አምባገነኖች ውጤቱ አስቀድሞ የሚታወቅ ቢሆንም መደበኛ ምርጫ እንዲካሄድ ለምን አጥብቀው ይጠይቃሉ? ይህ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች እንደ አቢይ አህመድ እና ሟቹ መለስ ዜናዊ ባሉ መሪዎች ስር በቁም ነገር መጠየቅ ያለበት ጥያቄ ነው። በመጀመሪያ ሲታይ እርስ በርሱ የሚጋጭ ይመስላል፡ – አንድ መንግሥት ወታደራዊ ኃይልን፣ የጸጥታ ኃይሎችን፣ ሚዲያዎችን፣ ፍርድ ቤቶችን እና የምርጫ ተቋማትን የሚቆጣጠር ከሆነ፣ ምርጫን የማደራጀት ጊዜን፣ ወጪን እና የፖለቲካ አደጋን ለምን አሁንም ያልፋል? ነፃ የፖለቲካ ውድድርን የማይፈቅድ መንግሥት በየጥቂት ዓመታት ምርጫ እንዲካሄድ ለምን አጥብቆ ይጠይቃል? ያለ ምርጫ ለምን በሥልጣን ላይ አይቆይም?
በእንደዚህ ዓይነት ሥርዓቶች ውስጥ የምርጫ ውጤቶችን ስንመለከት ይህ ጥያቄ የበለጠ አስፈላጊ ይሆናል፣ ገዥ ፓርቲዎች ብዙውን ጊዜ እጅግ በጣም ትልቅ በሆነ ህዳግ፣ አንዳንድ ጊዜ 90%፣ 95% ወይም 99% ያሸንፋሉ። በ 2002 እና በቀጣዩ ጠቅላላ ምርጫ ተብየው ድራማ ኢሕአዴግ/ህወሓት መጀመሪያ በ 99% ቀጥሎ በተካሄደው ጠቅላላ 5ኛው ሐገራዊ ምርጫ ተብየው 96% አሸነፍን በሚል ድራማ ስልጣናቸውን አስቀጠሉ። ይህ በተከታታይ ሁለት ክልላዊ እና ጠቅላላ ምርጫወች የታየው ውጤት አይን ጨፍነው በሐገሪቱ ተቃዋሚም ሆነ የተለየ ሐሳብ የሚአስተናግድ የለም የሚል አይነት ውጤት ነበር ያስመዘገቡት። ትዝ እንደሚለን በአንዷ የአሜሪካን ባለስልጣን 2012 በነበረ የአሜሪካንን አቋም አስመልክቶ በተጠየቁት ጥያቄ ሱዛን ራይስ የተባሉት የኦባማ መንግስት ባለስልጣን ሳቃቸው እስኪያፈተልካቸው በህወሓት የ 99% ማሸነፍ አፊዘዋል። ብዙ አልቆየም ፕሬዜዳንቱ ኦባማም አዲስ አበባ ድረስ ሄደው ነጻ ምርጫ የሚካሄድበት ሐገር ነው ብለው የዲፕሎማሲ ውሸትን አስመዝግበው በተመለሱበት ሰሞን የግዜዋ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ማዳም ክሊንተን ተመሳሳይ የሆነ የአለቃቸው ቃል ደግመዋል። የታላቋ ሐገር መሪወች የተናገሩት ከሕዝብ ልቦና ሳይወጣ እና ሳይውል ሳያድር ቢባል ይሻላል የሕዝብ ተቃውሞ ተነስቶ ሐገሪቱ ትናጥ ጀመር። ያ የሕዝብ ተቃውሞ እየሰፋ ሲሄድ የጨነቀው እርጉዝ ምን ይላል እንዲሉ ህወሓት ለደቡቡ ተወላጅ ለሐይለማርያም ደሳለኝ የጠቅላይሚኒስቴርነቱን ቦታ ለቃ ከጀርባ ሆኖ መዘወር የተሻለ ነው በሚል ሌላ እስትራቴጅ በተግባር አዋለች። ያም አልረዳም እንዴውም ተቃውሞው ስፋት እና ጥልቀት አግኝቶ መላ ሐገሪቱን አጥለቀለቃት ብሎም የህወሓት አመራር ለእርቅ እና ለተሻለ ሰላማዊ እና ዘላቂ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ከማምጣት ይልቅ ከልሂቅ እስከደቂቅ ተሰባስበው ከ 27 አመታት በላይ ወደረሷት መቀሌ ገቡ።
አሁን ላይ ቆሞ ያን ግዜ ስንቃኘው ግን ሰላምን፤ እርቅን፤ የሽግግር መንግስትን ሲጠይቅ ለኖረው ተቃዋሚ ቢለቁለት ኖሮ ከዚያ በኋላ የደረሰው የሕዝብ እልቂት እና እስከአሁን የቀጠለው ጀኖሳይዳል ጦርነት ባልኖረ ነበር። አሁንም ታሪክ በሳይንሳዊው መስፈርት እራሷን አትደግምም ይባላል እውነትም ነው አንድ ቁሰአካል ያድጋል እድገቱን ጨርሶ ወደሌላ ቁሰአካል ይለወጣል እንጅ ደግሞ ደጋግሞ በተመሳሳይ ቁሳዊነት እና ይዘት አይከሰትም ማለትም ነው።በሐገረ ኢትዮጵያ እና ሐገሪቱን ለ 50 አመታት ለችግር በጣሏት ጠባብ ድርጅቶች ተተብትቦ ባለው ሐገራዊ ሁኔታ የታሪክ ድግግሞሹ አንድ ወይንም ሁለት አይደለም መቶ እና ከዚያ በላይ ተደጋግሞ አይተናል። እራሱን ብልጽግና ብሎ የሚጠራው (ድንቄም መበልጸግ) ዳግማይ ኢሕአዴግ በአልጋ ተኝቶ እንደሚያጣጥር በሽተኛ የመንግስቱ ህይወት ከአረብ ሐገራት በተሰበሰበ መሳርያ እንደቀጠለ የሚታይ የሚዳሰስ ጉዳይ እያለ መልካም መሽሎኪያን ከመዘየድ ይልቅ። ምርጫ በማይታሰብበት አሁናዊ ገሐድ ምርጫ ለማድረግ የተነሳሳው የሚጋጋጠው በቀጣይ የሚያደርጋቸውን ጥፋቶሽ ስሌት ውስጥ በማግባት ሲሆን። በኢትዮጵያውያን ስም ያቀደውን እና በትንሸየዋ የአረብ ኤምሬትስ ፍላጎት ቀይባህርን የአንድ ልእለ ኀይል ባለቤት ለማድረግ የተዘየደውን። ከሁሉም በላይ ዛሬ አረብ አለምን እንደገና አፍርሶ ለመስራት የታቀደውን እቅድ አዳባሪ ሌላ ክልላዊ ጦርነት ለማስቀጠል የታሰበ እና ሕጋዊነትን ለማግኘት የተጸና የምርጫ ድራማን ለማድረግ መወሰኑ ህወሓት ሐይለማርያም ደሳለኝን መምረጥ ያም ሳይሆን መፈርጠጥ እና መቀሌ መከተምን ዳግም ታሪክ አስታዋሽ ነው።
ስለዚህ፣ ጥያቄው ምርጫዎች ይካሄዳሉ ወይ የሚለው ብቻ ሳይሆን ለምን ይካሄዳሉ? በምን ሁኔታዎች ይካሄዳሉ? እናም ይህን ቀጣይ ምርጫን በማካሄድ ማንን ይጠቅማል ማንስ ተጎጅ ይሆናል?የሚሉትን ጥያቄወች ማንሳት እና መመለስ ተገቢ ይሆናል። በተደጋጋሚ በተቋማት ላይ ጭቆና እና እቀባ በሚካሄድበት ሐገር እና መንግስት፣መንግስትን የተቹ በዘራቸው አማራ የሆኑት በእብነበለ ፍርድ እስራት እንግልት በሚካሄድበት ሐገር እና ፍትሐዊ ዳኝነትን በሚጸየፍ አስተዳደር ለምን መደበኛ ምርጫ ለማካሄድ አሁንም አጥብቆ ይጠይቃል? እነዚህ ምርጫዎች ለስልጣን ላይ ላሉት ምን አይነት ፖለቲካዊ፣ ህጋዊ እና አለምአቀፍ ጥቅሞችን ይሰጣሉ? ከሁሉም በላይ ደግሞ በእንደዚህ አይነት የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ በምርጫ ውስጥ መሳተፍ ዲሞክራሲን ወይስ የገዢውን ስርዓት ያጠናክራል?ብለንም የምርምር ጥያቄወች ብናቀርብ ሄዶ ሄዶ የምናገኘው መልስ አንድ እና አንድ ብቻ ይሆናል።
በኢትዮጵያ አሁናዊ የፖለቲካ ሁኔታ፣ ብዙ የተቃዋሚ ቡድኖች እና የፖለቲካ ታዛቢዎች መጪው ምርጫ አስተማማኝ የምርጫ ሂደት ዝቅተኛውን መስፈርት ስለማያሟላ ነፃ፣ ፍትሃዊ ወይም ህጋዊ ተደርጎ ሊወሰድ እንደማይችል ይከራከራሉ። ምርጫዎች የምርጫ ሳጥኖችን ማስቀመጥ እና ድምጽን መቁጠር ብቻ አይደሉም። ምርጫ ህጋዊ እንዲሆን የተወሰኑ መሰረታዊ ሁኔታዎች መኖር አለባቸው። የመራጮች ደህንነት፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የመደራጀት እና የምርጫ ዘመቻ ነፃነት፣ ገለልተኛ ፍርድ ቤቶች፣ ነፃ ሚዲያ፣ ገለልተኛ የጸጥታ ኃይሎች እና ያለፍርሃት ወይም ያለ ጫና የህዝቡ ተሳትፎ ዋነኞች ናቸው። በአብይ አህመድ በሚመራው መንግስት እያዘጋጀ ያለው ሐገራዊ ምርጫ በተቺዎች፤ በታዛቢ ምሁራን እና በራሳቸው በተቃዋሚ ድርጅቶች እነዚህ ሁኔታዎች በአሁኑ ጊዜ የሉም ብለው ይከራከራሉ። የተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪዎች ላይ እየተካሄደ ያለውን ዛቻ እና ማስፈራራት እያየን ነው።ጋዜጠኞች አግባብ ጥያቄወችን አይጠይቁም ወይንም በያዙት የጋዜጠኝነት ሙያ አፋጠው መልስ አያገኙም ወይንም የራሳቸውን አስተያየት ለመስጠት አይችሉም ባጭሩ እዳይታሰሩ ወይንም ሌላ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ይጠነቀቃሉ ለህይወታቸውም ይፈራሉ። ከዚያም በተጨማሪ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ተገድበዋል። የተቃዋሚ ፓርቲዎች በነፃነት ዘመቻ ማካሄድ ካልቻሉ፣ ሚዲያዎች በነፃነት ሪፖርት ማድረግ በማይችሉበት ጊዜ እና ፍርድ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ነጻ ባልሆኑበት፣ የምርጫ ሂደቱ ዴሞክራሲያዊ ሳይሆን አስተዳደራዊ ይሆናል ማለት ነው። እናም እያየን ያለው መሪዎችን በዴሞክራሲያዊ ውድድር የመምረጥ ሂደት ሳይሆን ስልጣንን በሀይል እና በአንድ ጎንዮሽ ፕሮፖጋንዳ የማረጋገጥ ሂደት ይሆናል። ቱማታ እየተነፋለት ያለው 7ኛው ተብየው የብልጽግና ምርጫ ሌላው እና ከአለማቀፍ መስፈርትም ሆነ ከህጋዊነት የሚያስፈነጥረው ጉዳይ ምርጫው ከግማሽ በላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ያላካተተ ግን ኢትዮጵያን ሊወክል የተነሳሳ የቀሽም አራዶች ምርጫ መሆኑ ነው። ለምሳሌ በሁሉም የአማራ አካባቢወች ጦርነት እየተካሄደ ነው። እንዴው በራሳቸው እስታትስቲክስ እንኳን አማራው 36 እስከ 40 ፐርሰንት ቢሆን ይህ አሃዝ የሐገሪቱ ከአንድ ሦስተኛ በላይ ነው ማለት ይሆናል። ከዚህ ላይ የትግራይን ክልልን ከዚህ ብንጨምረው ትግራይ ከ 5 እስከ 8 ፐርሰንት ነውም እንበል ይህ አሃዝ ከአማራ ክልል ጋር ሲቆራኝ የሐገሪቱ ግማሽ ለመሆን ትቂት ቁጥሮች ይፈልጋል። ሄደንም ኦሮሚያ የሚካሄደው ጦርነት ያለ ቁጥር አይደለም ምክንያቱም ብልጽግና እጅግ አናሳ የሆነ ክፍል ብቻ አመጹን የሚያካሂደው ለራሱ ሲል በኦሮሚያ ሰላምን በግድ ወይንም በውድ አስፍኖ ወደምርጫ በሄደ ነበር ግን አይደለም እናም ይህ በአመጽ ላይ የኦሮሚያ የሕዝብ ቁጥርን እስኪ ከ 8 እስከ 10 ፐርሰንት ባለው አሀዝ እናስገባው።ከዚህ በላይ ባስቀመጥሁት ጭብጥ አሃዝ ይህ እየተነገረለት ያለ ምርጫ የሚያስወግደው የአገሪቱ የህዝብ ቁጥር ከ 55 እስከ 60 ፐርሰንት የሚደርሰውን ሕዝብ ነው ማለት ነው። እናም ይህ ምርጫ ብዙ ሳንጓዝ ህገወጥ ምርጫ ነው የህግ ልባስ እንዳንሰጥ እንጠንቀቅ። ይህን ምርጫ ህገወጥ ስንል የአለማቀፍ የምርጫ መብት መከበር ጉዳይ በአለማቀፍ ሕግ የተካተተ የተባበሩት መንግስታት ዋና ጉዳይ የሆነውን በ 1948 በፈረንሳይ ዋና ከተማ በተደረገው የተባበሩት መንግስታት ኮንቬንሽን አለም የተስማማበትን መርህ በመመርኮዝ መሆኑ እንዲታወቅልን።
The Universal Declaration of Human Rights (UDHR) እና United Nations General Assembly in Paris on 10 December 1948 (Resolution 217 A) ነጻ እና ግልጽነት ያለው ምርጫን መስፈርቶች ይዘረዝራል። በዚህ መስፈርቶች ኮሮጆ ግልበጣ። የነጻ ሚዲያ በእኩል አለመዳረስ፤ ማስፈራራት እና በተወዳዳሪወች ላይ ዛቻ ወይንም እስራት። ከዚያ ወጥቶም ተወዳዳሪወች ላይ ከስልጡን የፖለቲካ ክርክር ዘሎ ስም ማጣፋት ያልሰሩትን ሰሩ በሚል መወንጀል ሁሉ የዚሁ ኮንቬንሽን ትንታኔ ነው። ሆኖም ዛሬ ባገራችን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የምርጫ ሒደት ጨርሶ ሕገወጥ የምርጫ ዘመቻ መሆኑን ከወዲሁ ማሳየት ተገቢ እና ውርድ ከራሴ የሚያስብል ነው።ባጠቃላይ ይህ የኢትዮጵያን ከግማሽ በላይ ሕዝብ ያላካተተ ምርጫ የወንበዴ እና የህገ ወጥ ፋሉሎች እንጅ ትክክለኛ እና ሕጋዊ ምርጫ የሚያስብል አንዳችም ጠብታ ስለሌለበት እውነተኛ ለሕዝብ እና ከሕዝብ ጋር የቆሙ የተቃዋሚ ድርጅቶች እራሳቸውን ከዚህ ምርጫ ቢያግዱ በታሪክም ፊት ተገቢ ክብር የሚሰጣቸው ታሪካዊ ኩነት ይሆናል።ግን ይህን ምርጫ አጅበው እና ህጋዊነት ሰጥተው ከተወዳደሩ ይህ ዘረኛ፤ ፋሽስታዊ እና ጦርነት ቀፍቃፊ የሆነው ስርአት የጀመረውን ሕገወጥ እና ጀኖሳይዳል ጦርነት ለማስቀጠር የመተባበር ያህልን ጉዳት ያደርሳሉ።
ለማጠቃለል ይህ የምርጫ ድራማ ከወዲሁ ውሳኔው እንደሚያመላክተው አብይ አሕመድ አሊ የኔ ለሚላቸው የምርጫ ተወዳዳሪወች እንደኢዜማ ላሉ ድርጅቶች እና ላያልፉ ብሎ ላአሰባቸው ቦታ እንደለቀቀላቸው የሚያሳዩ የምርጫ ወረዳወች ተስተውለዋል። ይህ የሚያመላክተው አብይ ምርጫውን በስንት ፐርሰንት ማቸነፍ እንዳለበት ቀድሞ የተወሰነ መሆኑን ነው።



