Featured image source: Murdock and Modern African Conflict –
የብሔር ማንነትን መሠረት አድርጎ ከ27 ዓመታት በፊት የተመሠረተው የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት፣ ለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ያጎናፀፈና የዘመናት ጭቆናን ያስቀረ እንደሆነ በርካቶች ያምኑበታል፡፡
ይሁን እንጂ የብሔረሰቦችን ማንነት ማክበርና ማስከበር ተገቢ ቢሆንም፣ በብሔር ማንነት ላይ የሚቆም ፌዴራላዊ የመንግሥት ሥርዓትን መመሥረት፣ ብሔርተኝነትን በማጠናከር በብሔረሰቦች መካከል ጤናማ ያልሆነ ከፍተኛ ፉክክርን ብሎም ግጭቶችን በመቀስቀስ፣ አገራዊ አንድነትን ሊያናጋና አገሪቱን ሊበታትናት እንደሚችል በርካታ የውጭና የአገር ውስጥ ምሁራን ሥርዓቱ ከተጠነሰሰበት ወቅት አንስቶ እስካሁን ሥጋታቸውን እያነሱበት ይገኛሉ፡፡
ያም ሆነ ማንነትን መሠረት ያደረገው የፌዴራሊዝም ሥርዓት ሕገ መንግሥታዊ ድጋፍ አግኝቶ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ የተቆጠረ ሲሆን፣ በትግበራ ሒደቱም ከላይ ተጠቀሱት ሁለቱም አዎንታዊና አሉታዊ ጎኖች ተንፀባርቀዋል፡፡
በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አሉታዊ ጎኖቹ በእጅጉ አመዝነው መላ አገሪቱን እየፈተናት ይገኛል፡፡ አሉታዊ ጎኖቹ አሁን ላይ ጎልተው የወጡ ይምሰል እንጂ ውስጥ ውስጡን ሲብላሉ መቆታቸውን ሪፖርተር ያነጋገራቸው አስተያያት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ አገሪቱን እያስተዳደረ ያለው የፌዴራሊዝም ሥርዓት ፈጣሪ ኢሕአዴግ የሥርዓቱ መዋቅርን ወይም አካላዊ ቅርፅን ይዘርጋ እንጂ፣ የትግበራ ሒደቱ በጠንካራ የኢሕአዴግ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት (Democratic Centralism) ተጠፍንጎ በመፈጸሙ፣ ላለፉት 20 ዓመታት ችግሮች ያልነበሩ እንዳስመሰለው ይናገራሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚታዩት ግጭቶችም ሆኑ ጥያቄዎች ከሞላ ጎደል ጠንካራ የነበረው የኢሕአዴግ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ሲበተን፣ መውጫ ያገኙ የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ እውነተኛ ውጤቶች ስለመሆናቸው ይገልጻሉ፡፡
በትግበራ ላይ ያለው የፌዴራሊዝም ሥርዓት የብሔር ማንነትን ተከትሎ ዘጠኝ ክልላዊ የመንግሥት አስተዳደሮችንና ሁለት የከተማ አስተዳደሮችን አዋቅሮ ያልተማከለ መንግሥታዊ ሥርዓትን ያቋቋመ ቢሆንም፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ግን ከማንነት መሠረቱ አፈንግጦ፣ በመልክዓ ምድራዊ የአደረጃጀት ሥልት 56 ብሔር ብሔረሰቦችን በአንድ ክልላዊ መንግሥት መዋቅር ውስጥ ከ20 በሚበልጡ የዞን መዋቅሮች እንዲተዳደሩ አድርጓል፡፡
ከደቡብ ክልል በተጨማሪም የተወሰኑ የክልል መንግሥታት ውስጥ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ያገኙ ብሔረሰቦች በዞን ተዋቅረው ይገኛሉ፡፡ ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ለብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚሰጠው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት የብሔር ብሔረሰቦች መብት ጥግ ድረስ እንደሆነ፣ ለዚህም ሲባል ሁለት ዓይነት የመንግሥት አመሠራረት መብቶችን ያጎናፅፋል፡፡
ይኸውም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 ሥር በተደነገገው መሠረት፣ ብሔር ብሔረሰቦች አባል ከነበሩበት ክልላዊ መንግሥት በመውጣት የራስን ክልል የመመሥረት፣ በአንቀጽ 39 የክልል መንግሥታት በፈለጉ ጊዜ ከፌዴራላዊ ሥርዓት የመገንጠልና የራሳቸውን ሉዓላዊ አገር መመሥረት እንደሚችሉ የሚደነግጉት መብቶች ናቸው፡፡
የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 አራት ንዑስ አንቀጾች ያሉት ሲሆን፣ ንዑስ አንቀጽ ሁለትና ሦስት ለብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ስለመመሥረት መብት የተደነገጉ ናቸው፡፡ በንዑስ አንቀጽ ሁለት የተዘረዘሩት በዘጠኝ ‹‹ክልሎች ውስጥ የተካተቱት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች በማንኛውም ጊዜ የየራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት አላቸው፤›› የሚል ሲሆን፣ ንዑስ አንቀጽ ሦስት ደግሞ ይህ መብት ሥራ ላይ የሚውልባቸውን ሒደቶች ያትታል፡፡
በዚህም መሠረት ሕገ መንግሥቱ፣ ‹‹የማንኛውም ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ የራሱን ክልል የመመሥረት መብት ሥራ ላይ የሚውለው የክልል መመሥረት ጥያቄው በብሔሩ፣ በብሔረሰቡ፣ ወይም በሕዝቡ ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ተቀባይነት ማግኘቱ ሲረጋገጥና ጥያቄው በጽሑፍ ለክልሉ ምክር ቤት ሲቀርብ፣ ጥያቄው የቀረበለት የክልል ምክር ቤት ጥያቄው በደረሰው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለጠየቀው ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ወይም ሕዝብ ሕዝበ ውሳኔ ሲያደራጅ፣ ክልል የመመሥረት ጥያቄው በብሔሩ፣ በብሔረሰቡ፣ ወይም ሕዝቡ ሕዝበ ውሳኔ በአብላጫ ድምፅ ሲደገፍ፣ የክልሉ ምክር ቤት ሥልጣኑን ለጠየቀው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ሲያስረክብና በሕዝበ ውሳኔ የሚፈጠረው አዲስ ክልል ጥያቄ ማቅረብ ሳያስፈልገው በቀጥታ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አባል ሲሆን ነው፤›› ይላል፡፡
ማንነትን መሠረት ባደረገው በዚህ የፌዴራል ሥርዓት የመጀመርያዎቹ ዓመታት ትግበራ ወቅት ከፌዴራላዊ ሥርዓት በመወጣት ሉዓላዊ አገር የመመሥረት ፍላጎት የታየባቸው ንቅናቄዎች ተስተውለው የነበረ ቢሆንም፣ በጊዜ ሒደት ደብዝዘው ይታያሉ፡፡ በተቃራኒው ጠንካራ በነበረው የኢሕአዴግ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ታፍነው የከረሙ ከክልል መንግሥት የመውጣትና የራስን ክልላዊ መንግሥት የመመሥረት ፍላጎቶች፣ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በዋናነትም በደቡብ ክልል ውስጥ በሚገኙ ብሔረሰቦች በመነሳት ላይ ይገኛሉ፡፡
በደቡብ ክልል ውስጥ ከሚተዳደሩ ብሔረሰቦች መካከል ከክልሉ ምሥረታ አንስቶ ራሱን የክልል አደረጃጀት እንዲኖረው ሲጠይቅ የነበረው የሲዳማ ብሔረሰብ፣ ከረዥም ዓመታት ትግል በኋላ በሐምሌ ወር 2010 ዓ.ም. በዞኑ ምክር ቤት የክልልነት ጥያቄውን አፅድቆ ለደቡብ ክልል ምክር ቤት አቅርቧል፡፡
ጥያቄው በኅዳር ወር 2011 ዓ.ም. የቀረበለት የደቡብ ክልል ምክር ቤትም ጥያቄው በሕገ መንግሥቱ መሠረት የቀረበ መሆኑን አረጋግጦ፣ ጥያቄውን ለመመለስ ሕዝበ ውሳኔ እንዲዘጋጅለት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አቅርቧል፡፡
ብሔረሰቡ ጥያቄውን ለክልሉ ምክር ቤት ባቀረበ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ መካሄድ እንዳለበት ሕገ መንግሥቱ የሚደነግግ ቢሆንም፣ ብሔረሰቡ እስካሁን ሕዝበ ውሳኔ ለማዘጋጀት የሚደረግ እንቅስቃሴ ባለማስተዋሉና በራሱ አቆጣጠር ጥያቄውን ካቀረበ አንድ ዓመት እንደሞላው በመገንዘብ የክልል ምሥረታውን በራሱ መንገድ ለማከናወን እንቅስቃሴ ውስጥ መግባቱ፣ በሐዋሳ ከተማና በአካባቢው የፖለቲካ ውጥረት ተቀስቅሷል፡፡
በተጨማሪም የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ሌላ የክልልነት ጥያቄ ማዕበል በክልሉ ቀስቅሷል፡፡ የሲዳማ አጎራባች የሆነውን የወላይታ ብሔረሰብን ጨምሮ ከአሥር በላይ የብሔረሰብ ዞኖች ከደቡብ ክልል ለመለየትና የራሳቸውን ክልል ለመመሥረት ውሳኔዎቻቸውን በየዞን ምክር ቤቶቻቸው አፅድቀው፣ ቀጣይ እንቅስቃሴያቸውን በማንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡
የደቡብ ክልል አደረጃጀት ወደዚህ ደረጃ ሊያመራ እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ነው የሚሉት ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያ፣ መፍትሔው ጥናትን መሠረት አድርጎ የክልል አደረጃጀቱን መቀየር አሊያም የኃይል ፖለቲካን መጠቀም ነው ብለው፣ ነገር ግን የትኛውም ዓይነት የኃይል አማራጭ ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ እንደማይችል ይገልጻሉ፡፡
የክልሎች መብዛት የአገር አንድነትንም ሆነ የፌዴራል መንግሥትን እንደሚያዳክም ከናይጄሪያ የፌዴራሊዝም ሥርዓት መረዳት እንደሚቻል የሚገልጹት እኚሁ ባለሙያ፣ ሚዛኑን የጠበቀ አዲስ አደረጃጀት መፍጠር ብቸኛውና ጤነኛ መፍትሔ እንደሆነ ያምናሉ፡፡
እየተነሱ ያሉትን ከክልልነት የመውጣትና የራስን ክልል የማቋቋም ጥያቄዎችን የበለጠ አስቸጋሪ የሚያደርገው፣ የነባሩን ክልል ሀብት እንዴት መከፋፈል ይቻላል የሚለው እንደሚሆን ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
የብሔር ማንነትን መሠረት ያደረገው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የራሳቸውን ክልል መሥርተው የፌዴራል መንግሥቱ አባል መሆን እንደሚችሉ ሲደነግግ፣ ብሔረሰቦች በመጀመርያ ከተዋቀሩበት ክልል ወጥተው የራሳቸውን ክልል የመመሥረት፣ እንዲሁም ክልሎች ከፌዴሬሽኑ መገንጠል እንደሚችሉ ያስቀምጣል፡፡
ከላይ የተገለጹት መብቶች ውሳኔ የሚያገኙበትን ሥርዓት ሕገ መንግሥቱ የሚደነግግ ሆኖ ሳለ፣ ይህ መብት ተቀባይነት ሲያገኝ በየክልሎች ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን የሚመለከቱ ሀብቶች መብቱን ባገኘው ብሔረሰብና በቀሪው የክልል ወይም የፌዴሬሽኑ አባላት መካከል የሚፈጸምበትን ሥርዓት አለማስቀመጡን፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፌዴራሊዝም ምሁር ያውሳሉ፡፡
ከክልል ተነጥሎ ክልል የመመሥረት መብትን በተመለከተ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 ላይ የተቀመጠው ‹‹ክልል የመመሥረት ጥያቄው በብሔሩ፣ በብሔረሰቡ፣ ወይም በሕዝቡ ሕዝበ ውሳኔ በአብላጫ ድምፅ ሲደገፍ፣ የክልሉ ምክር ቤት ሥልጣኑን ለጠየቀው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ሲያስረክብና በሕዝበ ውሳኔ የሚፈጠረው አዲስ ክልል ጥያቄ ማቅረብ ሳያስፈልገው በቀጥታ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አባል ሲሆን ነው፤›› ይላል፡፡
የመገንጠል ጥያቄ ተቀባይነት ሲያገኝም በሚገነጠለው ክልልና በቀሪው የፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች መካከል የሀብት ክፍፍል የሚፈጸምበትን የሕግ አግባብ ሕገ መንግሥቱ እንደማያስቀምጥ ምሁሩ ይገልጻሉ፡፡
ሕገ መንግሥቱ ይህንን ጉድለት ይዞ መቀመጡ የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ አንድ ትልቅ ጉዱለት ስለመሆኑ የሚናገሩት እኝሁ ምሁር፣ ከመገንጠልና አገር ከመመሥረት ጋር ተያይዞ የሚነሳን የሀብት ክፍፍል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.ኤ.አ. በ1883 ባወጣው ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን መሠረት መፈጸም እንደሚቻል ያስረዳሉ፡፡
በዚህ ኮንቬንሽን መሠረት ከአንድ ሉዓላዊ አገር ተገንጥሎ የሚመሠረት አገር በሚኖርበት ጊዜ፣ ከመገንጠሉ በፊት ተገንጣዩ ግዛት ውስጥ የሚገኙ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ነባሩ አገር አዲስ ለሚመሠርተው አገር ማስተላፍ እንዳለበት ግዴታ እንዳለበት ምሁሩ ያስረዳሉ፡፡
በተመሳሳይ የሚገነጠለው የአካባቢ አስተዳደር ከመገንጠሉ በፊት ይጠቀምባቸው የነበሩ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች አዲስ ለሚመሠረተው ወይም ለሚገነጠለው አገር እንደሚተላለፉ የሚደነግግ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ከደቡብ ክልል የመውጣት ጥያቄን ላነሳው የሲዳማ ዞን የዚህን ኮንቬንሽን መርህ መሠረት ያደረገ የሀብት ክፍፍል ሥርዓትን ማበጀት የሚቻል ቢሆንም፣ በሌሎች ብሔረሰቦች አስተዋጽኦ እንደተገነባችው ሐዋሳ ያሉ ከተሞች በሚኖሩበት ጊዜ አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡
የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ በሕዝበ ውሳኔ ለመመለስ ዝግጅት እያደረገ መሆኑንና በቀጣዮቹ አምስት ወራት ውስጥ ሕዝበ ውሳኔውን ሊያካሄድ እንደሚችል የገለጸው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ፣ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ በሌሎች አካላት ሊፈጸሙ ይገባቸዋል ያላቸውን ጉዳዮች ይፋ አድርጓል፡፡
ቦርዱ እንዳስታወቀው የሕዝበ ውሳኔ ሒደቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም መካከል አንዱ የሆነው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ከክልሉ መንግሥትና ከዞኑ መስተዳድር ጋር በመመካከር፣ በአሁኑ ወቅት የክልሉም የዞኑም አስተዳደር ዋና ከተማ ሆና የምታገለግለው የሐዋሳ ከተማ የሕዝበ ውሳኔው ውጤት የሲዳማን ክልል መሆን የሚያረጋግጥ ቢሆን፣ በከተማዋ ላይ ሁለቱ አካላት የሚኖራቸውን መብትና ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚነሱ የሀብት ክፍፍል ጥያቄዎች የሚያስተናግዱበትን አሠራር ማዘጋጀት እንደሚገባና ይህንንም ለቦርዱ እንዲያሳውቁ ጠይቋል፡፡
በሌላ በኩልም የደቡብ ክልል ምክር ቤት በሲዳማ ዞን የሚኖሩ የተለያዩ የሌሎች ብሔር ብሔረሰብ አባላት ከሕዝበ ውሳኔው በኋላ የሚኖራቸውን ሕጋዊ የመብቶች ጥበቃ አስመልክቶ ግልጽ አስተዳደራዊና ሕጋዊ ማዕቀፍ እንዲያዘጋጅና ለቦርዱ እንዲያሳውቅ ምርጫ ቦርድ የወሰነ መሆኑን፣ ከዚህም በተጨማሪ የሚመለከታቸው አካላት ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ምላሽ እስከ ሐምሌ 19 ቀን 2011 ዓ.ም. በጽሑፍ እንዲያሳውቁ ቦርዱ አስታውቋል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ በአገሪቱ ተመሳሳይ ክስተት አጋጥሞ ስለማይታወቅና የሀብት ክፍፍል ሕግ እስከ ዛሬ አለመሠራቱን ገልጸው፣ ይህንን በተመለከተ ጥናት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ለማበጀት እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
Source: Ethiopian Reporter