ኢሰመጉ
News

በእምነት ተቋማት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በአስቸኳይ ይቁሙ! – ኢሰመጉ

ታኅሣሥ 14/2012ዓ.ም

በኢሰመጉ የተሠጠ መግለጫ

ኢሰመጉ – የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 27 (1) ማንኛውም ሰው የማሰብ፣ የኅሊና እና የሃይማኖት ነጻነት እንዳለው ይደነግጋል፡፡ ይህ መብት ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል፣ ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተማር ወይም የመግለጽ መብትን እንደሚያካትት ይገልጻል፡፡ የሃይማኖት ተከታዮች ሃይማኖታቸውን ለማስፋፋትና ለማደራጀት የሚያስችሏቸው የሃይማኖት ትምህርትና የአስተዳደር ተቋማት ማቋቋም እንደሚችሉም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 27 (2) ተደንግጓል፡፡ ይህንንም መብት የማስከበር ግዴታ በዋናነት የተጣለው በመንግሥት ላይ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ሊከበር ባለመቻሉ ዐርብ ታኅሣሥ 10 ቀን 2012ዓ.ም በግምት ከምሽቱ 1፡30 ገደማ በሞጣ ከተማ በሚገኙ አራት መስጊዶችና ንብረትነታቸው የሙስሊም ወገኖቻችን የሆኑ መደብሮች፣ ሆቴሎችና የንግድ ድርጅቶች ላይ ቃጠሎ መፈጸሙን እንዲሁም የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች መዘረፋቸውንና የንብረት ማውደም እንደተፈጸመባቸው በአካባቢው የሚገኙ የኢሰመጉ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በዚያው ዕለት በመስጊዶቹ ላይ ከተፈጸመው ጥቃት ቀደም ብሎ በሞጣ ከተማ በሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ላይ የቃጠሎ ሙከራ ተፈጽሟል፡፡ ይህ ሁኔታ ስለችግሩ መባባስ ዓይነተኛ ማሳያ እንደሆነ ኢሰመጉ ያምናል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የሐገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት ላይ በተደጋጋሚ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ተስተውሏል፡፡ መንግሥት የሃይማኖት ነጻነትን ለማስከበር የተጣለበትን ዓለም አቀፋዊና ብሔራዊ ግደታ በአግባቡ ባለመወጣቱም ችግሩ በእጅጉ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል፡፡

መሰል ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መምጣታቸውም ኢሰመጉን ያሳስበዋል፤ ጥቃቶቹንም ያወግዛል፡፡ ይህን መሰሉ ድርጊት በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና ያገኘውን የሃይማኖት፣ የእምነትና የአመለካከት ነጻነት የሚጻረር ከመሆኑ በላይ በወንጀል ሕጉ ከባድ ቅጣት የሚያስከትል የወንጀል ድርጊት ነው፡፡

ጽንፈኞች በእምነት ተቋማት ላይ የሚፈጽሟቸውን ጥቃቶች የሁሉም እምነት ተከታዮች ሊያወግዟቸው ይገባል፡፡ ንጹሐንን በእምነታቸው ምክንያት መግደል፣ የአምልኮ ሥፍራቸውን ማውደም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚቀሰቅሰው ቁጣ በቀላሉ የሚበርድ አይሆንም፡፡ ሕዝብን በሕዝብ ላይ በማነሣሣት የበቀል እርምጃዎች በስፋት እንዲፈጸሙ ይጋብዛል፡፡ በእምነት ተቋማት ላይ የሚፈጸም ጥቃት ራሱን እየደገመ የሚቀጥል፣ ፈጻሚዎቹን ሳይቀር የሚያጠፋ መጥፎ ዑደት በመሆኑ በሃይማኖት ስም የሚፈጸሙ የጽንፈኞች ጥቃቶችን መንግሥት በአስቸኳይ ማስቆም፤ በሌሎች ሥፍራዎችም እንዳይደገሙ የመከላከል ኃላፊነቱን እንዲወጣ፣ እስካሁን የተፈጸሙ ድርጊቶችን አጣርቶ ፈጻሚዎችንና አስፈጻሚዎችን ለሕግ እንዲያቀርብ ኢሰመጉ ያሳስባል፡፡

በሞጣ ከተማ ከተፈጸመው የእምነት ተቋማትን የማቃጠል ድርጊት ጋር በተያያዘ የአማራ ክልል ፖሊስ ይህ መግለጫ እስከሚጠናቀርበት ጊዜ ድረስ 35 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ መጀመሩ ታውቋል፡፡ ተጠርጣሪዎችን ለሕግ ማቅረብ መጀመሩ ተገቢ ቢሆንም ተመሳሳይ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ በፌደራልና በክልል ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት አካላት አስፈላጊውን የመከላከል ሥራ በማከናወን ዜጎችንና የእምነት ተቋማትን ከጥቃት የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

እንዲሁም፤ የሃይማኖት ተቋማት በተከታዮቻቸው ዘንድ የሚስተዋሉ የጽንፈኛነት አዝማሚያዎችን በማውገዝና ከጥፋት መንገድ በመመለስ የማኅበረሰብ መሪነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ፣

ምዕመናንም በተለያዩ ሚዲያ እየተሠራጩ የሚገኙትንና ሕዝብን ለግጭትና ለጥቃት የሚያነሣሡ ንግግሮችና የሐሰተኛ መረጃ ከመፈብረክና ሳያመዛዝኑ ከማሠራጨት በመቆጠብ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *