ኢህአዴግን ከግንባርነት ወደ አንድ ህብረ ብሄራዊ ውህድ ፓርቲ የማሸጋገር ጉዳይ በ1996 ዓ.ም ከተካሄደው 5ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ጀምሮ በተከታታይ በተካሄዱት የድርጅቱ ጉባዔዎችና የተለያዩ ድርጅታዊ መድረኮች ሲነሳ የቆየ ጥያቄ እንደሆነ ይታወቃል። በሁሉም የኢህአዴግ መድረኮች በውህደቱ አስፈላጊነት ላይ ስምምነት እየተያዘበት የሄደ ሲሆን በየጉባዔዎቹ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ውህደቱን በጥናት ላይ ተመስርቶ ለመፈፀም የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ቆይተዋል። ይልቁንም በቅርብ ጊዜያት በተካሄዱ ጉባዔዎች ይነሳ የነበረው ቁልፍ ችግር በአፈፃፀሙ ላይ የታየው ከፍተኛ መጓተት ነበር። በተለይ ባለፈው አመት በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው 11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ የጥናት ስራው በቶሎ ተጠናቆ የኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ውህደት ፈጥረው አንድ ጠንካራ ሀገራዊ ፓርቲ እንዲፈጠር ውሳኔ ተላልፏል። በሂደቱ የአጋር ድርጅቶችም ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ ተቀምጧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የውህደቱ አቀንቃኝ ሆኖ ውህደቱን ሲመራ የነበረው ህወሃት በአሁኑ ወቅት ውህደቱን በተመለከተ አሉታዊ ገፅታ ያላቸው ተደጋጋሚ መግለጫዎችን በማውጣት ላይ ይገኛል። ምንም እንኳን ጉዳዩ በሂደት ላይ ያለና ያልተቋጨ በመሆኑ በዚህ ወቅት መግለጫ መስጠትም ሆነ በሚወጡ የተሳሳቱ መግለጫዎች ላይ መልስ መስጠት አስፈላጊ አይደለም በሚል እምነት ጉዳዩን በዝምታ ለማለፍ የተሞከረ ቢሆንም የተሳሳቱ መረጃዎች ተደጋግመው ሲወጡ ችላ ማለት ደግሞ ህዝቡ ውስጥ መደናገርን ሊፈጥር የሚችል መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ለህዝቡ ጠቅለል ያለ መረጃ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
ህወሃት እንደ ድርጅትም ሆነ በአንዳንድ አመራሮቹ በተደጋጋሚ የሚሰጣቸው መግለጫዎች በሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች ስህተት ሆነው እናገኛቸዋለን። የመጀመሪያው ስህተት ከድርጅት አሰራርና ዲስፒሊን ጋር የተያያዘ ነው። በድርጅቱ አሰራርና ህገ ደንብ መሰረት የግንባሩ አባል ድርጅቶች በማንኛውም አጀንዳ ላይ ውይይትና ክርክር ካደረጉ በኋላ የመሰላቸውን አቋም መያዝና በአቋማቸውም ላይ ተመስርተው ክርክራቸውን መቀጠል የተለመደ ነው።
በ2011 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው 11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ህወሃትን ጨምሮ ሌሎች አጋርና አባል ድርጅቶች ጥናቱ በአፋጣኝ ተጠናቆ ወደ ተግባር እንዲገባ ያለልዩነት ወስነዋል። በውሳኔው መሰረት ተጠንቶ በቀረበው ሃሳብ ላይ ደግሞ ሁሉም ድርጅቶች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፤ ጥናቱ እንዲዳብርም የበኩላቸውን ተሳትፎ አድርገዋል። በአሁኑ ሰዓት እየተካሄዱ ያሉ ውይይቶችም ከውሳኔ በፊት ጥናቱን የሚያዳብሩ ሃሳቦችን የማሰባሰብ ሲሆኑ በዚህ ደረጃ በተካሄዱ የአመራር ውይይቶች ህወሃትም ሆነ ሌሎች አባልና አጋር ድርጅቶች ተሳትፈዋል፤ አስተያየታቸውንም ሰጥተዋል። የተሰጡት አስተያየቶች ጥናቱን ለማዳበር ወይም ያልታዩ ጉዳዮች በአግባቡ እንዲዳሰሱ ለማድረግ እንጂ የውሳኔ ወይም የአቋም ጉዳይ ሆነው የሚቀርቡ አልነበሩም። በመሆኑም ይህ አጀንዳ ገና በጥናት ውጤቱ ላይ ውሳኔ ያገኘበት ደረጃ ላይ አልደረሰም። የመጨረሻ የውህደት ውሳኔም አሰራሩን ጠብቆ ወደፊት የሚታይ ይሆናል። ጉዳዩ በዚህ ደረጃ ባለበትና የመጨረሻ ውሳኔ ተሰጥቶ የሁሉም ድርጅቶች አቋም ባልተገለፀበት ሁኔታ ህወሃት አስቀድሞ ለብቻው በተደጋጋሚ መግለጫ መስጠቱ የድርጅት አሰራርና ዲሲፒሊንን የጣሰ እንዲሁም ወቅቱን ያልጠበቀ በመሆኑ መታረም ያለበት ነው።
“Ethiopia Ruling Coalition To Shake Up Decision-Making Structures “– BNN Bloomberg
የመግለጫው ሁለተኛው ስህተት ደግሞ ይዘቱ ነው። ህወሃት በተለያዩ መግለጫዎቹ ደጋግሞ የሚያነሳው ውህደቱ አሃዳዊ መንግስት ለመመስረት የታቀደ አስመስሎ ማቅረብ ነው። ፓርቲው ወደ አንድ ወጥ ፓርቲ በሚቀየርበት ወቅት ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብታቸው እንደሚገፈፍና ፌዴራላዊ ስርዓቱ ፈርሶ አሃዳዊ ስርዓት እንደሚመስረት አድርጎ የሚያቀርበው ሃሳብ ለማደናገሪያ ካልሆነ በስተቀር ለመከራከሪያ የሚሆን ተጨባጭ ነገር የለውም። በመሰረቱ የአንድ ሀገር የመንግስት አወቃቀር የሚወሰነው በሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎና በኢትዮጵያ ህዝብ ውሳኔ እንጂ በአንድ ፓርቲ ፍላጎት ብቻ ሊሆን አይገባውም። ስለዚህ የኢህአዴግ ውህደት ለብቻው የአገሪቱን የፌዴራል ስርዓት የሚያፈርስ አድርጎ ማቅረብ ውሃ የሚቋጥር መከራከሪያ አይደለም።