ጋዜጣዊ መግለጫ
ጉዳዩ: – በውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ የሰብዓዊ መብት፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ተሟጋቾችና ታጋዮች የፈጠሩትን ኅብረት ስለማሳወቅ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ ደርሶባት የማያውቅ ከፍተኛ ፈታኝ ወቅት ላይ ትገኛለች። እንደ ሀገር የመቀጠል ዕድሏ ፈተና ውስጥ ገብቷል። በአንድነት፣ አብሮ ተስማምቶ ተጋብቶና ተዋልዶ የነበረው ሕዝቧ፣ ባለፉት 34 ዓመታት፣ ሆን ተብሎ በተተከለበት የዘር ፖለቲካ፣ ዛሬ አማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ ወዘተ እየተባባለ ተከፋፍሎ እንዲናከስ እየተደረገ ነው።
በአማራ ላይ የተካሄደውንና የሚካሄደውን የጅምላ ዘር ፍጅት ለማስቆምና፣ የአማራን ህልውና ለማረጋገጥ፣ ብሎም የሀገሪቱን ታሪካዊ አንድነት የጠበቀ፣ ሁሉን ያካተተ የሥርዓተ መንግስት ለውጥ እንዲመጣ፣ የፋኖ አርበኞች የሚያካሂዱት ትግል፣ በጦር ግንባር አያሌ ድሎችን ማስመዝገብን እንደቀጠለ ነው።
የዲሞክራሲ መድረኩን ተጠቅመው በሰላም እንዲታገሉ፣ ህጋዊ ህልውና የተሰጣቸው የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ህገ-መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት አንዳይታገሉ፥ ህዝባዊም ሆነ የድርጅታቸውን ጉባኤና የአመራር ስብሰባ እንዳያደርጉ ፣የተቃውሞ ሰልፍ አንዳይወጡ ታግደው፣ መሪዎቻቸው ወደ እስር ቤት እየተወረወሩ ፍዳቸውን እየከፈሉ ነው።
በደቡብ ኢትዮጵያ፣ የጉራጌ፣ የጉጂ፣ የቦረና፣ የሲዳማ፣ የወላይታ ሕዝብና ሌሎችም፣ የአብይ አህመድን የግፍ አገዛዝ በመቋቋም እና በመቃወም ያለተቋረጠ ትግል እያካሄዱ ነው። በኦሮሞ ልዩ አካባቢዎች ፣ በባህላዊ መንገድ በሰላሌ፣ በምዕራብ ሸዋና በአዲስ አበባ ዙርያ ህዝቡ ሕዝቡ ቀንበር ተሽክሞ፣ ካህናት፣ ሴት ወንድ፣ ሕፃን፣ አዋቂ፣ ሳይል፣ እረፍት ስጡን፣ ሰላማችን ይመለስ፣ ጦርነት ይብቃን፣ ወዘተ እያለ ተማፅኖ ሲያቀርብ ነበር ።
የፖለቲካ ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞች፣ የምክር ቤት አባላት ሳይቀሩ፣ በግፍ እየታፈሱ በየእስር ቤቶቹ ይታጎራሉ። ከመካከላቸውም የሚደበደቡና ለሰቆቃ የሚዳረጉ ሞልተዋል።
የሃይማኖት ተቋማት፣ በተለይ ሁለቱ የአንድነት ዋልታና ምሰሶ የሚባሉት የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እና የሙስሊም ተቋማት፣ በመንግሥት ጣልቃ ገብነት እየታመሱ ናቸው። አብያተ ክርስቲያናቱ፣ ገዳማቱ እና መስጊዶቹ ይደመሰሳሉ። የዕምነት ተቋማቱ ይደፈራሉ፣ መሪዎችና ምዕመናን በመንግስት ኃይሎች ይታሰራሉ፣ ይገደላሉ።
በመላው ኢትዮጵያ፣ ሰላምና መረጋጋት፣ ፀጥታ፣ ፈጽሞ የለም ማለት ይቻላል። የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች የጦርነት ቀጠና ሲሆኑ፣ የትግራይ ሕዝብም ገና ካለፈው አውዳሚ ጦርነት ሳያገግም፣ በሕወሃት መሪዎች መካከል በተፈጠረ የስልጣን ሽኩቻ ምክንያት ከባድ ውጥረት ውስጥ ይገኛል።
የሶማሌና የአፋር ክልሎች ሕዝብ፣ በድንበር ግጭት እንዲጠመድና እንዲፋተግ እየተደረገ ነው። በኦሮሞ ብልጽግና የበላይነት የሚመራው ገዥ ፓርቲና አገዛዝ ሙሉ ድጋፍ፣ የኦሮሚያ ክልል ከሱማሌ፣ ከሲዳማ፣ ከጋምቤላ፣ ከቢንሻንጉል፣ ከአፋርና ከጉራጌ ክልሎችና ቀጠናዎች መሬት በመቀማት፣ በሚያደርገው የግዛት መስፋፋት ጥረት በየጊዜው ውጥረትና ግጭት እንዲከሰት እየተደረገ ነው።
ይህ ብቻ አይደለም፣ ዜጎች ከአዲስ አበባ በየትኛውም አቅጣጫዎች በመኪና ተጉዘው፣ በሕይወትና በሰላም ለመመለስ ዋስትና የላቸውም። በዚህ ላይ ሰውን እንደከብት እያገቱ፣ ከዜጎች የመክፈል አቅም በላያ የሆነ ክፍያን መጠየቅ ተስፋፍቶ ስለሚገኝ፣ የዜጎች የዕለት ከዕለት ኑሮ በፍርሃትና ሥጋት እንዲዋጥ አድርጓል።
የኢኮኖሚ ድቀት፣ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት፣ ሕዝቡን ለመከራና ችጋር ዳርጎታል። በዚህ ላይ ሙሰኝነት ተንሠራፍቷል። ዓይን ያወጡ አድላዊነትና ጉቦ-በልነት፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ባለስልጣናት ሕይወት ጋር የተቆራኙ ሆነዋል።
እነዚህ ከብዙ በጥቂቶች የጠቀስናቸው፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የተጋረጡ ዘርፈ ብዙ ችግሮች፣ በእርግጥም ሀገሪቱ በመስቀለኛ መንገድ” ላይ መገኘቷን ያረጋግጣሉ።
ከፍ ብሎ እንደተጠቀሰው፣ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ጠቅላላ ሁኔታ ፣ እጅጉን አስጊና አደገኛ መሆኑ እየታወቀ፣ ይህንን ሀገርን በማፍረስ ላይ ያለ ዘረኛ አገዛዝ ለመታገል ፣ የሚካሄደውን የዘር-ፍጅት ወንጀሎች ለማስቆም፣ ዲሞክራሲያዊና አካታች የሆነ ሥርዓት በኢትዮጵያ እንዲመሠረት ለመርዳት ፣ ሀገር ውስጥ የሚደረገውን ከባድ መስዋዕትነት እያስከፈለ ያለ የህዝብ ትግል እንዲጎለብትና ውጤታማ እንዲሆን የሚያስችል፣ የአገሪቱን ግዙፍ ችግሮች የሚመጥን ትብብርና ኅብረት ለመፍጠር፣ በውጪ በምንገኘው ኢትዮጵያውያን ዘንድ እስካሁን አልተቻለም ነበር ።
ሰለዚህም ኢትዮጵያውያን፣ ሁላችን ቆም ብለን በማሰብና በመምከር፣ ከዚህ አስፈሪ የውድቀት አዙሪት በአስቸኳይ ለመውጣት እንድንችል፣ ሀገርን ከመፍረስ ዝቡንም ከዕልቂት ለማዳን የሚደረገው ፈርጀ-ብዙ ትግልና ጥረት እንዲጠናከር ለማድረግ ኅብረት ማስፈለጉን፣ ሶስት ድርጅቶች፣ ማለትም ኢትዮጵያዊነት፣ ኢትዮ-አሜሪካን የዜጎች ካውንስልና ኢትዮጵያን እናድን መድረክ አመኑበት። ሦስቱ ድርጅቶች ከሜሪካን-ኢትዮጵያውያን የሕዝብ ጉዳይ ኮሚቴ (ኤፓክ) ጋር በመተባበር፣ ጠንካራ ኅብረት ለመመስረት የሚቻልበትንና መንገድና ብልሃት፣ በመረጧቸው ወኪሎቻቸው አማካኝነት ለተወሰኑ ወራት ሲመረምሩና ሲያጠኑ ከቆዩ በኋላ፣ ስለህብረት እጅግ አስፈላጊነትና አንገብጋቢነት፣ እንዲሁም ስለ አወቃቀሩ፣ ስለአላማዎቹና ተግባሮቹ የደረሱበትን ውጤት፣ በአራቱም ድርጅቶች እንዲመከርባቸው አድርገው፣ ስምምነት ላይ በመደረሱ፣ ሌሎች የተደራጁና ያልተደራጁትን ሀገር ወዳዶችን በመጋበዝ፣ የካቲት 16/2017 (Feb. 23, 2025) ዓም ትብብሩ በርካቶችን አካቶ እንዲመሰረት በመፈለግ ጉባኤ ጠርተው ነበር። ያም ሆኖ ተጋባዥ ተሰብሳቢዎች ህብረት ለመመስረት ያግዛሉ ተብለው የቀረቡትን ረቂቅ ሰነዶች ለመመርመርና ለማጥናት ጊዜ ይሰጠን ብለው በጠየቁት መሰረት፣ የሁለት ሳምንታት ቆይታ ለማድረግ ስምምነት ተደረሰ።
ስለዚህም ትብብሩን ለመመስረት የካቲት 30/2017 (March 9, 2025) በተያዘው ቀነ ቀጠሮ ሙሉ መግባባት ስለተደረሰ፣ የኢትዮጵያውያን ትብብር ንቅናቄ፣ኢትን፣ (Ethiopian Solidarity Movement (Solidarity) የተሰኘ ድርጅት ለመመስረት ተችሏል። የዚህ ትብብር መስራች አባላት ድርጅቶች ስምንቱ ሲሆኑ ሌሎች ሁለት ድርጅቶች በአባልነት ሳይሆን በተባባሪነት በሚያግባቡ ፕሮግራሞች ለመሳተፍ ቃል ገብተዋል።
ስምንቱ መስራች ድርጅቶች፣
1) ኢትዮጵያዊነት
2) የኢትዮ-አሜሪካውያን ዜጎች ካውንስል
3) ኢትዮጵያን እናድን መድረክ
4) የአሜሪካን ኢትዮጰያዊያን የሕዝብ ጉዳይ ኮሚቴ (ኤፓክ)
5) ኒውዮርክ ትራይ ስቴት፣ ተስፋ ለኢትዮጵያ
(New York Tri-State, Hope for Ethiopia)
6) የሶማሌ ዲሞክራሲያዊ ካውንስል
7) የኢህአፓ ድጋፍ ኮሚቴ
8) የኅብረ-ኢትዮጵያ ግብረ ሀይል ሲሆኑ፣ በሚስማሙባቸው ፕሮግራሞች፣ በተባባሪነት ለመሳተፍ፣ ግሎባል የአማራ ዲያስፖራ መድረክና ቪዥን ኢትዮጵያ ራሳቸውን አስመዝግበዋል።
ከእነዚህ ትብብሩን ከመሰረቱት ስምንት ድርጅቶች ከእያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ተወካዮች ተመድበው፣ በድምራቸው 16 የሚሆኑ የትብብሩን ካውንስል መስርተው ሳምንታዊ ስብሰባቸውን አካሂደዋል።
ይህ ስምንት አባል ድርጅቶችን ያቀፈ ፟፟የኢትዮጰያዊያን ትብብር ንቅናቄ ፟ በመመስረቱ፣ በጉባኤው የተካፈሉ ሁሉ ደስታቸውን ሲገልፁ ፣ በርካታ ለኢትዮጵያ የሚቆረቆሩ ታዋቂ ግለሰቦችም በትብብሩ ውስጥ በሚመሰረቱ የተግባር ኮሚቴዎች ውስጥ በንቃት እንደሚሳተፉ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ከዚህም በላይ በዚህ በምስረታው ቀን ሊገኙ ያልቻሉ ሌሎች የሲቪክ፣ ሰብዓዊ መብት አስከባሪ ድርጅቶችና ድጋፍ ኮሚቴዎች የዚህን ትብብር መለስተኛ ፕሮግራም፣ መመሪያውንና ግቡን የተቀበሉ፣ትብብሩን ለመቀላቀል ከፈለጉ በሩ ክፍት መሆኑን እንዲታወቅ የትብብሩ መስራች ድርጅቶችና የጉባኤው ታዳሚዎች አምነውበታል። በተጨማሪም ከዚህም በላይ ትብብሩን ለመመስረት የቀረቡት ረቂቅ ሰነዶች ሁሉ፣ አዲስ በተቋቋመው የትብብሩ ካውንስልም ሆነ አዲስ በሚገቡ ድርጅቶች ሊሻሻሉና ሊዳብሩ እንደሚችሉ ለማስገንዘብ እንወዳለን።
ከዚህ በመቀጠል የትብብሩን ዓላማና ተግባር እንደሚከተለው እንገልፃለን።
የዚህ ትብብር ዋና አላማና ተግባር፣ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን አደገኛ ሁኔታ በመገንዘብ፣ ኢትዮጵያውያን ሀገራችንን ከውድቀት ለማዳን፣ በተለያዩ የፓለቲካና፣ የማህበራዊ ድርጅቶች፣ እንዲሁም በግል የሚያደርጓቸውን ጥረቶች ለማስተባበርና ለዲሞክራሲና ለፍትሕ የሚደረገውን ትግል በተጠናከረ መንገድ ለማገዝ ነው።
የዓላማ አንድነት መተክሎቻችን (Unity of Purpose and Principles)
1) የኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነትዋ እንዲጠበቅና የሕዝብዋም ሉዓላዊ ሥልጣን እንዲከበር፣
2) የኢትዮጵያ ሕዝብ መሠረታዊ ነፃነቶቹ፣ ሰብዓዊና የዜግነት መብቶቹ ተከብረውለት በሠላም እንዲኖር፣
3) ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲመሠረትና ተጓዳኝ ተቋሞችም በነፃነት እንዲሠሩ ፣
4) ኢትዮጵያ ውስጥ የሕግ የበላይነት እንዲኖርና ፍትኅና ርትዕ እንዲሰፍን፣ የፍትህ ተቋሞችም በነፃነት እንዲሠሩ፣
5) ኢትዮጵያውያን በአያሌ ሽህ ዘመናት አብሮነት የማኅበራዊ፣ የባህል፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ የጋራ እሴቶችንና ትስስሮችን እንደፈጠሩ መረዳት፣ የተወሰኑ ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆኖ፣
6) የሁሉም ብሔረሰቦች/ጎሳዎች፣ ቋንቋዎች፣ ኃይማኖቶች፣ ባህሎች እንዲከበሩና አንድ ሀገራዊ የጋራ መግባቢያ ቋንቋም እንደሚያስፈልጋቸው መረዳት፣
7) የኢትዮጵያ ሕዝብ ከድህነት ተላቆ የተሻለ የኢኮኖሚ አቅም አግኝቶ፣ የተሻለ ህይወት እንዲኖር፣
8) የኢትዮጵያ ሕዝብ ህገ መንግስቱ የሚፈቅድለትን የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመሰብሰብ የመደራጀትና የተቃውሞ ሰልፍ የማድረግ መብቱን ተጠቅሞ፣ ሰላማዊና ህዝባዊ እምቢተኝነትን እንዲጠቀም ማንቃት፥ ማበረታታትና ማገዝ፣
9) ግፍ፣ በደል፣ በዘር ተፈርጆ መጠቃት፣ መዘረፍ፣ መፈናቀልና መባረር፣ ቤታቸው በባልሥልጣኖች ፈርሶባቸው ሜዳ-ላይ መጣል፣ የጅምላ ግድያና ጦርነት አስመርሯቸውና አንገሽግሿቸው ግፍን መታገል የጀመሩትን ወገኖቻችንን ማበረታት፣መደገፍ፣ ማገዝ፣
10) ኢትዮጵያ ውስጥ የዜግነት መብት እንዲከበርና፣ ከፋፋይ፣ ጥላቻን አራማጅና ጎጂ የሆነውን ዘውግ ተኮር ፖለቲካን በማስቆም፣ በእኩልነትና መከባበር ላይ የተመሠረቱ ግንኙነቶችን ማዳበር፣
11) መንግሥትና ሌሎችም የፖለቲካ ሃይሎች፣ እንዲሁም ህጋዊ ሰውነት ያላቸው አካላት፣ ግዴታቸውን ባለመወጣት፣ ማለትም ማድረግ ያለባቸውን ነገር ባለማድረግም ሆነ ማድረግ የሌለባቸውን ነገር በማድረግ፣ ወንጀል ወይም በደል በመሥራት፣ ለሚፈጽሙት ማንኛውም ጉድለትና ጥፋት ተጠያቂዎች ማድረግ፣
12) ሕዝብን ከዕልቂት፣ ሀገረን ከጥፋት በመታደግ፣ በጦርነትና የዘውግ ፖለቲካ አካሄድ፣ በጣም የደቀቁትንና የተጎዱትን አካባቢዎች፣ እንደደረሰባቸው ጉዳት መጠን፣ ቅደም-ተከተሉን በማስያዝ፣ የሚያገግሙበትን ሁለንተናዊ እርምጃ ሙሉ ድጋፍ መስጠት ፣
13) በፍረጃና በአሠሳ፣ በየማጎሪያዎችና እስር-ቤቶች እየማቀቁና እየተሰቃዩም ያሉትን የኅሊና እስረኞች በሙሉ፣ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ እንዲፈታ፣ መንግሥትን ለማስገደድ፣ ያልተቋረጠ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ ማድረግ፣
14) የዓቢይ አገዛዝ የሀገር ጥቅምን ያስቀደመ፤ በዕውቀትና በብልሃት የተተለመ፤ ዲፕሎማሲ ማራመድ ፈጽሞ ተስኖት፣ የሌሎች ሀገሮችን ፍላጎትና ጥቅም በማራመድ፣ ከጎረቤት አገሮች፤ ለምሳሌ፦ ከሶማልያ ሬፐብሊክ፣ ከሱዳን፣ ከጂቡቲና ከኤርትራ ጋር በየጊዜው ያለመግባባት እየፈጠረ፣ በአደገኛ፤ የቃላት ጦርነት ሲያካሂድ ይታያል። ይህ መዘዙ በጣም አስከፊ ውጤት ሊያስከትል ይችላል። ከቃላት ጦርነት በላይ ጠብ አጫሪነቱ ወደ አላስፈላጊ ግጭቶች ሊያመራም ስለሚችል፣ ይህም ተጨማሪ የሀገሪቱ ስጋት በመሆኑ ፤እንደሌሎቹ ሁሉ መፍትሔን ይሻል።
በኅብረት ትግላችን ኢትዮጵያ ታሸንፋለች!!!
ኢትዮጵያ፣ ለዘለዓለም ትኑር!!!