Addis Ababa at night
Current

የኦሮምያ ክልል ቤተ መንግሥት በአዲስ አበባ ሕገ ወጥ ነው።

Thursday, May 25, 2023

በትላንትናው ዕለት አሻም የተባለ ሚድያ ላይ የኦሮምያ ክልል መስተዳድር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ቀርበው፤ የቤተ መንግሥቱ ግንባታ ሕጋዊ ነው ምክንያቱም “ፊንፊኔ” የክልሉ ርዕሰ ከተማ ነው፤ ላለፉት ሰላሳ አመታትም የክልሉ መናገሻ ሆና አገልግላለች ሲሉ ተደመጡ። ልክ እንድ ሕወሃት መራሹ መንግሥት የኦሮምያ ክልል ባለሥልጣናትም የሚመሩበትን እና እራሳቸው የፃፉትን ሕግ እንኳን ያልተገነዘቡ መሆናቸው አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን፤ ከታሪክ ያለመማር በሽታም ነው።

የኦሮምያ ክለላዊ ቤተመንግስት በአዲስ አበባ መገንባት፤ ለከተማው ገቢ የሚያስገኝና የሥራ እድል የሚፈጥር ቢሆንም፤ ከሕግ፤ ከፖለቲካ እይታ እንዲሁም ከአስተዳደራዊ ኩነቶች አንፃር እጅግ የተሳሳተና አደገኛ የክልሎች ፉክክር ጅማሮ ሊሆን ይችላል። ይህ ቤተመንግስት ግንባታ የኢትዮጵያን ፌደራላዊ መንግስት ሕገ መንግሥት የጣሰ ብቻ ሳይሆን፤ የኦሮምያ ክልል መስተዳድርን ሕገ መንግሥት የጣሰም ጭምር ነው።

የፌደራሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 49 እንዲህ ይላል፡

1. የፌዴራሉ መንግሥት ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ ነው፡፡
2. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ይኖረዋል። ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡
3. የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጠሪነቱ ለፌዴራል መንግሥት ይሆናል፡፡

4.የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በዚህ ሕገ መንግሥት በተደነገገው መሠረት በፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይወከላሉ፡፡

5.የኦሮሚያ ክልል፤ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ፣ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳሰሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል፣ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል።”

ቁጥር 5ን በአጽንኦት ላስተዋለው፤ “አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳሰሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል” ይላል። አዲስ አበባ በኦሮምያ ክልል መሃል የሚገኝ እንጂ የኦሮምያ ክልል አካል አይደለችም።

የ1987 ዓም ኦሮምያ ክልል መሥተዳድር ሕገ መንግስት አንቀጽ 7 “የኦሮምያ ክልል ርእሰ ከተማ ፊንፊኔ ነው” ቢልም፤ ይህ ሕጋዊ አልነበረም ምክንያቱም ከፌደራሉ ሕገ መንግሥት ጋር ይፃረራል። ይህ አንቀጽ ግን፤ በ1994ቱ በተሻሻለው የክልሉ ሕገ መንግስት “የኦሮምያ ክልል ርእሰ ከተማ አዳማ ነው” ሲል ተቀይሯል።

ከዚህ በተጨማሪ የክልሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39 ቁጥር 3 የኦሮሞ ሕዝብ “እራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት አለው፤ በራሱ መልክአ ምድር ራሱን የሚያስተዳድርበት መንግስታዊ ተቋማትን የማቋቋምና በፌደራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብት አለው” ይላል። ይህ ማለት፤ የኦሮምያ ክልል መስተዳድር፤ ተቋማቱን ሊገነባ የሚችለው በክልሉ መልክአ ምድር ውስጥ ብቻ ነው።

አዲስ አበባ የክልሉ አካል ባለመሆኗ አዲስ አበባ ውስጥ የክልሉን ቤተ መንግስት መገንባት ሕገ ወጥነት ነው።

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግሥት ሕገ መንግሥት በግልጽ እንድሚያሳየው የሃገሪቱ የበላይ ሕግ የፌደራሉ ሕገ መንግሥት መሆኑን ብቻ ሳይሆን፤ የኦሮምያ ክልል ሕገ መንግስትም ሆነ የፌደራሉ ሕገ መንግሥት በግልጽ እንደሚያስቀምጡት፤ የየትኛውም ክልል ሕገ መንግሥት ከፌደራሉ ሕገ መንግሥት ጋር ሊፃረረ አይችልም።

ስለዚህም ከሕግ አኳያ፤ የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት በአዲስ አበባ ቤተ መንግስት የመገንባት ምንም ሕጋዊ መሰረት የለውም። ሌላው ቀርቶ፤ የክልሉ የፖሊስ መምርያም ሆነ ሌሎች የኦሮምያ ክልላዊ መስተዳደር ተቋማት ከአዲስ አበባ መነሳት አለባቸው። ይህም እንዲሆን መብቱን ማስከበር ያለበት የአዲስ አበባ ሕዝብ ነው።

በግልጽ እንደምናየው፤ የአዲስ አበባ መስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቢቤ በተደጋጋሚ ያሳዩን የአዲስ አበባን ጥቅም ለማስከበር ከመጣር ይልቅ፤ የኦሮምያ ክልልን አጀንዳ የሚያራምዱ መሆናቸውን ነው። የአዲስ አበባ ምክር ቤት፤ የፌደራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሆነ የጠቅላይ ምኒስትሩ ቢሮ ይህን ሕገ ወጥ ድርጊት እንዳላይ በማለፍ፤ በፖለቲካም የሚያስከፍለውን ዋጋና የሚፈጥረውን ውዝግብም ሆነ የሕዝብ ቅሬታ ከቁብ ባለመቁጠር እዎንታዊ የሰጡት የቤተ መንግሥት ግንባታ በከተማው ሕዝብ በዝምታ ሊታለፍ አይገባውም።

የተቃዋሚ ድርጅቶችም ሆኑ በዚህ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ሰዎች ተቀምጠው አቤቱታ ከማቅረብ ባለፈ፤ የፍርድ ቤት ተቋማትን በመጠቀም መብታቸውን ማስከበርና የፍርድ ቢቶችን ገለልተኝነትንም ሊፈትሹ ይገባል። ስለዚህ፤ በአዲስ አባበ መሰረት የተጣለለትን የኦሮምያ ክልል ቤተ መንግስት ግንባታ ለማስቆምና ሌሎች የክልሉ ተቋማት ወደ ኦሮምያ ክልል እንዲዛወሩ ሕጋዊ እርምጃ ይወስዱ ዘንድ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች የበኩሌን ጥሪ አቀርባለሁ። የምንፈልገውና የምንመኘው በሰዎች ሳይሆን በሕግ የሚተዳደር አገር ነው።

Source: tibebe samuel ferenji facebook page

አዲሱ የሀገራችን ሁኔታ አዲስ ራእይና አዳዲስ ግንኙነት ይጠይቃል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *