Analysis

የአማራ እና ትግራይ ጉዳይ ወዴት እያመራ ነው?

ቹቹ አለባቸው

Cheru Alebachew ·

 

በአማራ እና በትግራይ ክልሎች መካከል፣ የወሰንና ማንነት ጥያቄዎችን መነሻ አድርጎ የከረመውን ችግር ለመፍታት ጥረቶች እየተደረጉ እንደሆነ ይነገራል። በዚህም መሰረት ቢያንስ 2/3 ግዜ ውይይቶች ተካሂደዋል።

አሁን ጥያቄው ከሕወሓት ያልበረደ የእብደት ፍላጎት አንፃር ሰላም የመጽናት ዕድሉ ምን ያህል ነው የሚለው ጥያቄ ተስፋው ከሞላ ጎደል የተሟጠጠ ሆኖ ይታያል። ከዚህ ተነስተን ከወሰንና ማንነት አንፃር እውነተኛ ስምምነት ላይ መድረስ ይቻላል ወይ ለሚለው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ያለው አይመስልም። በተለይም ከህወሓት ባህሪ አንፃር።

በእኔ እምነት የፌዴራሉ መንግሥት የአማራና ትግራይ ክልሎች ውዝግብ ቢያንስ ከወሰንና ማንነት ጋር የተያያዘው በውይይት ይፈታል ብሎ ጊዜ ባያጠፋ መልካም ነው። ምክንያቱም በዚህ አጀንዳ ዙርያ የሕወሓት ፍላጎት ዛሬም ጉልበትን፣ ሴራንና መሰል ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረገ አደገኛ ስልት የሚከተል በመሆኑ ነው። ‘ከዚህም በላይ ጉዳዩ በሁለቱም በኩል በሰጥቶ-መቀበል መርህ የሚፈታ ነው’ ብሎ ጊዜ ማጥፋት የዋህነት ነው። ይህ የማይሆን መሆኑ ታውቆ በፍጥነት ወደ ሕጋዊ ሥርዓቱ ቢገባ ጥሩ ነው።

ይልቁንስ አንድ ስጋት አለኝ። ይሄንን አጀንዳ በአጭር ጊዜ በሕጋዊ መንገድ አለመቋጨት ሁለቱ ክልሎች ወደ ዳግም ጦርነት እንዲገቡ ዕድል መስጠት ነው የሚሆነው። አሁን ላይ በተለይም በህወሓት መንደር ወታደራዊ ዝግጅትና እንቅስቃሴ በግልፅ መታየት ጀምሯል።

ይሄም ሆኖ የተጀመሩ ውይይቶች መቀጠላቸውን እደግፋለሁ። ውይይቶቹ ከወሰንና ማንነት ጋር በተያያዘ መፍትሄ ያመጣሉ ብየ ባላምንም፣ ምን አልባት በጠላትነት የመተያየት ስሜቶችን ሊያረግቡ ይችላሉ። በሂደትም የህዝብ-ለህዝብ ግንኙነቱን በር ሊከፍት ይችላል። ይሄም ሆኖ ዕድሉ ጠባብ መሆኑ አይቀሬ ነው። ቢሆንም መሞከሩ አይከፋም።

በአጭሩ በትግራይና አማራ መካከል ለተፈጠረው ችግር መንስኤዎቹ ሁለት መሆናቸውን አውቆ ለነዚህ ችግሮች እንደ አግባቡ መፍትሄ ማበጀት ይገባል:–

1ኛ) መነሻውን የደደቢት ትርክት ያደረገው አማራን በጠላትነት የሚመለከተው ሐሳዊ ትርክት፣

2ኛ) የሕወሓት የግዛት ተስፋፊነት የወለዳቸው በአማራ ዘንድ የሚነሱ የወሰንና ማንነት ጥያቄዎች ናቸዉ።

እነዚህን መሠረታዊ ችግሮች ለማረም ብሎም በዘላቂነት ሠላምና አብሮነትን ለማጽናት የሕወሓት ያልተገባ ባህሪያትን ማረቅ የግድ ይላል።

ለአማራ ክልል መንግሥት ያለኝ መልዕክት የሚከተለው ነው:-

የአማራ ሕዝብ የተረጋጋ ሰላም ኖሮት ወደልማት ይገባ ዘንድ፤ የወሰንና ማንነት ጥያቄዎች ሕጋዊና ዘላቂ እልባት እንዲያገኙ ማድረግ የቅድምያ ቅድምያ ትኩረት ቢሆን ጥሩ ነው።

ይኼ ጉዳይ በአጭር ጊዜ የማይጨበጥ ከሆነ ደግሞ፣ የክልሉ መንግሥት የአማራ ሕዝብ በማንኛውም ወቅት ከህወሓት የሚሰነዘርን ጥቃት ቢኖር ለመመከት የሚያስችል የተሟላ ቁመና ላይ መገኘቱን ለሚመራው ሕዝብ ማረጋገጥ መቻል አለበት።

እንደዚህ አይነት መፍትሔ ወይም ዋስትና ባልተገኘበት ሁኔታ፣ በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል የተረጋጋ ሰላምና ልማት ማረጋገጥ እጅግ አስቸጋሪ መሆኑ አይቀርም። አሁን ምድር ላይ ያለው እውነታ የሚነግረን ነገር ይሄንኑ ሀቅ ነው።

በአማራ ክልል ከወሰንና ማንነት ጋር ያለውን ችግር፣ አንድም በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ መቋጨት፤ ሁለትም አሰተማማኝ የፀጥታ ሀይል መገንባቱን ማረጋገጥ፤ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ላይ የሚታየውን የፀጥታ ስጋት በአያሌው ይቀንሰዋል። ከነዚህ ሁለት ቅድመ ሁኔታዎች አንዱም ሳይሟላ፣ ስለ አማራ ክልል ሰላምና መረጋጋት ማሰብ አሰቸጋሪ መሆኑ አይቀርም። ሰላሙ ያልተጠበቀ ክልል ደግሞ በልማት ወደፊት ለመግፋት ቀርቶ ያለውን ማስጠበቅ እንኳን መቸገሩ አይቀሬ ነው።

በዚህ አጀንዳ ዙርያ ከሰሞኑ በነበረኝ የቅርብ ክትትል ነገሮች እንዳይበላሹ ስጋት አድሮብኛል። ሕወሓት አጀንዳውን አሳድጎ የወሰንና ማንነት ጥያቄ የተነሳባቸውንና በሕዝባችን ትርጉም በሚሰጥ መስዋዕትነት በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ስር የሚገኙትን አካባቢዎች “ተፈናቃዮችን” ከመመለሴ በፊት የፀጥታና አሰተዳደር አካላት መመለስ አለባቸው ወደሚል ደረጃ መጥቷል።

ትግራይ ውስጥ በአማራ ላይ ያለው ጥላቻ፤ በፖለቲካ ኢሊቱ ብቻ የተገደበ ሳይሆን፣ በኃይማኖት ተቋማት አባቶች ጭምር ስለመሆኑ ከመቸውም ጊዜ በላይ ግልፅ ሆኗል።

ስለዚህ የክልሉ መንግሥት የትኩረት መስኮችን ለይቶ ‘በጊዜ የለም መንፈስ’ ቢንቀሳቀስ ይመከራል። በተለይም ለውስጥ አንድነት፣ ለአመራር የሀሳብና ተግባር አንድነት ልዩ ትኩረት መስጠት ይገባል።

በልዩ ሁኔታ ሊታይ የሚገባው ከፋኖ ጋር በተያያዘ የተከሰተውን ችግር በሆደ ሰፊነትና በውይይት መፍታት የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሰጥ የሚገባው ጉዳይ ነው። ራሳችን በራሳችን የመብላት አዙሪት ሊቆም ይገባል።

የተግባራዊነቱ ጉዳይ ጥያቄ የሚያጭር ሆኖ፣ ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ እንዳሉት መከላከያ ከፋኖ ጋር የሚዋጋበት አጀንዳም ሆነ ዓላማ የለውም። ይህ ከሆነ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት አዳጋች አይሆንም። በርግጥ እስካሁን ባየነው ግን ተግባራዊ ሲሆን አልታየም። ቢሆንም ያለመታከት ችግሩን በዉይይት ለመፍታት መሞከር የተሻለዉ አማራጭ ነዉ ። ስለሆነም ሁኔታዎች ከዚህ በከፋ መልኩ ሳይቀያየሩ አመራሩ ‘ኳስ በመሬት…’ ቢያደርግ ይመከራል። አማራ ምክንያት ኑሮት የተቆጣ ሕዝብ መሆኑ ግንዛቤ ተወስዶ፣ ሊደመጥ ብሎም ችግሮቹን በውይይት ለመፍታት ቁርጠኛ መሆን ያስፈልጋል ።

ከዚህም በተጨማሪ አርሶ አደሩ እያነሳ ያለው የማዳበርያ ጥያቄ እንዲሁ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። አጀንዳው የህልውና ጉዳይ እንጂ “የጅራፍ ፖለቲካ” አይደለም። ያውም ሰፊ የሆነ የምግብ ዋስትና ችግር ባለበት አገር የምርት ማሽቆልቆልን የሚያመጣ ጉዳይ አቃልሎ ማየት ፍረጃ መስጠቱ suicide mission እንጂ ለአገርም ሆነ ለወገን በጎ መፍትሔ አይሆንም።

ስለሆነም ከተቻለ አቅርቦቱን ማሳለጥ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በየጥጋ ጥጉ የሚሽከረከረውን የማዳበሪያ ኮንትሮባንድ ተገቢና አስተማሪነት ያለው ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ይገባል። እነዚህን እርምጃዎች እየወሰዱ ችግሩን ለማስተካከል መጣር ብሎም እንደ አገር ያለንበትን ሁኔታ አርሶ አደሩን በተገቢው በማስረዳት ሌሎች የግብርና አማራጮችን ማፍለቅ ይገባል። በተረፈ፣ ይኼ አጀንዳ በወቅቱና በተገቢው ካልተስተናገደ ውጤቱ ከባድ ይሆናል።

ለሁሉም የወሰንና ማንነት ውዝግቡን አንድም በሰላማዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ መቋጨት አንድም ደግሞ ማናቸውንም ትንኮሳ ለመመከት ብቁ ሆኖ መገኘት፣ እንዲሁም ከፋኖ ጋር ያለዉን ዉዝግብ በሰላማዊ መንገድ መፍታትና ለአ/አደሩ የአፈር የማዳበርያ ጥያቄ አሳማኝ ምላሽ መስጠት የአማራ ክልል መንግሥት ወቅታዊና አንገብጋቢ አጀንዳዎች ተደርገዉ ቢሰራባቸዉ ምክሬ ነዉ።

ሰላም ለአገራችን ኢትዮጵያ!
ስክነትና መደማመጥ ለአማራ ፖለቲካ!

 

 

Source: Chuchu Alebachew facebook account

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *