባር ደጋግሞ ያረጋገጠው የብልፅግና መንግስት ሕግ ማስከበርን ለፖለቲካዊ ሸፍጥ እና ተገዳዳሪን የማድቀቂያ ሽፋን ሲያደርገው ከርሟል፤ አሁንም አጠናክሮ ቀጥሏል። የአማራ ምክር ቤት የአብን አባላት የአማራ ክልልን የጸጥታ መዋቅር የመበተን ጉዳይ የክልሉን ነባራዊ እውነታዎች ያላገናዘበ ፣ ከክልሉ የፀጥታ መዋቅርም ሆነ የክልሉ አመራር እና የሕዝብ እንደራሴዎች ያልመከሩበት አደገኛ እርምጃ መሆኑን በቀን መጋቢት 30 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣነው መግለጫ አሳውቀን ነበር። ሆኖም ጉዳዩ የፌዴራል መንግስትን የሚዘውሩ ቡድኖች ፖለቲካዊ ደባን ማስፈፀሚያ ስልት ስለነበር በሚዲያ ከሰው፣ በሚዲያ አፍርሰው፣ በሚዲያ ጦርነት በማወጅ የክልሉን የጸጥታ መዋቅር እንዲፈርስ ተደረገ። ዓላማው የጸጥታ ኃይሉን በማፍረስ በአማራ ሕዝብ ላይ ጦርነት ማወጅ የነበረ በመሆኑ ወዲያው «የሕግ ማስከበር» በሚል ክልሉ ላይ ጦርነት ታወጀ።

በታሪካችን ወደር የሌለው የሰሜኑ ጦርነት «ሕግ ማስከበር» በሚል ሽፋን ሚሊዮኖች ያለቁበት፣ በትሪሊዮን ብር የሚገመት ሀብት የወደመበት ነው። ዛሬም «በሕግ ማስከበር» ስም በአማራ ሕዝብ ላይ ግልፅ መንግስታዊ ጦርነት አውጇል። በመንግስት በኩል ያለውን ሁኔታ ከintensity of hostility እና organization አንፃር ስንመለከተው ከመደበኛ ጦርነት ውጭ ሌላ ሊባል የሚችል አይደለም። ትናንት ዋጋ ከፍሎ ሥርዓቱንና አገር የታደገው የአማራ ልዩ ኃይል እና ፋኖ የሥርዓቱ ገዢዎች ፖለቲካዊና ቀጠናዊ ስሌቶች ለማሳካት ሲባል ክሕደት ተፈፅሞበት እየተወጋ ይገኛል። ከሁለት ዓመት የሰሜን ጦርነት እና የጦርነት ድጋፍ ጫናዎች የተረፈው ወገናችን በሌላ ጦርነት እየተገደለ ነው፤ ሀብትና ንብረቱ እየወደመ ነው። ስለሆነም አሁን የፌደራሉ መንግስት በአማራ ክልል እየፈፀመ ያለው ድርጊት መንግስታዊ ሽብር እንጅ ሕግ ማስከበር ባለመሆኑ፦

ሀ) የፌደራል መንግስት ከሕግ ውጭ በአማራ ክልል የሚያደርገውን ጠልቃ ገብነት በማቆም ለአላስፈላጊ ጦርነት ያስገባውን ጦር በአስቸኳይ ወደ ካምፕ እንዲመልስ እንጠይቃለን።

ለ) የክልሉ ምክር ቤት ከሕግና አሰራር ውጭ በፌደራል መንግስቱ በሕዝባችን ላይ በተከፈተው ጦርነት ላይ በመወያዬት አስፈጻሚ አካሉን ማብራሪያ እንዲጠይቅ እንጠይቃለን።

ሐ) የአማራ ክልል መንግስት ፡ ትናንት ግዴታውን መወጣት ባልቻለበት ወቅት ደርሰውለት ከውድቀት የታደጉ የአማራ ልጆችን ማሳደድ አቁሞ፥ በምክር ቤት አባላት እና በሚመለከታቸው አካላት በኩል ከልዩ ኃይልና ፋኖ አደረጃጀቶች ጋር አግባብነት ያላቸው ምክክሮች እንዲያደርግ እንጠይቃለን።

መ) «በሕግ ማስከበር» ሰበብ ከክልሉ ውጭና በክልሉ በማንነታቸው ምክንያት የታፈኑ እና በየማጎሪያው ያሉ አማራዎች እንዲፈቱ እና የተያዘው አማራን ለይቶ ማሳደድ በአስቸኳይ እንዲቆም እንጠይቃለን፤

ኢትዮጵያን የአማራ የስቃይ ምድር የማድረግ ስርዓታዊ ደባው መሸከም ከሚቻለው በላይ አይነተ ብዙ ሆኗል። የደረሰ ውድመት፣ ጅምላ ግድያ እና መፈናቀል ሳያንስ በደሉን የተናገሩና በደሉን የሚያሰሙ የአማራ ልጆች፣ መንግስት ይፈፅመዋል ተብሎ በማይገመት ሁኔታ ልክ የማፍያ ቡድኖች እንደሚያደርጉት እያፈኑ መሠወርን፣ ማሰቃዬት፣ የጅምላ እስር እና መሳደድ እየተፈፀመ ነው። በተለይም በአዲስ አበባና የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቤቶች ሳይቀር የአማራ ማጎሪያና ማሰቃያ እስር ቤት እየተደረጉ ስለመሆኑ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ታሣሪዎች ሁኔታ የሚመሰክረው ኃቅ ነው።

ስለሆነም የአማራ ልጆችን እያፈኑ በጅምላ በማጎር ዳር የሚጸና መንግስታዊ ሥልጣንም ሆነ ዳር የሚደርስ ዓላማ እንደማይኖር በማመን ሕግ እየጣስኩ «ሕግ አስከብራለሁ» የሚለው መንግስት ከዚህ ሕገ-ወጥ እና ፀረ-አማራ ተግባር እንዲታቀብ ደጋግመን ማሳሰብ እንፈልጋለን። ይኼ ፍፁም ፀረ-አማራ የሆነ ሁሉንአቀፍ የአማራ ጥቃት እንዲቆም ለመንግስት፣ ለመላ ኢትዮጵያውያን እና ሌሎች አካላት ሁሉ ጥሪ እናቀርባለን።

ሠ) በሕግ ማስከበር ስም በማንነታቸው ምክንያት በጅምላ የታሰሩ ወጣቶች፣ ምሁራን፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ የኃይማኖት አባቶችና በልዩ ልዩ አደረጃጀት መሪዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲፈቱና በዚህ ሂደት በንጹሃን ላይ ወንጀል የፈጸሙ የጸጥታና የመንግስት አሥፈጻሚ አካላት በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚሉ እንጠይቃለን።

ረ) መላው ኢትዮጵያውያን እና ዲፕሎማቲክ ማሕበረሰብ ይሔንን ታሪክ ይቅር የማይለውን እና መንግስት «ሕግ ማስከበር» እያለ የሚያቃልለው ጦርነት እንዲቆም በጎ ጫና እንዲያሳርፉ እንጠይቃለን።

3) የአማራ ክልል ሉዓላዊ የአሥተዳደር መብቶች እንዲከበሩና ጣልቃ ገብነቶች እንዲቆሙ እንጠይቃለን፤

አገራዊ ጉዳዮችን በማዕከላዊነት የመጠቅለል ዝንባሌዎች የጭቆና ኢንስትሩመንት ሆነዋል። የፓርቲ ፖለቲካ ማዕከላዊነት የሕዝብን ሉዓላዊ የራስ አስተዳደር መብቶች እና መዋቅሮች የመሻር መብት የላቸውም። የወታደራዊና አመፅ መብቶችን በማዕከላዊነትና በብቸኝነት የመጠቅለል ሙከራዎች የክልሎችን ሕጋዊ መብት ድንበሮች የሚያፈርስ ሊሆን አይገባም። አሁን መንግስት «ሕግ እያስከበርኩ ነው» የሚለው በሕገ-መንግስቱ ዳር ድንበር የመጠበቅ ኃላፊነት የተሰጠውን መከላከያን ከሕግና ከአሰራር ውጭ በሕገ-ወጥ መንገድ በመጠቀም ነው። የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት «የተለዬ ሁኔታ አጋጥሞኛል» በሚል የፌደራል መንግስቱንና የመከላከያን ድጋፍ ባልጠየቀበት ሁኔታ በፌደራል የሚገኙ ጥቂት የክልሉን ተወላጅ ሹመኞችን በመጠቀምና በእነሱ አማካኝነት ክልሉን ከአዲስ አበባ የመምራት ፍላጎትና ሙከራ በተደጋጋሚ ታይቷል።

ስለሆነም የፌደራሉ መንግስት የክልሉን አመራርና ምክር ቤት መብቶችና ኃላፊነቶች እየተጋፋ ይገኛል። የፌደራሉ መንግስት ባልታወጀ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የአማራ ክልልን በቀጥታ እያስተዳደረ ይገኛል። በመሆኑም የክልሉ ምክር ቤት ከሕግና አሰራር ውጭ በፌደራል መንግስቱ እየተፈጸመ ያለውን ጣልቃ ገብነት እና በሕዝባችን ላይ እየደረሰ ያለው ውድመት ላይ በመወያዬት አቋም እንዲይዝ እንጠይቃለን።

4) በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል የሚፈፀመው የዘር ማፅዳት በአስቸኳይ እንዲቆም እናሳስባለን፤

የአማራ ሕዝብን ማዕከል አድርጎ በተሰበከው የጥላቻ ስሁትዊ ትርክት ሕዝባችንን ላለፉት 30 ዓመታት በተለይም ደግሞ ባለፉት 5 ዓመታት መዋቅራዊ ድጋፍ ያለው ሁሉንአቀፍ ፍጅት እየተፈጸመበት ይገኛል። «የሠፋሪ ቅኝ ግዛት ተፈፅሞብናል፤ ወራሪ እና ሠፋሪ» በሚሉ በአንዳንድ የኦሮሞ ብሔርተኞች ሲሰበኩ የቆዩ አሉታዊ ትርክቶች፣ በአንድ በኩል ሀውልት ሲቆምላቸው፣ በሌላ በኩል ሐውልት ሲፈርስባቸው እያየን ቆይተናል። አሁን ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ብልጽግና መራሹ መንግስት ሥልጣኑን ለማጽናት «ሠፊሪን ማፅዳት» በሚል በአማራ ሕዝብ ላይ የዘር ማፅዳት እየተፈፀመ ነው። አሁንም በ«ሕግ ማስከበር» ሽፋን እየተፈፀመ ያለው ወንጀል ከአማራ የጸዳች ኦሮሚያን የመፍጠር ፕሮጀክትን እውን ለማድረግ ያለመ ስለመሆኑ ተፈናቃዮችና ተሳዳጆች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ታዛቢዎችም የሚመሰክሩት ኃቅ ነው።

ይኼ ፀረ-ሕዝብ ተግባር በአዲስ አበባ ብቻ ግማሽ ሚሊዮን ሕዝብ አፈናቅሏል፤ ዜጎች ለዘመናት ለፍተው የሠሩት ንብረታቸው ወድሟል። ለረጅም ዓመታት ከኖሩበት እና ልጅ ወልደው ካሳደጉበት ቤታቸው ተፈናቅለው ሜዳ ላይ ወድቀዋል። ተከራይቶ የመኖር መብታቸው ተነፍጎ የፈረሰ ንብረታቸውን ይዘው የመንቀሳቀስ መብታቸው ክልከላ ተጥሎበታል። ይኼ ግፍ የሚያደላለት እና ለጥቃት የሚመርጣቸው ሕዝቦች መኖሩ ግልፅ የዘር ማፅዳት ተግባር ያደርገዋል። ጉዳዩ ነባር ትርክትን የማስፈፀም እና «ከተሞቻችን በአማራ ተይዘዋል» ሲባልለት የኖረውን ትርክት የማረም ነው። ይኼን የዘር ማፅዳት የኦሮሚያ ክልል መንግስት በሌሎች 600 የሚደርሱ የክልሉ ከተሞች ተጠናክሮ የሚቀጥል ተግባር መሆኑን አሳውቋል። ስለሆነም፦

ሀ) ይኼ ዓለምአቀፍ ወንጀል ለአገራዊ አንድነት የማይበጅ ለሕዝቦች አብሮነት የማይጠቅም ዘላቂ ቅራኔን የሚፈጥር መሆኑን በማሰብ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከዚህ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እንዲታቀቡ እንጠይቃለን።

ለ) የፌደራሉ መንግስት፣ በፌደራል ፓርላማ የምትገኙ የአማራ ወኪሎች፣ የክልል መንግስታት፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች ይኼንን በአማራ ላይ ያነጣጠረ የዘር ማፅዳት እና ዘር ማሳሳት እንዲሁም የጅምላ ግድያ እና ማፈናቀል እንዲቆም እንድትሠሩ እንጠይቃለን።

ሐ) በኦሮሚያ ክልልና በአዲስ አበባ በሚኖሩ አማራዎች ላይ የሚፈፀም ማስፈራራት፣ አፈና፣ መድሎና ሥነ-ልቦናዊ ጥቃት እንዲቆም የሚመለከታቸው የሰብዓዊ መብቶች እና ዲፕሎማቲክ አካላት ሁሉ በጎ ተፅዕኖ እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን።

5) የአማራ ክልልን የጦርነት መልሶ ግንባታ እቅድ ይፋ ሆኖ በተግባር እንዲጀመር እንጠይቃለን፤

የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ ጉዳት በደረሰባቸው 7 ዞኖችና በርካታ ከተሞች መልሶ ለማቋቋም ከ522 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ የክልሉ መረጃ ያሳያል። ከ11.4 ሚሊዮን ሕዝብ በጦርነቱ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ጫና ደርሶበታል። ከ2 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ከኦሮሚያ፣ ከአዲስ አበባና ከየተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተፈናቅለው በክልሉ በየድንኳኑ እርዳታ ጠባቂ ሆነው ይገኛሉ። ከዚህ ውስጥ 1.1 ሚሊዮን ሕዝብ ደግሞ አስቸኳይ የእለት ደራሽ እርዳታ ፈላጊ ሆኗል። ይኼ በእኛ ዘመን በወገናችን ላይ የተፈፀመ አስከፊ የሰብዓዊ ቀውስ ነው። ሆኖም የፌደራሉ መንግስት እና ሌሎች የተዛባ ጥሎ ማለፍ ፖለቲካ አራማጆች ግን መልሶ ግንባታ ሳይሆን ተጨማሪ ጦርነት እና ተጨማሪ መፈናቀልን በአማራ ሕዝብ ላይ አዘውበታል።

ስለሆነም የፌዴራል መንግስት እና የአማራ ክልል መንግስት በክልሉ የደረሰውን የጦርነት ውድመት መልሶ ግንባታ እና ተፈናቃዮችን በዘላቂነት መቋቋም ዙሪያ ግልፅ መርሃ ግብር፣ የኃብት ምንጭ እና ትግበራ እቅድ በይፋ በማውጣት ወደ ተግባር እንዲገቡ እንጠይቃለን።

በመጨረሻም የአማራ ሕዝብ የተጋረጠበትን ሁሉንአቀፍ መንግስት መር የኅልውና አደጋ ለመቀልበስ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድ ሆኖ እንዲቆም እያሳሰብን እኛ በክልሉ ም/ቤት የምንገኝ የአብን ተወካዮችም ለሕዝባችን ሁሉንአቀፍ ደኅንነት ከፊት የምንሰለፍ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን።

በአማራ ክልል ምክር ቤት የአብን የሕዝብ ተወካዮች
ግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም
ባሕር ዳር ፥ አማራ ፥ ኢትዮጵያ!

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *