wolkayit
Press Release

ከወልቃይት-ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ: – የሰማዕታት የትግል አደራ አይታጠፍም!

የሰማዕታት የትግል አደራ አይታጠፍም!
ወልቃይትጠገዴ ትላንትም፣ ዛሬም፣ ነገም አማራ ነው!!

የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ሕግና ሥርዓትን መርዂ አድርጎ በሰላማዊ የትግል መንገድ የወከለውን ሕዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ ለማስመለስ ከፍተኛ ትግል ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

ኮሚቴው ሕግና ሥርዓትን በተከተለበት በሰላማዊ ትግሉ ሂደት የተሰጠው ምላሽ ግድያና አፈና ሆኖ በርካታ አይተኬ አባሎቹንና ወገኖቹን ሕይወት ገብሯል፡፡ እውነትና መርኽ በእጁ የሌለው አፋኙ የትሕነግ አገዛዝ በሰላም የቀረበለትን ጥያቄ በጉልበት ለመቀልበስ ቃታ ስቦብናል፤ ከጅምላ ፍጅት እስከ ጅምላ እስር ድረስ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ተመጋጋቢ ወንጀሎችን ያለአንዳች ምህረት ፈጽሞብናል፡፡

የማንነት ጥያቄችን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ለማቅረብ ጥር 19/ 2008 ዓ.ም ወደአዲስ አበባ በተጓዝንበት ወቅት፣ የማንነት ኮሚቴው አባላት ሱሉልታ ከተማ ላይ በደህንነት መዋቅሩ አፈና ተፈጽሞብን እንደነበር ከፖለቲካ አመራር ለውጡ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በፓርላማ ንግግራቸው ምስክርነታቸውን መስጠታቸው ይታወሳል፡፡

ይህ ምስክርነት የወልቃይት-ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴው በሰላማዊ ትግሉ ሂደት ይደርስበት ለነበረው አፈናና እንግልት ዕውቅና የሚሰጥ ከመሆኑም ባሻገር የማንነት ኮሚቴው ጥያቄው የዋለ ያደረ ስለመሆኑ በመሪ ደረጃ የተረጋገጠ ጉዳይ ስለመሆኑ ያስረግጣል፡፡

ትግላችን እውነተኛና ፍትሐዊ በመሆኑ በርካታ ፈተናዎችን በጽናት ያለፈው የወልቃይት-ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ፣ የአማራ ሕዝባችንንና የማንነት ትግላችን አጋር የሆኑ ፍትሕ ወዳድ ኢትዮጵያዊያንን በመያዝ መከራውን በብርታት፤ ችግሩን በጽናት፤ ሴራውን በትግል አሸንፈን አሁን ላለንበት ወሳኝና ታሪካዊ ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡

ባሳለፍናቸው የሰላማዊ ትግል ጊዜያትም ሆነ ከነጻነት በኋላ ባሉ ወሳኝ የትግል ምዕራፎች ውስጥ የአማራ ሕዝብ ለዘመናት ዋጋ የከፈለበት የማንነትና የወሰን ጥያቄው ከተራራው ጫፍ የፍትሕ ትግሉ የአሸናፊነት ሰንደቅ እንዳይቆም እጅግ አድካሚ፣ ውስብስብና ተቋማዊ እንቅፋቶች ገጥመውናል እየገጠሙንም ይገኛል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የሆነው፡- የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ዶ/ር አብርሃም በላይ በ16/12/2015 የትግራይ የአሸንዳ በዓል መሠረት አድርገው በማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው ያስተላለፉት ኃላፊነት የጎደለው መልዕክት፣ የኢትዮጵያ መንግሥትና መላ የአማራ ሕዝብ ወደፍጹም ግጭትና ወደእውነተኛ ፍች እንዲገቡ የሚያደርግ አደገኛ ጠብ-አጫሪነት ነው፡፡ ግለሰቡ የፌዴራል ሥልጣን ላይ ሆነው ከምንም በላይ የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች ውሕድ ማንነት ምልክት የሆነን ተቋም እየመሩ ለጠባብ ዘረኛ ፍላጎታቸው ተገዥ ስለመሆናቸው ራሳቸውን አጋልጠዋል፡፡

ከባዱ የጨለማ ጊዜ ሲያልፍ ‹ገብስ› ክረምቱን ባሳለፈው ‹ጎመን› ላይ ሲመጻደቅ ክሱት ሆኖ በገሃድ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰማይ ስር እያስተዋልን ነው፡፡ ይህ በቀቢጸ ተስፋ የተሞላ ጠብአጫሪ ንግግር፣ የመታመን ዕዳ ፈተና የሆነባቸው በየተቋማቱ የሰርጎ ገብ ሚና የሚጫወቱ የሰላም ፀሮች እዚህም እዚያም ለመኖራቸው ጉልህ ማሳያ ነው፡፡

ባለሥልጣኑ ኃይማኖታዊ መሠረት ያለው ባህላዊ ክብረ-በዓል በሚከበርበት ወቅት ውስብስብ ፖለቲካዊ አጀንዳ የሆነን ጉዳይ በማንሳት ያስተላለፉት መልዕክት፣ ግለሰቡ አንድም ወንበራቸውን የጠባብ ዘረኝነት ፍላጎት ማስፈጸሚያ እያደርጉት ነው፤ አንድም ደግሞ እጅግ አደገኛ ጠብአጫሪ በሆነ ሁኔታ ኢትዮጵያን የማፍረስ አደገኛ ተልዕኮ ይዘው እየሰሩ ስለመሆኑ ያስጠረጥራል፡፡ መሰል አጀንዳዎችን በየጊዜው በመልቀቅ ከመሠረታዊው የአማራ ሕዝብ የትግል አጀንዳ መስመር ማስወጣት እንደማይቻል እያስረገጥን፣ ያለተገቢ እርማት ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ ከእስካሁኑ በከፋ መልኩ ወደለየለት ደምአፋሳሽ ግጭት እንዳያመራ ስጋታችንን እንገልጻለን፡፡

በሌላ በኩል ገዥው ፓርቲ፣ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያን ሁኔታ በተመለከተ ባደረገው ድርጅታዊ ግምገማ፡- የኢትዮጵያን ህልውና በተደጋጋሚ ለአደጋ የሚያጋልጠው ዋናው መሠረታዊ ቀውስ ሕዝቡ በመሠረታዊነት የሚያነሳቸውን የፍትሕ ጥያቄዎች አለመመለሳቸውና ፍላጎቶቹ ሳይመለሱ መቅረታቸው እንደሆነ መግለጹን ዋቢ አድርገን በወቅታዊ አገራዊ በተለይም በአማራ ክልል ባለው ወቅታዊ ሁኔታ አቋማችንን እንገልጻለን፡፡

አጠቃላይ የሀገራችንን ሕዝብ ለግጭትና ተከትሎ ለሚመጣው ነውጥ የሚዳርገው መሪዎቹ በሀገሪቱ የፖለቲካ ምኀዳር የሚነሡ ጥያቄዎችን መመለስ ተስኗቸው፤ ከፈታኙ ጥያቄ ለመሸሽ የሚከፍቱት የአፈናና የሰምቶ አልሰማሁምን መንገድ በመምረጥ የቤት ሥራን የማሳደር አባዜ ነው፡፡ ይልቁንም ጥያቄ ጥያቄን እየወለደ፣ የሕዝብ ፍላጎት አለመሟላት ብሶትን እያመረቀዘ፣ ቀስ በቀስ ህልውናን ወደሚፈታተንና ወደ እርስ በርስ መጠፋፋት ጎዳና ሲመራን ብዙ ጊዜ ተስተውሏል፡፡ አሁን ያለንበት ሀገራዊ ቀውስ የዚህ ድምር ውጤት እንደሆነ የወልቃይት-ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ያምናል፡፡

የኢትዮጵያን ሀገረ-መንግሥት ህልውና አደጋ ላይ ሲጥሉ ያስተዋልናቸውና ሀገራችንን መውጫ በሌለው የግጭት አዙሪት ውስጥ እየደጋገሙ ሲደፍቁ የምናገኛቸው የሕዝብ ቁጣዎችና አመፆች መነሻና መድረሻቸው የሕዝብን ፍላጎቶችና ጥያቄዎች በአግባቡና በወቅቱ ባለመመለሳቸው ነው። በተለይም አካላዊና ሰብዓዊ መብቶቹንና ማንነቶቹን የማስከበር ጥያቄ፣ ነጻነትንና ፍትህን የመሻት ፍላጎቶች ባለመሟላታቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ በመንታ መንገድ ላይ በቆመችበት በዚህ ወቅት በአማራ ክልል ላይ የተፈጠረው ግጭት የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች በተለይም የወሰንና ማንነት ጥያቄዎቹ ባለመመለሳቸው ይልቁንም ደሙን እያዘራ ከወንድም ሕዝቦች ጋር ኢትዮጵያን የፈጠረው ታላቁ የአማራ ሕዝብ የህልውና አደጋ ውስጥ በመግባቱ ነው፡፡

የወልቃይት-ጠገዴ ጠለምት፣ ራያና አበርገሌ የማንነትና የወሰን ጥያቄዎች ታሪክን፣ ፖለቲካንና ነባራዊውን ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ መልኩ በሕግ አግባብ ለባለቤቶቹ እንዲጸና አለመደረጉ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ሊኖር የሚገባውን መተማመን ሸርሽሮ፣ ጤናማ ግንኙነት እንዳይኖር ይልቁንም የአገረ-መንግሥቱ ጠላቶች በሚፈልጉት መንገድ ግጭት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ የውስጥና የውጭ ጠላቶች የደስታ ምንጭ ለገዛ ሕዝቧና ለወዳጆቿ ደግሞ አሳዛኝ፣ የታሪክ ጠባሳ የሚያሳርፍ ታሪካዊ ስህተት በመሆኑ በፍጥነት ሊታረም ይገባል፡፡

አሁንም ቢሆን ወንድም በወንድሙ፤ ወገን በወገኑ ላይ በመተኮስ የሚወሳሰብ እንጂ የሚፈታ ችግር የለም፡፡ በመንግሥት በተለይም በፌዴራል መንግሥት በኩል መሠረታዊዎቹን የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በአግባቡ ከመመለስ ውጭ የኃይል አማራጭ መከተል አደጋው የከፋ ነው፡፡ ከግጭት አዙሪት መውጣት የሚቻለው መሠረታዊውን የሕዝብ ጥያቄ በሰከነ መንገድ፣ ከልብ በመመለስ ብቻና ብቻ ነው፡፡

ስለሆነም፡-

  1. የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄ ፍትሐዊ እና ሕጋዊ መሆኑን በመጣንባቸው የትግል ምዕራፎች አስመስክረናል፡፡ ለዚህ እልፎችን በሰማዕትነት ለገበርንበት፣ የአማራ ሕዝብ የትግል አስኳል ሆኖ ለቀጠለው የወሰንና ማንነት ጥያቄችን በዘላቂነት መመለስ እስከመጨረሻው ፀንተን እንቆማለን!!
  2. ምንጊዜም ቢሆን ትግላችን ሕዝባዊ እንጅ በመዋቅር ላይ የሚንጠለጠል አይደለም፡፡ መዋቅር የሚያስፈልገው የሕዝብን የትግል ዓላማ በተሰናሰለ መልኩ ለማስፈጸም ነው፡፡ አሁንም ቢሆን መዋቅር በማፈረስ የሚጣል የማንነት ትግል አጀንዳ የለንም! ለአማራዊ ማንነታችን በዘላቂነት መከበር እንደቀደመው ጊዜ ሁሉ ሕዝባችን ኃይላችን፤ ጉልበታችን ሕዝባዊነታችን ሆኖ ይቀጥላል፡፡ በመሆኑም ትግላችን ሕዝባዊ ሆኖ እንደሚዘልቅ እናረጋግጣለን!!
  3. የወልቃይት-ጠገዴ ሕዝብ አማራ ነን አለ እንጂ አማራ እንሁን አላለም፡፡ ወልቃይት የአማራ ማንነት የዘር ግንድ መነሻ ነው፡፡ አማራነታችን በተፈጥሮ ያገኘነው ህያው ማንነታችን እንጂ በምርጫ ኮሮጆ ውስጥ የምናገኘው ፖለቲካዊ ስም አይደለም፡፡ ስለሆነም አማራዊ ማንነታችን ለጨረታ አይቀርብም!!
  4. የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ሕዝብ ለሦስት አስርት ዓመታት የሚሻገረውን የትህነግን ሁለንተናዊ ጭቆና ተቋቁሞ ባከናወነው መራር ትግል፤ ይዞት በዘለቀው የማንነት ትግል ጽናት አሁን ያለበት የነፃነት ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡ የግፍ ብዛት፣ የመከራ ቀንበር አማራዊ ባህሉንና ማንነቱን ሊያስጥሉት አልቻሉም። የወልቃይት-ጠገዴ ሕዝብን በቋንቋ፣ በባህልና በሥነ-ልቦና ከበጌምድር ጎንደር አማራዊ ማንነት ለመነጠል የተሞከረው መዋቅራዊ ጭቆና ግቡን ሊመታ አልቻለም፡፡ በዘመናት መፈራረቅ ወልቃይት- ጠገዴ ቋንቋው አማርኛ፤ ባህልና ትውፊቱ ከመላው አማራ ጋር አንድ ቤተሰብ ሆኖ በትግሉ እዚህ ደርሷል፡፡ ቀሪ ያልቋጨናቸው የቤት ስራዎች ቢኖሩብንም የጨለማው ዘመን አልፏል፡፡ ዕጣ ፈንታችንን ከወገናችን አማራ ጋር ሆነን እንወስናለን፡፡ ማንነት የራስ ምርጫ እንጅ በሌሎች ይሁንታ የሚሰጥ አይደለም፡፡ ይህም ሆኖ የወልቃይት-ጠገዴ አማራዊ ማንነት በሕግ እንዲፀናልን ዛሬም አበክረን እንጠይቃለን!!
  5. የኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት በአንቀጽ ቁጥር 48 የአከላለል ለውጦችን በሚመለከት የፌደሬሽን ምክር ቤት “የሕዝብ አሰፋፈር እና ፍላጎትን መሰረት” በማድረግ እንዲወስን ስልጣን በሚሰጠው አግባብ፣ ይህንኑ ጥያቄም “ከሁለት አመት ባልበለጥ ጊዜ ውስጥ የፌዴሬሽን ምክርቤት የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጥበታል።” በማለት በግልፅ የሚደነግግ ቢሆንም፣ በእኛ በኩል ያቀረብነው ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ ከሰባት ዓመት በላይ ስለቆየ የፌዴሽን ምክር ቤት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ምላሽ እንዲሰጠን አበክረን እንጠይቃለን!!
  6. ወልቃይት-ጠገዴ አማራነት በክብር ሊገለጽ ወይም አማራነት ዕዳ ሊሆን በምርጫ የቀረበበት ምድር ነው፡፡ የትግል ጠረጴዛው ላይ የቀረቡት ሁለት አማራጮች ብቻ ናቸው፡፡ አንደኛው፡- ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ወደ ቀደመ የአማራ ማንነቱ በመመለስ አማራ አንገቱን ቀና አድርጎ እንዲሄድ በማድረግ ህልውናውን በማጽናት ወደ ዕድገት የሚያደርገውን ግስጋሴ ማሳካት፤ ወይንም ሁለተኛው፡- ሕዝባዊ የትግል ውጤታችን የሆነውና እንደአማራ የያዝነውን ዕድል በውስጥ እና በውጭ የአማራ ጠላቶች ሴራ ተጠልፎ በመውደቅ አማራን አገር አልባ ማድረግ የቀረቡልን ብቸኛ አማራጮች ናቸው።

ምርጫችን አንደኛው እንደሚሆን አንጠራጠርም። ታሪክ ትልቅ ነገር ነው፤ ክብር መሠረታዊ ጉዳይ ነው፤ ህልውና መተኪያ የለውም፡፡ ስለሆነም ለታሪካችን፣ ለክብራችንን እና ከሁሉም በላይ ለህልውናችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ ሆነን እንገኛለን፡፡ ስለሆነም ሁሉም አማራ የታገለለትን እና ዋጋ የከፈለለትን የወልቃይት-ጠገዴ የአማራ ማንነት የትግል አጀንዳ፣ በመላው አማራ እና በወንድም የኢትዮጵያ ሕዝቦች አጋርነት ዘላቂ ሕጋዊነቱ እንዲፀና እስከመጨረሻው ድረስ ጸንቶ እንዲታገል ጥሪያችንን እናቀርባለን!!

በመጨረሻም!

በፌዴራል መንግሥት ደረጃ ያሉ መንግሥታዊ አካላት በወልቃይት-ጠገዴ የዘመናት ጥያቄ ላይ የሚሰራ ስህተት ከኢትዮጵያም አልፎ የመጭውን አርባና ሃምሳ ዓመት የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ሊያወሳስብ የሚችል በመሆኑ ከታሪክም፣ ከሕግም፣ ከሞራልም ከፖለቲካም፣… አኳያ ማስተዋል፣ የሕዝባችንን እውነተኛ ጥያቄ ከልብ መመለስ ለቀጠናው ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት እንደሚበጅ እየመከርን፣ በፌዴራል ደረጃ በትልልቅ የኃላፊነት ቦታ ተቀምጠው ነገር ግን ከጠባብ ዘረኛ አስተሳሰብና ፍላጎት ያልወጡ አካላት በሚዲያ በሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች ከጠብ-አጫሪ ንግግሮች፣ አለመተማመንን ከሚያሳድጉ እኩይ መልዕክቶች እንዲታቀቡ ይልቁንም የወልቃይት-ጠገዴን እውነተኛና ፍትሐዊ የአማራ ማንነት ጥያቄ ከልብ በመረዳት ጥያቄው በዘላቂነት እንዲመለስ፣ መልካም ጉርብትና እንዲፈጠር አዎንታዊ ሚናቸውን እንዲወጡ ስንል በሠላም ወዳዱ ሕዝባችን ሥም እንጠይቃለን፡፡

 

ምንግዜም ለአማራዊ ማንነታችን ትርጉም ያለው መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነነ!

ሕጋዊና ፍትሐዊ የማንነት ትግል የትም ቦታ ተሸንፎ አያውቅም!!

ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለትግሉ ሰማዕታት!!

***

ከወልቃይት-ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ
ሁመራ-አማራ-ኢትዮጵያ

ነሐሴ 18/2015 ዓ.ም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *