መላኩ ተገኝ (ዶ/ር)፣ አንጋፋ ፖለቲከኛና ጸሐፊ የአለማያ ኮሌጅ ተማሪዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት ነበሩ፡
፡ ያኔ እነ ጥላሁን ግዛው የተገደሉበትና ለውጥ ጠያቂ ወጣቶች የታፈነ እልህና ቁጭት የሚንጣቸው ጊዜ ነበር፡፡ በጊዜው አለማያ ኮሌጅ ከሦስተኛ ክፍለ ጦር የተወሰነ ጦር መጥቶ ግቢውን በመክበብ ለ15 ቀናት ተማሪዎች ሳይንቀሳቀሱ መቆየታቸውንም ያስታውሳሉ፡
፡ የትግል መንፈሳቸውመነቃቃት የጀመረው እዚሁ አገር ቤት ኔዘርላንድስ ከመሄዳቸው በፊት መሆኑን ይናገራሉ፡፡
‹‹እኔን የመሳሰሉ ሰዎች ወደ ውጭ የሄድነው እኮ ለመማርና ለመሥራት አይደለም፣ ተደራጅቶ አብዮታዊ ትግል ለማድረግ ይጠቅማል በሚል ነበር፤›› ሲሉም ይናገራሉ፡፡ በኔዘርላንድስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ሶሻል ስተዲስ የፖስት ግራጁዌት ዲፕሎማ ተምረዋል፡፡ በዚሁ ጊዜ ጎን ለጎን ደግሞ የኦልተርኔቲቭ ፖለቲክስ ትምህርት ተከታትለው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል፡፡ ከደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ በዴቨሎፕመንት ሶሺዮሎጂ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን (ፒኤችዲ) ወስደዋል፡፡
በሥራ ረገድ የፋኖስ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሆነው ሠርተዋል፡፡ የናይል ተፋሰስ ዲስኩር ዳይሬክተርም ነበሩ፡፡ በአፍሪካ ኅብረት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የነባር ሕዝቦች ጥናት ቡድን ውስጥ አገልግለዋል፡፡ በተመድ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሊቀመንበር፣ እንዲሁም በወሰን አካባቢ ሕዝቦች መብት ተሟጋች ዓለም አቀፋዊ ካውንስል አባልም በመሆን አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡
ከተማሪዎች የፖለቲካ ንቅናቄ እስከ ኔዘርላንድስ የደረሰ የፖለቲካ ትግል አድርገዋል፡፡ መላኩ ተገኝ (ዶ/ር) ‹‹ከሰንጋ ተራ እስከ አምስተርዳም›› የተባለ ግለ ታሪካቸውን ያሰፈሩበት መጽሐፍ አበርክተዋል፡፡ የአብዮቱን 50ኛ ዓመት በተመለከተ ሰፊ ጉዳዮችን ያነሱበት ዮናስ አማረ ከእሳቸው ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ሪፖርተር፡- አብዮቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣቱን፣ የመሬት ጥያቄን ደርግ መመለሱን፣ እንዲሁም የብሔሮችን ጥያቄ ኢሕአዴግ ፈቶታል ቢባልም አብዮቱ ያነሳቸው ጥያቄዎች አሁንም አልተመለሱም የሚሉ አሉ፡፡ የመሬት ጥያቄ፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት፣ የሰብዓዊና የዴሞክራሲ መብቶች ጥያቄ የመሳሰሉት በአብዮቱ ወቅት የተነሱ በርካታ ጉዳዮች አልተመለሱም ስለመባሉ ምን ይላሉ?
መላኩ (ዶ/ር)፡- በእኔ ግምት የየካቲት አብዮት እኮ ተሸንፏል፡፡ ተሸነፈ ማለት ደግሞ የተነሳበትን ዓላማ አላሳካም ማለት ነው፡፡ ከሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም ጀምሮ እስከ ሴቶች መከበር ድረስ በርካታ በርካታ ጥያቄዎች ነበር ይዞ የተነሳው፡፡ ከእነዚህ ጥያቄዎች ውስጥ ወደ 95 በመቶ አልተመለሱም፡፡ ተድበስብሶ የመሬት አዋጅ ቢታወጅም ይህ ነው የሚባል ውጤት አላመጣም፡፡ በአጠቃላይ ስታየው ከየካቲት አብዮት በፊት ጀምሮ ሲነሱ የቆዩና በተማሪዎች ንቅናቄ፣ ቀጥሎም በአብዮቱ ጊዜ የተነሱ የዴሞክራሲና የመብት ጥያቄዎች እስከ ዛሬም ጨርሶ አልተነኩም፡፡ ይህ መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ የማንኛውም አብዮት ጥያቄ የፖለቲካ ጥያቄ ነው፣ የሥልጣን ጥያቄ ነው፡፡ ይህ ጥያቄ ካልተፈታ ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎች አይፈቱም ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ የሚታየው ችግርም ይኼው ነው፡፡
ደርግ የአብዮቱን ጥያቄ አልመለሰም እንዳይባል አንዱን የመሬት ጥያቄ ብቻ ነጥሎ የመሬት አዋጅ አወጀ፡፡ የመሬት አዋጁ ሙሉ ለሙሉ ጥያቄውን የመለሰ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ወታደራዊ መንግሥት ይህን ሊመልስ አይችልም፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ የመሬት ጉዳይ ብዙ ምሁራን እንደሚስማሙበት በአርሶ አደሮች አብዮት እንጂ በመሬት ሪፎርም አይመለስም፡፡ ከመሬት ጥያቄ ጋር ተያይዞ ብዙ ጥያቄዎች ስለሚከተሉ ነው፡፡ የመሬት ጥያቄ የመሬት ይዞታ ጥያቄ ብቻ አይደለም፡፡ የመሬት ይዞታው ምን ዓይነት ሥርዓት ውስጥ ነበር የነበረው የሚለውን መመለስ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ፊውዳላዊ ሥርዓት ውስጥ ነበር፡፡ ፊውዳል ሥርዓት ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ገጽታ ብቻ ያለው አይደለም፡፡ ፖለቲካንም፣ ማኅበራዊንም፣ ባህልንም የያዘ ነው፡፡ አንዱን የመሬት የኢኮኖሚ ገጽታ ብቻ እመልሳለሁ ብትል ሌላው ነገር ሊመለስ አይችልም፡፡
ሪፖርተር፡- አብዮቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣቱን፣ የመሬት ጥያቄን ደርግ መመለሱን፣ እንዲሁም የብሔሮችን ጥያቄ ኢሕአዴግ ፈቶታል ቢባልም አብዮቱ ያነሳቸው ጥያቄዎች አሁንም አልተመለሱም የሚሉ አሉ፡፡ የመሬት ጥያቄ፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት፣ የሰብዓዊና የዴሞክራሲ መብቶች ጥያቄ የመሳሰሉት በአብዮቱ ወቅት የተነሱ በርካታ ጉዳዮች አልተመለሱም ስለመባሉ ምን ይላሉ?
መላኩ (ዶ/ር)፡- በእኔ ግምት የየካቲት አብዮት እኮ ተሸንፏል፡፡ ተሸነፈ ማለት ደግሞ የተነሳበትን ዓላማ አላሳካም ማለት ነው፡፡