News

የካናዳ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የናዚ ቡድን አባልን በመጋበዛቸው ሥልጣናቸውን ለቀቁ

አፈ ጉባኤ አንተኒ ሮታ

የፎቶው ባለመብት,REUTERS

የምስሉ መግለጫ,አፈ ጉባኤ አንተኒ ሮታ

በናዚ የጦር ቡድን ውስጥ አባል ሆነው የተዋጉ ዩክሬናዊን በአገሪቱ ምክር ቤት ጋብዘው አድናቆታቸውን የገለጹት የካናዳ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሥልጣናቸውን ለቀቁ።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ሥልጣናቸውን እንዲለቁ የተደረገባቸውን ግፊት መጀመሪያ ላይ የተቃወሙት አፈ ጉባኤው አንተኒ ሮታ፣ ከፓርቲ መሪዎች ጋር ኦታዋ ውስጥ ከተወያዩ በኋላ ነው በፈቃዳቸው ከኃላፊነታቸው የለቀቁት።

ሮታ “ከምክር ቤቱ አፈ ጉባኤነት መልቀቅ አለብኝ” በማለት ፓርላማው ውስጥ ተናግረዋል። ጨምረውም “የተሰማኝን ጥልቅ ፀፀት መግለጽ እፈልጋለሁ” ብለዋል።

ባለፈው አርብ በምክር ቤቱ ውስጥ የተካሄደው ሥነ ሥርዓት ዓለም አቀፍ ውግዘትን ያስከተለ ነበር።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት አርብ ዕለት ካናዳ ውስጥ ካደረጉት ጉብኝት ጋር ተያይዞ፣ የ98 ዓመቱ ያሮስላቭ ሁንካን አፈ ጉባኤው “ጀግና” ብለው ከጠሯቸው በኋላ የካናዳ ምክር ቤት አባላት ከመቀመጫቸው ተነስተው በጭብጨባ አድናቆታቸውን ገልጸውላቸዋል።

በኋላ ላይ አፈ ጉባኤው እንዳሉት ግለሰቡ ከናዚ ጋር ግንኙነት እንደነበራቸው አለማወቃቸው በስህተት በፓርላማው ሥነ ሥርዓት ላይ እንዲገኙ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።

የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶም ሁኔታውን ተከትሎ ሰኞ ዕለት “ይህ መሆኑ በጣሙን የሚያበሳጭ ነው” ብለዋል።

“ይህ ሁኔታ ከካናዳ ፓርላማ በተጨማሪ ሁሉንም የካናዳ ዜጎችን በጣሙን የሚያሳፍር ነው” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

በምክር ቤቱ ደማቅ አቀባበል የተደረጋላቸው ዩክሬናዊው ያሮስላቭ ሁንካ፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በናዚዎች በሚመራ የዩክሬናውያን የወዶ ገቦች የጦር ቡድን ውስጥ አገልግለዋል።

ምንም እንኳን የጦር ክፍሉ በፍርድ ቤት በምንም አይነት ወንጀል ጥፋተኛ ነው ተብሎ ባይፈረጅም፣ አባላቱ ሰላማዊ ፓላንዳውያንን እና አይሁዶችን በመግደል ይከሰሳሉ።

ማክሰኞ ዕለት የፖላንድ የትምህርት ሚኒስትር ግለሰቡ ተላልፈው እንዲሰጡ የሚያስችል “እርምጃዎችን መውሰዳቸውን” ተናግረዋል።

የውዝግቡ ምክንያት የሆኑት አዛውንቱ ያሮስላቭ ሁንካ ቤተሰቦች ምላሽ እንዲሰጡ ቢቢሲ ያደረገው ጥረት አልተሳካም። አስካሁንም በጉዳዩ ላይ ለካናዳ መገናኛ ብዙኃን ያሉት ነገር የለም።

አፈ ጉባኤው ከሥልጣናቸው መልቀቃቸውን ከማሳወቃቸው ከሰዓታት ቀደም ብሎ የካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜላኒ ጆሊ “ሙሉ ለሙሉ ተቀባይነት የሌለው” ስህተት ነው ብለው በማለት አፈ ጉባኤው ሥልጣናቸውን መልቀቅ አለባቸው ብለው ነበር።

አፈ ጉባኤው ኃላፊነታቸውን መልቀቃቸውን ካሳወቁ በኋላ የካናዳ ባላሥልጣናት እና የካናዳ አይሁዳውያን ድርጅቶች ውሳኔያቸውን ትክክለኛ በማለት ተቀብለውታል።

ነገር ግን ሌሎች ደግሞ ጉዳዩ በአፈ ጉባኤው ሥልጣን መልቀቅ ብቻ ማብቃት እንደሌለበት በመግለጽ “ይህ ሁኔታ እንዴት ሊከሰት እንደቻለ” መታወቅ እንዳለበት የአይሁዳውያን ቡድኖች እየጠየቁ ነው።

የካናዳ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ፒየር ፖይሊቨር ለአገሪቱ ምር ቤት ባደረጉት ንግግር “በዓለም ላይ ባለን መልካም ዝና ላይ የደረሰውን ከባድ ጉዳት ለመቀልበስ” ኃላፊነቱ በጠቅላይ ሚኒስተር ጀስቲን ትሩዶ ላይ እንደሚወድቅ በመጥቀስ “ለዚህ አሳፋሪ ይቅርታ ይጠይቃሉ ወይ?” በማለት ጠይቀዋል።

Source: BBC Amharic

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *