ሲሚንቶ
News

ብልፅግና በስሚንቶ ንግድ ላይ ያለው ሚና ምን ያህል ይሆን

በአዲስ አበባ ከተማ የሲሚንቶ ንግድ በመንግሥት ሹመኞች እና በሕገወጥ ደላሎች በስፋት በመያዙ ተማረን ከገበያ እየወጣን ነው ሲሉ፤ ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን ያቀረቡ የሲሚንቶ ቸርቻሪዎች ተናግረዋል።

ቸርቻሪዎቹ እንዳሉት ሲሚንቶውን በእጅ አዙር ከፋብሪካ የሚያወጡት ባለሥልጣናት ሲሆኑ፤ እነዚህ አካላት ለአከፋፋዮች አስረክበው፣ አከፋፋዮች ደግሞ ለቸርቻሪዎች ያስተላልፋሉ።

መንግሥት የሲሚንቶ ንግድ ስርዓቱን ለመቆጣጠር ሚያዚያ 2015 ላይ የንግድ ትስስር የሚል አዲስ መመሪያ ማውጣቱን በማውሳትም፤ በዚህም አከፋፋዮች ከፋብሪካ ቀጥታ አውጥተው ለቸርቻሪዎች እንዲያስረክቡ እና ነጋዴዎችም ሲሚንቶ በኩንታል ከ1 ሺሕ 100 ብር በላይ ሲሸጡ ከተገኙ ከፍተኛ ቅጣት እንደሚጣልባቸው መደንገጉን ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ መመሪያው 2 ወር እንኳን ሥራ ላይ ሳይውል የገበያ ትስስር የተባለው አሰራር በጅምር ቀረ የሚሉት ነጋዴዎች፤ ይህንን ክፍተት በመጠቀም ሕገወጥ ደላላዎች ወደ ገበያው በስፋት እንደገቡ ገልጸዋል፡፡

“ስለሆነም ሥራ ላለማቆም ከእነዚሁ ሕገወጥ ደላሎች አንድ ኩንታል ሲሚንቶ እስከ 1 ሺሕ 800 ብር በመረከብ ከስረን መሸጥ ስለሌለብን የተወሰነ ጭማሪ አድርገን ስንሰራ የቆየን ቢሆንም፣ የክፍለ ክተማ የንግድ መምሪያ እና የወረዳ ንግድ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች “መንግሥት ያወጣውን መመሪያ ተላልፋችኋል” በሚል ሱቃችንን ያሽጉብናል ወይም ሲሚንቶውን ይወርሳሉ፡፡” ብለዋል።

ሥሜ እንዳይጠቀስ ያሉ እና አሁን ላይ ከገበያ የወጡ አንድ የሲሚንቶ ቸርቻሪ የክፍለ ከተማ እና የወረዳ አመራሮች “ሥራውን መስራት ከፈለጋችሁ ለእኛ የሚገባውን ክፍያ በመክፈል ከደላላ እንደፈለጋችሁ መቀበል እና መሸጥ ትችላላችሁ፣ ይህ ካልሆነ ግን አትሰሩም፡፡” በማለት ቃል በቃል እንደነገሯቸው ተናግረዋል።

ቸርቻሪው አክለውም፤ በሚሰሩበት ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አደባባይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በየወሩ ከእያንዳንዱ የሲሚንቶ ቸርቻሪ ሱቅ 25 ሺሕ ብር ተሰብስቦ በየደረጃው ላሉ የክፍለ ከተማ እና የወረዳ አመራሮች እንደሚሰጥ ገልጸው፤ ይህም ድርጊት ከመለመዱ የተነሳ ሕጋዊ መስሏል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ብሩን የተወሰነ ቀንሱልን ስንልም “እኛ ብቻ አይደለንም፣ ብሩ ለፖሊስ አዛዦች፣ ለሌሎች ደንብ አስከባሪ አካላት እና በየደረጃው ላሉ ሰዎች ነው የሚከፋፈለው፡፡” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው አውስተዋል፡፡

“ይህንኑ ጉዳይ ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ጀምሮ ለአዲስ አበባ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት እና በየደረጃው ላሉ ለሚመለከታቸው አካላት በተደጋጋሚ ቅሬታችንን ብናቀርብም ምላሽ የሚሰጥ አካል ባለመኖሩ፤ ሱቃችንን ሙሉ ለሙሉ ከዘጋን አራት ወራት አልፎናል፡፡” ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ይህ ችግር በመዲናዋ ጎተራ፣ ሰሚት፣ ጀሞ እና መገናኛን በመሳሰሉ አካባቢዎች በስፋት መኖሩን አዲስ ማለዳ ከቅሬታ አቅራቢዎች መረዳት ችላለች።

አዲስ ማለዳ ነጋዴዎቹ ያቀረቡትን አቤቱታ በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮን የጠየቀች ሲሆን፤ “አቤቱታውን ያቀረቡ ሰዎች በአካል ቢሮ መጥተው ያመልክቱ፡፡” በማለት ተጨማሪ ማብራሪያ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።

ምንጭ፥ ራስ ጋሻው ፌስቡክ ገጽ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *