Press Release

 አገራችን ኢትዮጵያን ከከፋው የህልውና አደጋ ለመታደግ ለነገ የማይባልና ቁርጠኝነትን የተላበሰ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ያስፈልጋል!! 

 

 አገራችን ኢትዮጵያን ከከፋው የህልውና አደጋ ለመታደግ ለነገ የማይባልና ቁርጠኝነትን የተላበሰ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ያስፈልጋል!! 

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከመኢአድ፣ ኢህአፓ፣ እናት ፓርቲ፣ ዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄ እና አንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ የተሠጠ መግለጫ 

በአገራችን ኢትዮጵያ ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ በተጠና መልኩ እየተተገበረ የሚገኘው የጎሣ ፖለቲካ መራራ ፍሬ አፍርቶ ሕዝቧ የመከራና የሰቆቃ ሕይወት ማሳለፍ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የመከራዉ እና የሰቆቃዉ መጠን ከእለት እለት ከመሻል ይልቅ ይበልጥ ሥር እየሰደደና እየከፋ የሄደ ሲሆን ዓለም በዝምታ እያየ አንድ ሚሊዮን ህዝብ ካለቀበት ከሩዋንዳዉ የዘር ፍጅት በኋላ በአፍሪካ መጠነ ሰፊ የዘር ፍጅትና የዘር ማፅዳት ሥራ እየተካሄደ እንደሚገኝ ነጋሪ አያሻም፡፡ ልክ እንደ ሩዋንዳዉ የዘር ጭፍጨፋ ዓለም ኢትዮጵያ ዉስጥ በተከታታይ ዓመታት እየሆነ ያለዉን ባላየ እያለፈ ይገኛል፡፡

 በዚሁ አገር በጀመረችዉ የጥፋት ጉዞና የዚሁ ውጤት በሆነውና የ፳፩ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የዓለማችን ከፍተኛው ደም አፋሳሽ ጦርነት ከግማሽ ሚሊየን እስከ አንድ ሚሊየን የሚደርሱ ዜጎቻችን ሕይወታቸዉን አጥተዋል፤ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ከቤት ንብረታቸዉ ተፈናቅለዋል ፣ በመንግስት መግለጫ መሠረት በትሪሊየን ብር የሚገመት ሃብትና ንብረት ወድሟል፡፡ በሌላ በኩል ባለፉት አምስት ዓመታት ዜጎች በቄያቸዉ በማንነታቸዉ ተለይተዉ በጅምላ ተጨፍጭፈዋል ፣ ቤታቸዉ ፈርሶ ለስደትና ተረጂነት ተጋልጠዋል። በነዚህ ማንነት ተኮር ጥቃቶች ግንባር ቀደም ሰለባ የሆነው የአማራው ማኅበረሰብ በቅርቡ በወጣ ዘገባ ከ፳፭ ሺህ እስከ ፵ ሺህ የሚደርሱ ዜጎች ለውጥ መጣ በተባለበት ወቅት በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸው ተዘግቧል። ይህ ሁሉ የዛሬይቷ አገራችን ኢትዮጵያ በዜጎቿና በዓለም ማኅበረሰብ ዘንድ የምትታወቅበት ወቅታዊ መገለጫዎች ቢሆንም አገራችን ከቀን ወደ ቀን ወደ ሁለንተናዊ ቀዉስ እያመራች መንግሥት በአንዳንድ አካባቢ ምንም እንዳልተፈጠረ በቸልታ በመመልከት በሌላ አካባቢ ቀዉሱን ራሱ በመፍጠርና በማባባስ ለአገር ወደ ከፋ ቀዉስ መግባት የማይገባውን ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ 

የኑሮ ውድነት ሕዝባችንን እንዴት እንዳጎበጠው በዚህ መግለጫ መናገር ሳያስፈልግ በአገራችን በተተገበረዉ የጎሳ ፌደራላዊ አወቃቀር ከፍተኛዉን የሕዝብ ቁጥር የሚይዙት የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ በሰሰላም እጦት ቀዉስ ዉስጥ የሚገኙበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ከፊል አካባቢ መንግሥት ኦነግ ሸኔ በሚለዉና ራሱን የኦሮሚያ ነጻነት ሠራዊት ብሎ በሚጠራዉ ታጣቂ ኃይል ሥር ወድቆ የኦሮሞ ማኅበረሰብ በአንድ በኩል በመንግሥት በሌላ በኩል በታጣቂ ኃይሎች ቀንበር ሥር ወድቆ ከአራት ዓመታት ለዘለቀ ጊዜ የሰቆቃ ኑሮ እየገፋ የሚገኝ ሲሆን በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ የክልሉ ነዋሪ የአማራ ማኅበረሰብ ዜጎቻችን በማንነታቸዉ ምክንያት ብቻ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉበትና እየተገደሉ ያሉበት ሁኔታ ዉስጥ እንገኛለን፡፡ በዚሁ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ሰሚ ያጣው ደግሞም ለወራት የቀጠለዉ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ አካባቢውን እየናጠ ይገኛል፡፡ 

በሌላ በኩል በአማራ ክልል ኢመደበኛ ኃይል ብሎ መንግሥት ስያሜ በሰጠው ፋኖ ላይ በከፈተዉ ጥቃት የአማራ ክልል ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል መልኩ የግጭት አዉድማ እንዲሆን እየተደረገ ሲሆን መከላከያ ሠራዊት በየቦታዉ “ኢመደበኛ ኃይሎችን” ዒላማ በማድረግ ሽፋን ከሰላማዊ የክልሉ ኗሪዎች ጋር የማያቋርጥ ግጭት ዉስጥ ገብቷል፡፡ በዚህም ብዙ ዜጎች ሕይወታቸው አልፏል በሚደርሱ የደፈጣ ጥቃቶች በየቦታው የመንግሥት ሹማምንትና ባለሥልጣነት መገደል የእለት ተእለት ክስተት ሆኗል። 

የአገራችን ነባራዊ እዉነታ ይህ ሆኖ ሳለ የፌደራል መንግሥቱም ሆነ የሁለቱም ክልሎች መንግሥታት በማያቋርጥ ስብሰባ ተጠምደዉ ነገሮችን ከማመንዥክ በዘለቀ አገር ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ በአግባቡ አምኖ በመቀበል አገርን ካንዣበበባት ሁለንተናዊ የጥፋት አደጋ ለመታደግ የሚደረግ ሙከራ እንደሌለ የኢትዮጵያ ሕዝብም የዓለም ማኅበረሰብም እየተመለከተ ያለ ጉዳይ ነዉ ፡፡ አገር ቁልቁል እየተንደረደረችና ወደ ጥፋት እያመራች ባለችበት በአሁኑ ወቅት ከፍታ ላይ ነች፤ ወደ ብልፅግና ጎዳና እየተጓዘች ነዉ፤ ከብልጽግና መንገዳችን ማንም ወደ ኋላ አይመልሰንም በሚሉ ዲስኩሮች ራስን ማሞኘት ለችግሩ መፍትሄ በመሻት አገርን ከመታደግ ይልቅ የጥፋት ጉዞዉን በማፋጠን ወደማያባራና የተወሳሰበ የግጭት አዙሪት አገርን በማስገባት የችግሩን መፍቻ ያርቀዉ ካልሆነ በስተቀር ችግሩን እንደሌለ አያደርገዉም። በአገራዊ አባባል “ በሽታዉን የደበቀ መድኃኒት አይገኝለትም“ እንደሚባለዉ አገር እየተከተለች ባለችዉ ጎዳና 

የስልጣን ወንበሩን የተቆናጠጠዉ መንግስትም ስልጣኑን ጨብጦ እንደማይዘልቅ አገርም እንደ አገር አንድነቷና ህልዉናዋ ተጠብቆ እንደማትቀጥል ይልቁን ኹለት መቶ አመታት ወደ ኋላ ተመልሳ በጦር አበጋዞች ልትመራ የምትችልበትና የዘመነ መሳፍንት አይነት እጣ ፋንታ ሊያጋጥማት የመቻል እድል እጅግ የሰፋ መሆኑን ቆም ብሎ በሰከነ መንፈስ መረዳት ያሻል፡፡ 

ከዚህ በመነሣት አስቸኳይ የአገር አድን እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ፤ ኢትዮጵያዉያን ችግሮቻችንን ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረ ተወያይተን መፍታት እንደምንችል ፤ ይህን ለማድረግ ጥበቡንም እዉቀቱንም ችሎታውንም እንዳለን በማመን እኛ በትብብር የምንሠራ አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ለወቅታዊ የአገራችን ችግር ብቸኛ መፍትሄዉ ሥልጣን ላይ ባለው መንግሥት፣ ነፍጥ አንስተዉ ዉጊያ ላይ በሚገኙ ኃይሎች እና ሕጋዊ እውቅና ኖሯቸው በሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በእኛው ኢትዮጵያዉያን በባለቤትነት የሚመራ ወዳጅ አገራት በደጋፊነት የሚሳተፉበት አስቸኳይ የአገር አድን ውይይት ማድረግ መሆኑን እናምናለን። ለዚህም ጉዳዩ የሚመለከታቸዉ በሙሉ የአገርን ህልዉና የመታደግ እንቅስቃሴን ቸል ባለማለት በአፋጣኝ ወደ ተግባር ኢንዲገባ የአገሩ ጉዳይ እንደሚገደውና የተደራጀ የፖለቲካ ኃይል የጥሪ ደወል እናሰማለን፤ ለተግባራዊነቱም እኔነትን ወደ ጎን ትተን ሁሉም በጋራ እንዲንቀሳቀስ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ 

አገርን የማዳን ውይይቱ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሁሉም በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች የሚሳተፉበት ሲሆን ስብሰባው ኢትዮጵያዉያን መራሽ ሆኖ በዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ የተሻለ ጎዳና ላይ በሚገኝ የአፍሪካ አገር ርዕሰ ከተማ ቢካሄድ ለተሳታፊዎች የደህንነት ስጋትን ለማስወገድ፤ እንደ አፍሪካዊት አገር ለአፍሪካ ችግር መፍትሄውን እኛው አፍሪካውያን በዚሁ ማፈላለግና ማግኘት እንደምንችል በማሳያነት ልንጠቀምበትና በዴሞክራሲ ሥርዓት መልካም ስም ባላት አገር መከናወኑ በአስተማሪነቱ ጠቀሜታ ሊኖረው እንደሚችል መጥቀስ ተገቢ ይሆናል፡፡ 

ይህ አገርን የመታደግ አስቸኳይ ውይይት መንግስት በአዋጅ ካቋቋመዉ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራ ጋር የማይቀላቀልና ሊምታታ የማይገባው ሲሆን አገር ላይ ላንዣበበዉ የህልዉና አደጋ በተቀናቃኝ ወገኖች መካከል የሚደረግ የኅልውና አደጋን ማስወገጃ የአደጋ ጊዜ መውጫ ሥራ ነው፡፡ በአገር አድን ውይይቱ መንግሥት እንደ አንድ ተወያይ አካል የሚቀርብበት ሲሆን በሌላ በኩል ነፍጥ አንስተው የትጥቅ ትግል እያደረጉ ያሉ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ፣ ታጣቂ የአማራ ኃይሎች እንዲሁም በህጋዊ መልኩ ተመዝግበዉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች የሚሳተፉበት ሲሆን ይህን በማድረግ አገርን ከከፋዉ ጥፋት መታደግ ይሆናል፡፡ 

በዚህ መሠረት 

1. የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን ሃሳብ ተቀብሎ እንደ መንግሥት ተግባራዊ ለማድረግ በአስቸኳይ ቀን ወስኖ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ አንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲጀምር፤ 

2. መንግሥት ለሰላም ያለውን ቁርጠኛ ፍላጎት ለማረጋገጥ ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ በፌዴራል ፖሊስ፣ በአማራና በኦሮምያ ክልሎች እስር ቤት በጅምላ አጉሮ የሚያሰቃያቸውን የኅሊናና የማንነት እስረኞች እንዲፈታ፤ 

3. የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት እንዲሁም የአማራ ታጣቂ ኃይሎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በዚህ አገርን የመታደግ ዓላማ ባነገበ ዉይይት እንዲፈቱ የሚፈልጉዋቸዉን ጥያቄዎቻቸዉን በመለየት የዉይይቱ ተሳታፊዎቻቸዉን ዝግጁ እንዲያደርጉ፤ 

4. የአገር ጉዳይ ግድ የሚላቸው የፓለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ማኅበራት አገር ከገባችበት ቀዉስ እንድትወጣ አስፈላጊዉን ዝግጅት በማድረግ የመፍትሄ አካል በመሆን አገርን ከጥፋት የሚታደግ ሃሳብ በማመንጨትና በማቅረብ ታሪካዊ ኃላፊነት እንዲወጡ፤ 

5. የአፍሪካ ህብረት ኢትዮጵያ መስራች አባል እንደሆነችበትና መቀመጫዉን እንዳደረገባት አገር በአገራችን እያንዣበበ ያለው አደጋ በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና፣ በምሥራቅ አፍሪካና በአጠቃላይ አህጉሩ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን እጅግ አደገኛ የሆነ ተጽዕኖ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ዉይይቱ በአህጉራዊው ተቋም የቅርብ እይታ በእህት የአፍሪካ አገር መዲና ሊከናወን የሚችልበትን ሁኔታ እንዲያመቻች፤ 

6. የወዳጅ አገራት መንግሥታት አትዮጵያ ካላት ጂኦፖለቲካዊ ጠቀሜታ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ሊከሰት የሚችል የህልውና አደጋ በአካባቢ አገራትና በአፍሪካ ቀንድ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ በአግባቡ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ይህን ኢትዮጵያውያን የአገራችንን ህልውና ለመታደግ የምናደርገውን ጥረት አስፈላጊ የሆነዉን የፋይናንስ እና የቴክኒክ ድጋፍና እገዛ በማድረግ እንዲደግፉ፤ 

7. የእምነት ተቋማት የታለመዉ ዓላማ ተሳክቶ አገር ከጥፋትና ሁለንተናዊ ቀዉስ እንድትድን በጸሎት ተግታችሁ እንድታስቡ፤ 

8. በመጨረሻም ከሁሉ በላይ የችግሩና የመከራው ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ ሆነህ ለግማሽ ምዕተ ዓመት የኖርከውና ዛሬም የመከራ ቀንበር ተሸክመህ በሥጋት የዕለት ተለት ኑሮህን እንድትመራ የተገደድከው የኢትዮጵያ ሕዝብ የመከራ ዘመንህ 

እንዲያበቃ በምትችለው መንገድ ኹሉ አገርህን ከጥፋት ጎዳናና ከመፍረስ ለመታደግ ተግተህ እንድትሠራ፤ በአገርህ ላይ ያንዣበበው የህልውና አደጋ ተወግዶ በሰላም ወጠተህ መግባት እንድትችል በምናደርገው ጥረት ከጎናችን እንድትቆም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡ 

ከላይ የተጠቀሰዉ አገርን የማዳን ፈጣን ተግባር በዋነኛነት መንግሥት ሊተገብረዉ እንደሚገባ በማምን በአስቸኳይ ወደ ተግባር እንዲተረጉመዉና አገራችንን ከሁለንተናዊ ቀዉስና ጥፋት እንዲታደግ ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡ መንግሥት ይህን ማድረግ ካልቻለ ወይንም ፈቃደኛ ካልሆነ ትናንት የነበሩ መሪዎች ዛሬ እንደሌሉ ሁሉ ዛሬ የሥልጣን ወንበር የተቆናጠጡ መሪዎችም ለዘላለም እንደማይዘልቁና አገርና ሕዝብ የሁሉም መሠረትና ምንጭ መሆናቸውን በጽኑ በማመን የሥልጣን ወንበር ባንይዝም የአገር አንድነትን የማጽናት ኃላፊነት ያለብን መሆኑን በማመን ለዚህ ሁሉን አቀፍ አገርን ከህልውና አደጋ የመታደግ ዉይይት መሳካት አቅማችን በፈቀደ ወደፊት እንደምንራመድና እዉን እንዲሆን በቁርጠኝነት እንደምንሠራ እናሳስባለን፡፡ 

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ! 

አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ 

ሐምሌ ፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. 

መኢአድ ኢህአፓ እናት ፓርቲ የዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄ አንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *