EHRC
Press Release

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) ኅዳር 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ

Ethiopian-Human Rights

መግቢያ
1. የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) ኅዳር 28 ቀን 2015 ዓ.ም.
ባወጣው መግለጫ በኦሮሚያ ክልል በሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች እና በመንግሥት
የጸጥታ ኃይሎች መካከል በተለያዩ ወቅቶች በሚደረጉ ውጊያዎች እና ከውጊያ ዐውድ
ውጪ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ሳቢያ በሲቪል ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ሞት፣ የአካል
ጉዳት፣ ዘረፋ፣ የሰዎች እገታ እና መፈናቀል መፍትሔ ለመስጠት የፌዴራል
መንግሥት አፋጣኝ እርምጃ እና ተጨባጭ ዘላቂ መፍትሔ መስጠት የሚገባው
መሆኑን የሚገልጽ ሪፖርት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። እንዲሁም በሐምሌ 5 ቀን
2015 ዓ.ም. በዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርቱ በክልሉ ያለው የሰብአዊ
መብቶች ሁኔታ አሳሳቢ ሆኖ መቀጠሉን በመግለጽ፣ በተለይም የክልሉን ሰላም እና
ጸጥታ ማረጋገጥ የፌዴራል እና የክልል መንግሥቱ ቀዳሚ ተግባር እንዲሆን ማሳሰቡ
ይታወሳል። መግለጫውን ተከትሎ ኮሚሽኑ በክልሉ ያለውን የሰብአዊ መብቶች
ሁኔታ መከታተሉንና ምርመራ ማድረጉን ቀጥሏል።

2. በዚህም መሠረት በተለይም ከመስከረም 1 ቀን 2014 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 30 ቀን
2016 ዓ.ም. ድረስ በቄለም ወለጋ፣ በምሥራቅ ወለጋ፣ በሆሮ ጉድሩ ወለጋ፣ ጉጂ፣
ምዕራብ ጉጂ፣ አርሲ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ በሰሜን ሸዋ እና በምሥራቅ ሸዋ ዞኖች
ተጎጂዎችን፣ የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ የዐይን ምስክሮችን፣ የሕክምና ባለሙያዎችን፣
የሀገር ሽማግሌዎችን፣ አባገዳዎችን እና የመንግሥት አካላትን በአጠቃላይ158
ሰዎችን በተለያየ መንገድ በማነጋገር የተሰባሰቡ ግኝቶችን እና ምክረ ሐሳቦችን በዚህ
ሪፖርት አካትቷል።

3. ኢሰመኮ በምርመራው ምክንያታዊ አሳማኝነት (reasonable grounds to believe)
የማስረጃ ምዘና ደረጃ ተጠቅሟል።

4. ለዚህ ምርመራ መረጃ እና ማስረጃ በመስጠት የተባበሩ እና አሁንም የደኅንነት ሥጋት
ያለባቸው ተጎጂዎችን፣ ምስክሮችን እና ቤተሰቦቻቸውን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል
ኮሚሽኑ በምክንያታዊ አሳማኝነት ያረጋገጣቸው የተወሰኑ ከባድ የሰብአዊ መብቶች
እና የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶች እንዲሁም በሪፖርቱ የተካተቱ የጥሰት ዝርዝሮች
ውስጥ ጥሰቶች የተፈጸሙባቸው የአንዳንድ ተጎጂዎች ሰዎች ስም እና ዝርዝር
መረጃዎች አልተጠቀሱም።

5. ኢሰመኮ የዚህን የምርመራ ሪፖርት ግኝቶች በተመለከተ ለመንግሥት የጸጥታ አካላት
በተለይም በሀገር መከላከያ ሰራዊት አባሎች መፈጸማቸው የተረጋገጠ የሰብአዊ
መብቶች እና የሰብአዊነት ሕጎች ጥሰቶችን በዝርዝር የሚገልጽ እና ምላሽ የሚጠይቅ
ደብዳቤ ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር፣ ለኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ
መንግሥት ፖሊስ ኮሚሽን እና ሰላምና ጸጥታ ቢሮ መስከረም 24 ቀን 2016 ዓ.ም.
የላከ ቢሆንም ይህ ሪፖርት እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ምላሽ ባለማግኘቱ የተቋማቱን
ምላሽ በዚህ ሪፖርት ለማካተት አልተቻለም።

 

ወደ ሙሉ መግለጫው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *