FivePoliticalParties
Press Release

አስቸኳይ አገር አድን ውይይት እንዲደረግ በድጋሚ ስለመጠየቅ፣

ግልጽ ደብዳቤ!

ለክብርት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ

ለተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ

ለክቡር አቶ ቴዎድሮስ ምህረት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት

 

አዲስ አበባ

ጉዳዩ፦ አስቸኳይ አገር አድን ውይይት እንዲደረግ በድጋሚ ስለመጠየቅ፣

እናት ፓርቲ፣ መኢአድ፣ ኢህአፓ፣ ዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄ እና አንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሐምሌ ፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ባወጣነው የጋራ መግለጫ በአገራችን እየተስተዋለ ያለውን ውስብስብ ችግር ለመፍታትና የአገራችንን ህልውና ለመታደግ አስቸኳይ የአገር አድን እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ ያደረግን ሲሆን ይህንኑ የሚገልጽ ደብዳቤ በአድራሻ ማስገባታችን ይታወሳል።

በዚህም መግለጫ እና ደብዳቤ የሰላሳ ሁለት ዓመታት እኩይ ዘር ፍሬ ለሆነውና ዛሬ ላይ አገራችን ለተደቀነባት ሁለንተናዊ ችግር ብቸኛ መፍትሄሔ በምትመሩት መንግሥት፣ ነፍጥ አንስተዉ ዉጊያ ላይ በሚገኙ ኃይሎች እና ሕጋዊ እውቅና ኖሯቸው በሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አስቸኳይ የአገር አድን ውይይት ማድረግ መሆኑን በመግለጽ ይኸው አገር አድን ውይይት አንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ እንዲጀመር መጠየቃችን ይታወሳል።

ይሁን እንጂ ጥያቄያችንን ካቀረብን ከሶስት ሳምንታት በላይ የተቆጠረ ቢሆንም አገርን ከከፋው አደጋ ለመታደግ ያለመውን ማሳሰቢያችንን ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት ይልቁን እልህና ፉክክር የተላበሰ በሚመስል መልኩ ግጭቱ እየሰፋ መጥቶ መላው የአማራ ክልል ወደ ጦር አውድማነት እየተለወጠ መሆኑን እየተመለከትን ነው። በዚህ ጦርነት መሣሪያ ያልታጠቁ ንጹሐን ዜጎችም ሕይወት እያለፈ መሆኑን፤ ብሔራዊ ፈተና የሚፈተኑ ተማሪዎችም ላይ በዚሁ ምክንያት መተጓጎል እንደደረሰባቸው ለመረዳት ችለናል።

አገር ትምህርት መውሰድ ያለባት ከሌላ ሳይሆን የአንድ ሚሊየን ልጆቿን ህይወት ከቀጠፈው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሊሆን እንደሚገባ በማመን አገራችን ላይ ላንዣበበው የከፋ አደጋ ብቸኛ መፍትሄ አስቸኳይ ሁሉን አቀፍ ውይይት መሆኑን ዛሬም አጽንኦት ሰጥተን በደጋሚ ልናሳስብና ዛሬ ነገ ሳይባል መንግሥት ራሱን ዝግጁ አድርጎ በገለልተኛ አገር ውይይት እንዲጀመር አጥብቀን እንጠይቃለን። መንግሥት ድጋሚ ያቀረብነውንና ለአገር ባጠቃላይ እንዲሁም በሥልጣን ላይ ላለው መንግሥት መውጫ መንገድ ሆኖ ሊያገለገል የሚችለውን ይህን የአገር አድን ውይይት ሃሳብ ቸል በማለት በሚወስደው የኃይል እርምጃ እና ይህን ተከትሎ ለሚደርሰው ጉዳት ሙሉ ተጠያቂነት እንደሚወስድ አጽንኦት ሰጥተን እናሳስባለን።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ!

መኢአድ፣ ኢህአፓ፣ እናት ፓርቲ፣ የዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄ እና አንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *