Gedu Andargachew
News

የቀድሞው የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ምን አሉ?

የምስሉ መግለጫ,አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ
የፎቶው ባለመብት,SCREEN GRAB

በአማራ ክልል በአሁኑ ወቅት ለተከሰተው ችግር መሠረታዊው ምክንያት የገዢው የብልጽግና መንግሥት የፖለቲካዊ አመራር ውድቀት ነው ሲሉ የቀድሞው የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር እና የፌደራል ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተናገሩ።

በአማራ ክልል የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማጽደቅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ባደረገበት ጊዜ ነው አቶ ገዱ ይህንን የተናገሩት።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የነበሩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ቢሆኑም እምብዛም በምክር ቤቱ ውስጥ ተሳትፎ ሲያደርጉ አይታዩም ነበር።

በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ለወራት ሲካሄድ የነበረው ተቃውሞ እና ግጭት ተባብሶ ከክልሉ መንግሥት አቅም በላይ በመሆኑ የፌደራል መንግሥቱ ሕግ እንዲያስከብር በቀረበለት ጥያቄ መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በክልሉ ላይ ታውጆ የመከላከያ ሠራዊት እንዲሰማራ ተደርጓል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በእረፍት ላይ እያለ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያጸድቁ የምክር ቤቱ አባላት አስቸኳይ ስብሰባ ነሐሴ 08/2015 ዓ.ም. ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ ውሳኔ ተሰጥቷል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ወደ ሥልጣን እንዲመጣ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል ተብለው ከሚጠቀሱት ፖለቲከኞች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ገዱ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪነት ከተነሱ በኋላ በክልልም ሆነ በፌደራል መንግሥቱ የኃላፊነት ቦታ ላይ አልታዩም።

በተጨማሪም ከመገናኛ ብዙኃን ርቀው በምክር ቤቱ ውስጥም ያላቸው ተሳትፎ ውስን እንደነበር እራሳቸውም በሰኞው ዕለት አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።

አቶ ገዱ በአማራ ክልል ውስጥ የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በተመለከተ በመንግሥት ተጠሪ በኩል ማብራሪያ ከተሰጠ በኋላ ከሌሎች የምክር ቤቱ አባላት ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ ገዢውን የብልጽግና ፓርቲን እና የፌደራል መንግሥቱን አጥብቀው ተችተዋል።

“ካለፉት አምስት ዓመታት ስህተቶቻችን እና ጥፋቶቻቸን መማር አለመቻላችን ይገርመኛል” ያሉት አቶ ገዱ፣ “መንግሥት ራሱ ፖለቲካዊ ችግር ይፈጥራል፤ ችግሩን በፖለቲካዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ በወታደራዊ ኃይል ለመፍታት ይንቀሳቀሳል” ሲሉ ወቅሰዋል።

ከዚህ በፊት በአገሪቱ ውስጥ የተለያዩ ፖለቲካዊ ችግሮች ተፈጥረው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለመፍታት እንደተሞከረ፣ ለዚህም ማስፈጸሚያ በርካታ ኮማንድ ፖስቶች መቋቋማቸውን ጠቅሰው “ነገር ግን አንድም ያቃለሉት ችግር የለም” በማለት መፍትሄው ፖለቲካዊ መሆኑን የትግራይ ጦርነት የተፈታበትን መንገድ በምሳሌነት አንስተዋል።

የአማራ ክልል ሕዝብ በለውጡ ጅማሬ ወቅት የብልጽግና ደጋፊ እንደነበር በምክር ቤቱ ውስጥ የተናገሩት አቶ ገዱ፣ ነገር ግን የለውጡ እንቅስቃሴ አቅጣጫውን መሳቱን ሲገነዘብ ሕዝቡ የመንግሥት ስህተቶች እንዲታረሙ አጥብቆ ሲጠይቅ መቆየቱን እና ሰሚ እንዳላገኘም ተናግረዋል።

በገዢው ፓርቲ በኩል ተፈጽመዋል ያሏቸው ስህተቶች ከመታረም ይልቅ ተባብሰው በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ሆኖ በማያውቅ ሁኔታ “የአማራ ሕዝብ በማንንቱ ምክንያት ተከታታይ የጅምላ ጭፍጨፋ ተፈጽሞበታል፣ ከሚኖርበት ቀየው በገፍ ተፈናቅሏል፣ ለጉስቁልና እና ለውርደት ተዳርጓል” በማለት ይህም ቅሬታውን እንዳባባሰው እና አሁን ለተፈጠረው ቀውስ ምክንያት መሆኑን አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል የሚካሄደው “የሕዝብ የተቃውሞ እንቅስቃሴ የተጠራቀመ ግፍ እና በደል የወለደው ቁጣ ነው” ያሉት አቶ ገዱ፣ ችግሩን ለመፍታት መፍትሄው ወታደራዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ ውይይት ነው የሚል ዕምነት እንዳላቸው ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።

አክለውም በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል የተከሰተው ችግር መሠረታዊ ምክንያቱ “የብልጽግና መንግሥት የፖለቲካዊ አመራር ውድቀት ነው” ያሉት አቶ ገዱ፣ “የአማራ ሕዝብ እና የብልጽግና ግንኙነት በማይጠገንበት ሁኔታ ተበጥሷል” ብለዋል።

የአማራ ሕዝብ ሲያቀርበው የቆየውን ጥያቄ የጥቂት ቡድኖች አድርጎ የመመልከት፣ ክብረ ነክ የሆኑ ፍረጃዎችን በማኅበረሰብ ላይ በማሳረፍ፣ የበለጠ ሕዝቡ እንዲቆጣ በማድረግ የበለጠ ጥፋቱን እንደሚያባብሰው አሳስበዋል።

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ወደ 12 ደቂቃ ለሚፈጅ ጊዜ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ እና በአማራ ክልል ስተለተፈጠረው ችግር ባስረዱበት፣ እንዲሁም በመንግሥት እና በገዢው ፓርቲ ላይ የሰላ ትችትን በሰነዘሩበት የምክር ቤት ንግግራቸው ወቅት በተደጋጋሚ በምክትል አፈ ጉባኤዋ እና በምክር ቤት አባላት የሥነ ሥርዓት ጥያቄ ቀርቦባቸዋል።

በክልሉ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት እና ሰላም እና መረጋጋት እንዲመጣ ከተፈለገ ያግዛሉ ያሏቸውን የመፍትሄ ሃሳቦችን አቅርበዋል።

“መንግሥት በራሱ ክፋት እና አቅመ ቢስነት ያጣውን ቅቡልንት በመሳሪያ ኃይል ለማስመለስ መሞከር የጥፋት መንገድ ነው” ያሉት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ በአማራ ክልል የተሰማራው “የመከላከያ ሠራዊት ያለቅድመ ሁኔታ ወደ ካምፑ ይመለስ” ሲሉ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም በክልሉ ውስጥ ገዢው ፓርቲ ተቀባይነቱን ስላጣ “ሁሉንም የአማራ የፖለቲካ ኃይሎች ያካተተ ጊዜያዊ አስተዳደር በአስቸኳይ በማቋቋም” ችግሩን ማቃለል ይቻላል ብለዋል።

በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ሌሎች አባላትም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ የተቃውሞ እና የድጋፍ አስተያየት የሰጡ ሲሆን፣ የመንግሥት ተጠሪ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ እንዲሁም የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ማብራሪያ እና ምላሽ ሰጥተዋል።

ይህንንም ተከትሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኞ ነሐሴ 8/2015 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአማራ ክልል እንዲተገበር ያሳለፈውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በ12 ድምጸ ተአቅቦ በ16 ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል።

ምንጭ፥ ቢቢሲ አማርኛ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *