News

አንጋፋው የአሜሪካ የምክር ቤት አባል የግብጽን መንግሥት ለመደገፍ ጉቦ ተቀብለዋል የሚል ክስ ቀረበባቸው

ሜንዴዝ እና ባለቤታቸው

የፎቶው ባለመብት,GETTY IMAGES

የአሜሪካ ህግ መወሰኛ ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሊቀ መንበር ቦብ ሜንዴዝ የግብጽ መንግሥትን ለመደገፍ ጉቦ ተቀብለዋል የሚል ክስ መቅረቡን ተከትሎ ለጊዜው ከኃላፊነታቸው ለቀቁ።

የአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴር ፖለቲከኛው እና ባለቤታቸው የግብጽ መንግሥትን ለመደገፍ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዶላር ጉቦ ተቀብለዋል ሲል ከሷል።

የግብጽን መንግሥት በድብቅ ረድተዋል የተባሉት ጥንዶች ክሱን ውድቅ አድርገዋል።

አርብ ዕለት ይፋ በሆነው ባለ 39 ገጾች ክስ መሰረት ሜንዴዝ ስልጣናቸውን ተጠቅመው በአገራቸው እና በውጭ አገራት ባሉ የሙስና እቅዶች ላይ ተጽእኖ በማሳደር ተከሰዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሊቀ መንበር በአሜሪካ በሚገኘው የግብጽ ኤምባሲ ውስጥ የሚሰሩ ዲፕሎማቶችን በተመለከተ ከፍተኛ ሚስጥራዊ መረጃዎችን በማጋራት እንዲሁም የግብጽን መንግሥት ሚስጥራዊ በሆነ ሁኔታ የሚደግፉ እርምጃዎችን ወስደዋል በሚልም ከስ ተመስርቶባቸዋል።

ሜንዴዝ እና ባለቤታቸው ናዲን አርስላኒያን ከሶስት የኒውጀርሲ ነጋዴዎች ገንዘብ፣ ወርቅ፣ ለቤት ብድር የተፈጸመ ክፍያ እና የቅንጦት ተሽከርካሪ ጉቦ በመቀበል ተከሰዋል።

ባለፈው ዓመት የፌደራል የደህንነት ሰራተኞች በሜንዴዝ ቤት ፍተሻዎችን አካሂደዋል።

በነዚህም ፍተሻዎች ከ480 ሺህ ዶላር በላይ “በጥሬ ገንዘብ በአብዛኛው በፓስታ ውስጥ እንዲሁም በልብስ ውስጥ ኪሶች፣ በቁም ሳጥኖች እና ካዝናዎች ውስጥ ተደብቀው” ተገኝተዋል ሲልም አቃቤ ህግ በክሱ ገልጿል።

አቃቤ ህግ የጉቦ ስምምነቶችን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን አግኝተናል ብሏል።

ውዝግብ ውስጥ የገቡት የቋሚ ኮሚቴው ሊቀመንበር በትውልድ አገራቸው ኒውጀርሲ ከሚገኙ ዲሞክራቶች ከአባልነታቸው እንዲለቁ የቀረበላቸውን ጥያቄም ውድቅ አድርገዋል።

የህግ መወሰኛው ምክር ቤት መሪ ቹክ ሹመር አርብ ዕለት እንደተናገሩት ሜንዴዝ “ጉዳዩ እልባት እስኪያገኝ ድረስ” ከውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበርነታቸው ለመልቀቅ መወሰናቸውን ተናግረዋል።

የኒውዮርኩ ዲሞክራት ቹክ ሹመር የስራ ባልደረባቸው ሜንዴዝ “ህዝብን በጽናት የሚያገለግሉ እና ለኒውጀርሲም ማህበረሰብ ጠንክረው የሚታገሉ ናቸው” ብለዋቸዋል።

ከአውሮፓውያኑ 2006 ጀምሮ በአሜሪካ የምክር ቤት አባልነት ያገለገሉት የ69 አመቱ ሜንዴዝ ከውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበርነታቸው ሲለቁ የመጀመሪያው አይደለም።

በኒውጀርሲ ከሚገኙ የፍሎሪዳ የዓይን ሐኪም ጉቦ ጉቦ ተቀብለዋል የሚል ክስ በአውሮፓውያኑ 2015 ከቀረበባቸው በኋላ ከኃላፊነታቸው ለቀው ነበር።

ዳኞች በአንድ ድምጽ ብያኔ ማስተላለፍ ባለመቻላቸው ጉዳዩ ያለ ውሳኔ እንዲጠናቀቅ ምክንያት ሆኗል።

በወቅቱ የቋሚ ኮሚቴውን ኃላፊነት የተረከቡት የሜሪላንዱ የምክር ቤት አባል ቤን ካርዲን አሁንም ያንን ኃላፊነት ይረከባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

 

Source: BBC Amharic

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *