Abiy Ahmed
Opinion

የጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ በአለም አቀፍ መድረክ ንግግሮቻቸውን በአማርኛ ቢያደርጉስ?

ጥቅምት 8, 2016 (ኦክቶበር 18፣ 2023 )

ከባጤሮ በለጠ

ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይም ሆኑ ሌሎች የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣኖች በአለም አቀፍ መድረኮች ደግመው ደጋግመው አማርኛን ከመጠቀም ይልቅ ችሎታቸው ብዙም ባልሆነው የእንግሊዝኛውን ቋንቋ ሲጠቀሙ ይታያል፡፡  በዛሬው የቻይና ቤልት ኤንድ ሮድ የመሪዎች ጉባኤ ላይም የታየው ይኽው ነው፡፡

ይህ ታዲያ ለምን ይሆናል ጥቅምና ጉዳቱስ ምንድን ነው የሚለውን ጥያቄ ማንሳቱ ተገቢነት ያለው ነው፡፡ አንዳንድ መሪዎች የብዙ ቋንቋ ተናጋሪዎች በሚገኙበት አለም አቀፍ ስብሰባዎች በእንግሊዝኛና በፈረንሳይኛ ቋንቋን በመጠቀም ከተለያየ ቋንቋ ተናጋሪዎች ጋር መነጋገርን ይመርጣሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ፣ በተለይም የራሳቸው ሀገር በቀል የሆነ ሀገራዊ ወይም ብሄራዊ ቋንቋ ያላቸው ሀገሮች መሪዎች ደግሞ የራሳቸውን ሀገር ቋንቋ መጠቀማቸው የተለመደ ነው፡፡

ለምሳሌ ከሚጠቀሱት መሀል የሩስያ የተለየዩ የአርብ ሀገራት፣ የቻይና፣ መሪዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የመንግስታት መሪዎች በአለም አቀፍ መድረኮች የራሳቸውን ለየት ያለ መገለጫ የሚያሳይ ቋንቋ ሲናገሩ ብዙ ትርጉምን ያስተላልፋል፡፡

ስለሆነም –
> በራስ ቋንቋ በመጠቀም ሀሳብን እንደልብ አፍታትቶ ምንም ብዥታ ሳይፈጠር መልእክታቸውን ያስተላልፋሉ፡፡ በሌላ ሀገር ቋንቋ በሚያደርጉት ንግግር ሀሳብን በጥልቀት ለማስተላለፍ፣ ብቻ ሳይሆን አድማጩም በተለየ ሁኔታ እንዳይተረጉመው የመለክት መዛባት እንዳይኖር ይረዳል፡፡

> ጠቀሜታው በአለም አቀፍ መድረክ የሀገርንና የህዝብን ልዩ ቋንቋ መጠቀም የራስ ባህልና የማንነት የኩራት መግለጫ ነው፡፡

> የራሳችን ባህል ታሪክ ማንነት መገለጫ ያለን የዳበረ ባህል ያለን ነው የሚለውን ጎላ ብሎ ለማስተላልፍ የሚረዳ መሆኑ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ ስልጣን በያዙ ሰሞን በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቋንቋ በአማርኛ ሲናገሩ የተደመጡ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከናካቴው አንድም ቃል በአማርኛ ሳይተነፍሱ በተሰባበረ እንግሊዝኛ ሲውተረተሩ ይታያል፡፡ ይህ ለምን ይሆናል ብሎ ሲታይ ፣ የምክንያቱን የሚያውቁት ጠቅላዩና አማካሪዎቻቸው ቢሆኑም የሚከተሉት ከምክንያቶች ውስጥ ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት ግ ን ይቻላል፡፡

> ዶክተር አብይ አንግሊዝኛ መናገርን የተማረ ሰው መለኪያ አድርገው ስለሚያዩ ፣ በአለም አቀፉ ስብሰባዎችም የበቃሁ የነቃሁ ነኝ የሚል መልእክት ሊያስተላልፉ ሰለሚያስቡ፡፡

> አብይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያራምዱታል በሚባለው አማራን “ልክ የማግባት ”፡ የፖለቲካ እስትራተጂ በተመለከት የአማርኛን ቋንቋ በአለም አቀፍ መድረክ መጠቀም በማቆም አለም አቀፍ ክብሩን ዝቅ ለማድረግ ስለፈለጉ፡፡

> በአለም አቀፍ መድረክ ላይ የሚደረግ ንግግር አድማጩ የሀገሩ ህዝብም ጭምር ሰለሆነ በሀገር ውስጥ ፡የአማራ ባህል አራማጅ ነህ ከሚሏቸውን ክፍሎች ወቀሳ ለማምለጥና አማርኛ ጠል ከሆኑ ብሄረተኞች ድጋፍ ለማግኘት፡፡

> በንግግራቸው ውስጥ አመርኛን ሳይጠቀሙ ሰለ ሀገር ክብር ማውራታቸው ለሀገሬው ህዝብም ይሁን ለውጭው አድማጭ አማርኛና ኢትዮጵያዊነትን ለያይቶ ለማሳየት ከጊዜ በዃላም የአማርኛን ቋንቋ ቦታ ዝቅ በማድረግ የሚፈልጉትን ለማድረግ (ለመተካት ወዘተ) መደላድል ለመጣል የሚያደርጉት ጥረት ሊሆን ይችላል፡፡

በአጭሩ መሪዎች በሀገራችው ቋንቋ ሲናገሩም ሆነ ሳይናገሩ የሚያስተላልፉት እጅግ ብዙ መልእክት እንዳለው ሁሉ የጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ ጉዳይም በዚሁ አውድ የሚታይ ከመሆን አያመልጥም፡፡፡

በሀገራችን ሁኔታ አማርኛ በመላው አለም አፍሪካን ጨምሮ ተፈላጊነቱ እየጨመረ በመጣበት በአሁኑ ሰአት፣ በራሽያና፣ በቻይና መሰል ታላቅ ተጸኖ ፈጣሪ ሀገሮች ከአንደኛ ደረጃ ትምርት ቤት ጀምሮ እንደ አንድ ትምህርት መስጠት በተጀመረበት በአሁኑ ሰአት፣ አፍሪካ ህብረት አማርኛን አህጉራዊ ቋንቋ ለማድረግ ምክክር በሚያደርግበት ሰአት፣ መላው አፍሪካም ከአውሮፓውያን ቋንቋ ይልቅ የራስ ሀገር በቀል ቋንቋንና ባህልን ወዘተ ለማዳበር በሚጥርበት ሰአት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ አማርኛ ቋንቋን ከመጠቀም እየራቁ መሄዳቸው አሳሳቢ ነው፡፡

በተለይም ደግሞ በራስ ቋንቋ መጠቀም ላይ ታላቅ ትኩረት በምትሰጠውና በቅርቡም አማርኛን በትምርት ካሪኩለሟ ውስጥ ባስገባችው ሀገር በቻይናው የቤልት ኤንድ ሮድ የመሪዎች ጉባኤ አንድም አማርኛ ሳይጭምሩ በእንግሊዝኛ ብቻ ንግግር ማድረጋቸው ለምን የሚል ትልቅ ጥያቄን ይቀሰቅሳል፡፡ ይህ እርምጃቸው የሚኖረውን ትልቅ ጎጂ እንደምታ ተረድተው ጠቅላይ ሚኒስቴሩም ሆኑ ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣኖች በተቻለ መጠን በአለም አቀፍ መድረኮች ሀገራዊ ቋንቋ እንዲጠቀሙ በማድረግ ለሀገራዊ መንነታችን ተሀድሶ በጎ አስተዋጻኦ እንዲያደርጉ እመኛለሁ፡፡

 

ሀገራችንን ፈጣሪ ይታደጋት

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *