News

ኢትዮጵያ – በጦርነት በሞቱ ሰዎች መርዶ ሐዘን ያጠላባት ትግራይ

የሚያለቅሱ ሴቶች

የፎቶው ባለመብት,REUTERS

በትግራይ ለሁለት ዓመታት በተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ምክንያት የሞቱ የትግራይ ኃይል አባላት መርዶ ባለፉት ቀናት ለቤተሰቦቻቸው እየተነገረ ነው።

እስካሁን የተደረገውን መደበኛ ያልሆነ እና ውስን የሚመስለውን መርዶ ተከትሎ በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች የሟች ቤተሰቦች ‘ግፍዒ’ ወይም ‘ኣገወል’ የሚባል ባህላዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት እና ሃይማኖታዊ ፍትሃት በጋራ እና በተናጠል እየተደረገ እንደሚገኝ የቢቢሲ ዘጋቢ ገልጿል።

በመቀለ ከተማ በአዲ ሀቂ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ብርሃኑ ገብሬ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ባለፉት ሁለት ሳምንታት የበርካታ ታጋዮች መርዶ እንደተነገረ እና ከተማዋም ሐዘን እንዳጠላባት ይገልጻሉ።

“በቅርብ ጊዜ በአዲ ሺንድሁን እና በደብር አካባቢዎች የበርካታ ታጋዮች መርዶ ተነግሯል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተካሄደ ባህላዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት ተሳትፌያለሁ። በጣም ያሳዝናል። ብዙ ሰዎች በቤተሰባቸው፣ በዘመድ አዝማድ እና በሚያውቋቸው ሐዘን ላይ ተቀምጠዋል” ይላሉ።

እሳቸው በሚኖርበት አካባቢ ባለፈው ቅዳሜ የሟቾች መርዶ እንደሚነገር ተገልጾ እንደነበረ የሚናገሩት አቶ ብርሃኑ፣ ወደ ሚቀጥለው ሳምንት መራዘሙን እና ጭንቀት ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

“ከአካባቢያችን ወጥተው ያልተመለሱ ወዳጆች እና ጎረቤቶች አሉ። በጣም ፈርተናል፤ ተጨንቀናል” በማለት በሰፈራቸው ያለውን ድባብ ያስረዳሉ።

ባለፈው ሳምንት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በጦርነቱ ውስጥ ተሳትፈው የሞቱ ተዋጊዎች መርዶ በቅርቡ እንደሚገለፅ ተናግረዋል።

“በቅርቡ ለክብራቸው በሚመጥን መልኩ ሕይወታቸውን የከፈሉት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰማዕቶቻችንን በይፋ መርዶ በመግለጽ ቢያንስ በተወሰነ ደረጃ ከእናንተ ጋር ነን ብለን ለቤተሰቦቻቸው መልዕክት እናስተላልፋለን” ብለዋል።

በትግራይ ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት ምን ያህል ተዋጊዎች እና ሰላማዊ ሰዎች እንደሞቱ በትክክል የሚታወቅ ነገር የለም።

ጦርነቱን ለማስቆም በተደረገው ሽምግልና የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ የነበሩት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ የፕሪቶሪያው ስምምነት ከመፈረሙ በፊት እንደተናገሩት በጦርነቱ 600 ሺህ ያህል ሰዎች ሞተዋል።

ከዚህ ባሻገር ደግሞ የተለያዩ ወገኖች በሁለት ዓመቱ ጦርነት የሞቱት ሰዎችን አሃዝ አስከ አንድ ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ይገልጻሉ።

ነገር ግን አስካሁን በጦርነቱ የጠፋውን ሕይወት በተመለከተ በትክክል የታወቀ አሃዝ የለም።

ከዚህ ባሻገር ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ሁሉም ተሳታፊዎች ግድያ፣ ጾታዊ ጥቃት እና ዘረፋን ጨምሮ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸማቸው በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።

በተለይም የጦርነቱ ዋነኛ አውድማ በነበረችው እና ለረጅም ጊዜ ተዘግታ በቆየችው ትግራይ ውስጥ ብዙ ሰዎች በደረሰባቸው ጥቃት፣ በምግብ እና በመድኃኒት እጦት ለሞት መዳረጋቸው ሲነገር ነበር።

በቅርቡ ከመቀለ ወደ ሽሬ የተጓዘው መዓርግ ኃይሌ ለቢቢሲ እንደተናገረው በትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች የሐዘን መርዶ እየተነገረ ነው።

“ከመቀለ ተነስተን በሐውዜን እና ከዚያም በተንቤን አድርገን ነው የመጣነው። ብዙ የሐዘን ልብስ የለበሱ ሰዎች እና የሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት የሚከውኑ ጃንጥላ የያዙ ቀሳውስት ናቸው የሚታየው። የጠየቅናቸው ሰዎች የተሰዉ ታጋዮች መርዶ መሆኑን ነግረውናል።”

ደቡብ ትግራይን ጨምሮ ለሥራ በተንቀሳቀሰባቸው አካባቢዎችም ተመሳሳይ ሁኔታ መመልከቱን የሚገልጸው መዓረግ፣ መርዶ የሚነገርበት ሁኔታ መደበኛ እንዳልሆነ እና በአፋጣኝ መስተካከል እንዳልበት ያስረዳል።

“እኔም በቅርቡ አዲ ጉዶም አካባቢ ሄጄ ነበር። እዚያም ተመሳሳይ ነው። እዚያ እንኳን ጦርነቱ እያለም ቤተሰቦች መርዶ ይነገራቸው ነበር።”

“በዚህ ሁኔታ የመረጃ ችግር ሊኖር ይችላል። ነገር ግን መረጃ ያላቸውን ቢያረዱ የተሻለ ነው። እንጂ ዓመቱን ሙሉ የሐዘን ነጠላ ማየት ተገቢ አይደለም” ሲል ያክላል።

የውቅሮ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዳንኤል የታጋዮች መርዶ እየተነገረ እንደሆነ እና ቤተሰቦችን የማርዳቱ ሂደት ግን ሥርዓትን የተከተለ ባለመሆኑ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ይገልጻሉ።

በየአካባቢው ያሉ እና የቤተሰብ አባሎቻቸው ያሉበትን ሁኔታ የማያውቁ ሰዎች በከባድ ጭንቀት ውስጥ የሚመጣውን እየተጠባበቁ መሆናቸውን “ብዙ ሰዎች ሐዘን ውስጥ ናቸው። ሁሉም ነጠላውን አዘቅዝቆ ነው የሚሄደው” ሲል ይገልጻል።

አሁን ያለው ቤተሰቦችን የማርዳት ሁኔታ መደበኛ ባልሆነ መንገድ መሆኑ በሐዘንተኞች ላይ ከባድ ሰቀቀንን እየፈጠረ መሆኑን በርካቶች የሚናገሩ ሲሆን በወላጆች ላይ የሚያደርሰው ሥነ ልቦናዊ ጉዳት አሳሳቢ ነው ይላሉ።

“ልጆቻቸው የት እንዳሉ የማያውቁ ቤተሰቦች በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ናቸው። ወደ ቀብር ሲሄዱ ለጠፉ ልጆቻቸውም ያለቅሳሉ። የሚያውቁት ነገር የለም። በተለይ ስለልጆቻቸው መረጃ የሌላቸው እናቶች ከፍተኛ ጭንቀትና የሥነ ልቦና ጉዳት ላይ ናቸው” ይላሉ አቶ ዳንኤል።

እሳቸው እንደሚሉት መርዶ የሚነገረው ወላጆች ልጆቻቸው ወደ ተመደቡበት ቦታ ሄደው የሥራ ባልደረቦቻቸውን በመጠየቅ እንጂ ወጥ የሆነ የታወቀ ሕጋዊ አሰራርን የተከተለ አይደለም።

“አንዳንድ ጊዜ ደብዳቤ ከክፍላቸው ተልኳል ይባላል፤ አንዳንድ ጊዜ የቀበሯቸው ጓዶቻቸው እንደሚነግሯቸው እንሰማለን። ከፊል የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ያለ ይመስላል።”

ለሥራ በተንቀሳቀሱባቸው የምሥራቅ ዞን አካባቢዎች ድርቅ መከሰቱን የሚናገሩት አቶ ዳንኤል፣ ይህ ችግር ሐዘን ታክሎበት ሕዝቡ በከባድ ሁኔታ እንደሚገኝ ማስተዋላቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ፕሪቶሪያ ላይ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ አስር ወራት የተቆጠሩ ሲሆን፣ በጦርነቱ የሞቱ ሰዎች መርዶ አስካሁን ሳይነገር ቆይቶ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ነው መነገር የጀመረው።

መርዶ መንገር የዘገየበት ምክንያትን አስመልክቶ “የተሰዉ ታጋዮች መጠን መብዛት፣ ቤተሰቦቻቸውን ለማጽናናት በቂ አቅም አለመኖር እንዲሁም መርዶ መንገር ላይ በወታደራዊ እና በፖለቲካ አመራሩ መካከል ልዩነት መኖሩ ይመስለኛል” ሲሉም አቶ ዳንኤል ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ነዋሪዎች በጦርነቱ ተዋጊ ሆነው የሞቱ የቤተሰብ አባሎቻቸው መርዶ መነገርን ተከትሎ በየመንገዱ የሐዘን ድንኳኖች ይታያሉ።

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በጦርነቱ ወቅት ወጥተው መርዶ ያልተነገራቸው እና አስካሁን ያሉበት ሁኔታ ያልታወቀ የቤተሰብ አባል ያላቸው ወላጆች በካበድ ጭንቀት ውስጥ ሆነው ነገን እየጠበቁ ነው።

ምንጭ፥ ቢቢሲ አማርኛ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *