ከዚህ በመቀጠል በተከሰስኩበት ክስ የእምነት ክህደት ቃሌን እሰጣለሁ።
በቀዳሚነት የተከሰስኩት ጉዳይ የአማራ ህዝብ እኩል ከሌሎች ብሄሮችና ህዝቦች ጋር የአገር ባለቤት ሆኖ እያለ አገር ተወስዶበታል ብሎ ተናግሯል የሚል ነዉ።ክሴ ይሄን የሚል በመሆኑ አሁን ለፍርድ የቀረበዉ የአማራ ህዝብ የህልዉና ትግል ነዉ ማለት ነዉ።
የአማራ ህዝብ ላለፉት ሰላሳ አራት አመታት ፀረ አማራ ሀይሎች ተደራጅተው እና ተቀናጅተው ስልታዊ እና መንግስታዊ ጥቃት እያደረሱበት ያሉ ህዝብ ነዉ።
የአማራ ህዝብ የአገር ባለቤትነቱንበግልፅ በአደባባይ የተነጠቀዉ በ1983 ዓ.ም አማራ ጠል ሀይሎች የመንግስት ስልጣንን ተቆጣጥረዉ ባደረጉት የ ሰኔ 1983ቱ የቻርተሩ ጉባኤ ነበር።
ጉባኤው ያለምንም የአማራ ህዝብ ዉክልና የተካሄደ መሆኑን የስርአቱ ቁንጮ መለስ ዜናዊ በአደባባይ የመሰከረው ሀቅ ነዉ።በዚህ የቻርተር ጉባኤ የተመሰረተው የሽግግር መንግስት ባደረገው የክልል አከላለል ዉስጥ ምንም አይነት የአማራ ህዝብ ዉክልና ያልነበረው ሲሆን በዚህ የሽግግር መንግስት ዘመን የተዘጋጀው ህገመንግስትም የአማራን ህዝብ በማዉገዝ ተጀምሮ በማዉገዝ ያለቀ መሆኑን የቻርተሩ ጉባኤ ቃለጉባኤዎች ,የሽግግር ም/ቤቱ ቃለጉባኤዎች,የህገመንግስት ጉባኤ ቃለጉባኤዎች ዘላለማዊ ምስክር በመሆኑ ያስረዳሉ ።
በዘመኑ ትህነግ/ኢህአዴግ በአማራ ህዝብ ላይ የፈፀሙት አድሏዊ ድርጊቶች ,መፈናቀሎች,የንብረት ዉድመት,የዘር ፍጅትእና አገር አልባነት ልለፈዉና የዛ ስርአት ቀጥተኛ ወራሽ የሆነውን የብልፅግና ፓርቲ እና መንግስት በአማራ ህዝብ ላይ የፈፀመዉን እና እየፈጸመ ያለዉን በደል ልግለፅ።
የብልግና መንግስት በአማራ ህዝብ ተጋድሎ ወደ ስልጣን የመጣ ቢሆነም ህገመንግስታዊ ማሻሻያን ጨምሮ ፀረ አማራ የሆኑትን የመንግስት ፖሊሲዎች አስተካክላለሁ ብሎ ቃል ገብቶ የነበረ ቢሆንም በተግባር ግን አማራ ጠል መሆኑን ያስመሰከረዉ ጊዜ ሳይወስድ ነበር።
የብልፅግና መንግስት ከ ትህነግ ኢህአዴግ የወረሰውን የፌደራል እና የክልል ህገመንግስቶች ,ፖሊሲዎች እና መመሪያዎች ይዞ ቀጥሏል።ከ 50 በላይ በአማራ ህዝብ ላይ የዘር ፍጅት እንዲፈፀም ፀረ አማራነትን የሚቀሰቅሱ መፃህፍት አሳትሟል ።በምርምር መፅሄቶች ስም አማራ ጠልነትን ሰብኳል።በመንግስትነቱ በሚያስተዳድራቸው በኦሮምያ ቱሪዝም ቢሮ,በኦሮምያ ፕሬዝዳንት ፅ/ቤት,በኢትዮጽያ ፕሬስ ድርጅቱ ስር በሚታተሙ መፅሄትና ጋዜጦቹ በአማራ ህዝብ ላይ ለአመታት የቆየ የጥላቻ ዘመቻ አካሂዷል ።ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ፀረ አማረ ንግግሮች እና ትንኮሳዎች ተደርገዋል።
በተጨማሪም የብልፅግና መንግስት የአማራ ህዝብ የፖለቲካ ዉክልና እንዳይኖረው በማድረግ ዛሬ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠረው ከአማራ ክልል ዉጭ የሚኖረው የአማራ ህዝብ ምንም አይነት የፖለቲካ ዉክልና የለዉም ።
ከመንግሥት የስራ ሀላፊነት ጠርጎ በማዉጣት አድሎአዊ አሰራርን በማስፈን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በማፈናቀል ፣ በቢሊዮኖች የሚገመት የአማራን ህዝብ ሀብትና ንብረት በማውደም እንዲሁም ዘግናኝ የሆነ እንኳን ሊያዩት ሊሰሙት እንኳ የሚከብድ የዘር ፍጅት እንዲፈፀም አድርጓል ። ይህ የዘር ፍጅትበመላው ኢትዮጵያ በሶማሌ ፣ በኦሮሚያ ፣ በትግራይ ፣ በሲዳማ ፣ በቀድሞ የደቡብ ክልል ፣ በጋምቤላ እና በቤኒሻንጉል ክልሎች የተፈፀመ ነው ።
ለዚህም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የአይን ምስክሮች በተጨማሪ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ፣ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ላይ የሚሰሩ ጥምረት እንዲሁም አለም አቀፍ የሆኑት የተባበሩት መንግስታት ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና የሂውማን ራይትዎችን ዘገባዎች በማየት መረዳት ይቻላል ።
ጉዳዩን ሊከታተል ይችላል ተብሎ ይታሰብ የነበረው የብልፅግናው የአማራ ክልል መንግሥት ደግሞ እንኳን የአማራን ህዝብ ሊታደግ የገዛ ስልጣኑን የማያውቅ ፣ የፖለቲካ ነፃነቱን አሳልፎ የሰጠ እንዲሁም ከውሳኔ ሰጪነት ወደ ፈፃሚነት የወረደ ነው ። (ከክልሉ ውጪ ያሉ አማራዎች እንታገላቸዋለን እንጂ አንታገልላቸውም)ከማለት የደረሰ ሎሌ ነዉ።
በተደጋጋሚ ባጋጠሙ ጉዳዮችም ተፈትኖ የወደቀ ለምሳሌ በአማራ ልዩ ሃይል መፍረስ ፣ በፕሪቶሪያ ድርድር ፣ በሱዳን ወረራ ፣ በአጣዬ እና ሸዋሮቢት ፍጅት የአማራን ህዝብ መብት ማስከበር ያልቻለ ለተፈናቃይ ዱላ ለዘር ፈጂዎች ግን ካባ የሚሸልም ስብስብ ነው ።
የፌደራል መንግሥቱ ደግሞ ያለምንም እፍረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ፣ አቃቢ ህጉ ፣ መርማሪው ፣ ደህንነቱ ፣ የፍርድ ቤት አስተዳደር በአጠቃላይ የአንድ ብሔር/ሀይማኖት አባላት በመሆን ህግን የማጥቂያ መሣሪያ በማድረግ የአማርን ሕዝብ ልጆች ያጠቃል ።
የአማራ ሕዝብ ከላይ በጠቀስኳቸው ምክንያት የሀገር ባለቤትነቱ የተወሰደበት ፣ ሀገሩን የተቀማ በመሆኑ ፣ ድርጊቱም ሥርአታዊና መንግሥታዊ ለመሆኑ የሚመሠክሩ በርካታ ማስረጃዎች ያሉ በመሆኑ የአማራ ህዝብ ከዚህ የህልውና አደጋ ለመውጣት መንቃት ፣ መደራጀትና እራስን ከጥቃቶች መከላከል ይገባዋል የሚል የፀና አቋም ያለኝ በመሆኑ ይሄንን ዘረኛ እና ነውረኛ አንባገነን ሥርዓት ለመጣል ትግል እንደሚያስፈልግ እምነቴ ነው ።
በጭብጦቹም ላይ
* የሸዋ ፋኖን በማደራጀት በኩል የራሴን አስተዋፅኦ አድርጊያለሁ
*የአማራ ፋኖን ወደ አንድነት ለማምጣት ሲባል የተመሠረተው አመቻች ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆኜ ሠርቻለሁ
*የአማራ ፋኖ ምክርቤት እንዲመሠረት የራሴን አስተዋፅኦ አድርጊያለሁ
* አገሪቱ በተቀበለቻቸው ዓለምአቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችና የብልፅግና መንግሥት እመራበታለሁ በሚለው ህገመንግስት በሰፈሩት ሰብአዊና እና ዲሞክራሲያዊ መብቶቹን መሰረት በማድረግ የህዝቤን ግፍ እና በደል ለማስቆም በህቡዕ ሳይሆን በአደባባይ ታግያለሁ።
*የሰራሁት በሙሉ በግልጽ በአደባባይ የተፈፀመ እንጂ ምንም አይነት ህቡዕ ድርጅት አቋቁሜ አልሰራሁ።
*በህቡዕ አደረጃጀት ተፈፀሙ የሚሉትን ተግባራት አላዉቅም።አልፈፀምኩም
የኢትዮጵያ ህዝብ የአማራን ህዝብ በደል በደንብ ይገነዘባል ብዬ አምናለሁ የኢትዮጵያ ህዝብ “የአማራ ህዝብ እንባ በዋንጫ”ቢሰጣቸዉ የማይጎፈንናቸዉን የብልፅግና ስርአት ቁንጮዎች በቃችሁ ሊላቸዉ ይገባል።
በተጨማሪም የአማራ ህዝብ የህልዉና ትግል ለነፃነት ለእኩልነትና ለፍትህ የሚደረግ ትግል እንጅ ጠላቶቻችን እንደሚያወሩት ሌላዉን ለመጨፍለቅ የሚደረግ ባለመሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ የአማራን ህዝብ የህልውና ትግል ደግፎ እንዲቆም እጠይቃለሁ።
አለማቀፉ ማህበረሰብም የአማራ ህዝብ እየተፈፀመበት ያለዉን የዘር ፍጅትና መፈናቀል ቸል በማለቱ በጣም እያዘንኩ ለአምባገነኑ መንግስት ጅምላ ጨራሽ ድሮዎኖች እና ተተኳሾችን የሚያቀብሉ አገራት ታሪክና እና እግዚአብሔር ፍርዱን ይሰጣችኋል እላለሁ።
አመሰግናለሁ ።
ኅዳር 5/2017 ዓ.ም
ዶ/ር ወንዶሰን አሰፋ