Opinion

መሆን የነበረበት የአማራን ህዝብ ለቀቅ ወያኔ ጠበቅ ማድረግ ነበር !!

August 6, 2023

Andargachew Tsigeአንዳርጋቸው ጽጌ

በትናንትናው እለት የፌደራል መንግስቱ፣ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ጥያቄ አቀረቡልኝ በሚል የአማራን ክልል “በአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ” ስር ማስገባቱን አሳውቆናል። ይህን ዕዝ ለማቋቋም የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6/2015፣ የህዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የወጣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ” አጽድቋል። የዚህ ሰነድ ክፍል ሶስት “በአስቸኳይ ጊዜ የሚወሰዱ እርምጃዎችና የተከለከሉ ተግባራት” በሚል ርእስ፣ በአንቀጽ 5 ስር “በአስቸኳይ ጊዜ የሚወሰዱ እርምጃዎች” በማለት በተራ ቁጥር 5 እና 6 የሚከተሉትን ይደነግጋል።

“5) በሃገረ መንግስቱና በህገመንግስታዊ ሥርዓቱ ላይ የሚቃጡ ወንጀሎችን እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመጣስ እና አፈጻጸሙን የማደናቀፍ ወንጀልን መፈጸሙ፣ መሞከሩ፣ ለመፈጸም በዝግጅት ላይ መሆኑ የተጠረጠረ ማናቸውም ሰው ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ በቁጥጥር ስር በማድረግ ማቆየት፣

6) ወንጀል እንደተፈጸመባቸው ወይም ሊፈጸምባቸው እንደሚችል የተጠረጠሩ እቃዎችን ለመያዝ ሲባል ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ በየትኛውም ጊዜ ማናቸውንም ስፍራ እና መጓጓዣ ለመበርበር፣ …………. ስልጣን አለው” ይላል።

በአማራ ክልል እየሆነ ባለው እጅግ አሳዛኝ ሁኔታ ላይ የዛሬውን የግል ምልከታዬን ሳቀርብ ከላይ በአንቀጽ 5 እና 6 ገደብ የሌለው ስልጣን የተሰጣቸው አካላት በእኔም ይሁን ከእኔ ጋር ቅርበት ባላቸው አካላት ላይ ማንኛውንም እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ እያወቅሁ ነው። በሌሎች ግለሰቦች ላይ እንዲህ አይነቱ እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነ መረጃው እየደረሰኝም ነው። በእንዲህ አይነቱ ወቅት ዝምታን ያልመረጥኩት፣ በመንግስት ወንጀለኛ ሆኖ ከመታየት ይልቅ በራሴ ህሊና ወንጀለኛ ሆኖ መታየት የበለጠ የሚያስጨንቀኝ ሰው በመሆኔ ብቻ ነው።

ይህ እንዳለ ሆኖ፣ የአማራ ክልል “በአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ ማእከላዊ እዝ” በወደቀበት እለት አንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናት፣ በተለይ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሚያውቋቸው የትግራይ የመረጃ ምንጮች፣ ወያኔ በ24 አርሚዎች፣ በእየአንዳንዱ አርሚ 11500 ታዋጊ፣ በጥቅሉ 276000፣ ጤንነቱና ብቃቱ የተረጋገጠ የታጠቀ ሰራዊት ለውጊያ ያዘጋጀ መሆኑን መረጃ ደርሶኛል። ይህን አይነቱን እና ሌሎችንም ከዚህ የላቁ በጣም ወሳኝ መረጃዎች ጦርነቱ ከመቆሙ ከስድስት ወራት በፊት ጀምሮ እንዴት ወደ እኔ መፍሰስ እንደጀመሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ጥቂት ጀነራሎቹ ያውቃሉ።

በትናንትናው እለት ያገኘሁት መረጃ፣ ከእነዛው አንድም ቀን የተሳሳተ መረጃ ልከው ከማያውቁት የህወሃት ምንጮች የመጣ ነው። የትናንቱ መረጃ ግን እስከዛሬ ሲደርሱን እንደነበሩ መረጃዎች ሚስጥራዊ መረጃ ነው ማለት አንችልም። ሚስጥር አለመሆኑ ማወቅ የቻልነው የኢትዮጵያ መንግስት እውቅና ከሰጣቸው የትግራይ ጊዚያዊ መንግስት የወያኔ ባለስልጣናት አንደበት ነው።

ከጥቂት ቀናት በፊት ጌታቸው ረዳ፣ ዴንቨር ኮለራዶ ላይ ከ200 ሽህ በላይ ለውጊያ የተዘጋጀ ሰራዊት እንዳለው ተናግሯል። በዚህ ሰራዊት የተማመነው ጄነራል ጻድቃን “የማእከላዊ መንግስቱ በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ቃል በገባልን መሰረት የትግራይን ግዛቶች ማለትም ወልቃይትን እና ራያን የማይመልስን ከሆነ በጉልበት እናስመልሳለን” ብሎ እዛው አሜሪካን ውስጥ በተዘጋጀ ስብሰባ ላይ ተናግሯል። ጻድቃን “ቃል ተገብቶልናል” ስለሚለው ጉዳይም ይሁን ስለጉልበት መጠቀሙ የሚናገራቸው ነገሮች ዝም ብሎ እንዳልሆነ ከህወሃት ከራሱ ስናገኛቸው የነበሩ በቂ መረጃዎች እንዳሉ የመንግስት ባለስልጣናት ያውቁታል።

እነዚህ ሁለት ግለሰቦች ከየትኛውም የወያኔ አመራር በተለየ በጦርነቱ ወቅት “ከአማራ ህዝብ ጋር ሂሳብ እናወራርዳለን” በማለት በአደባባይ የተናገሩ ፣ የአማራ ህዝብ የተጨፈጨፈበትን፣ ሰው ብቻ ሳይሆን እንስሳቱ በጥይት የተቆሉበትን፣ ክልሉ ከስልጣኔ ርቆ ወደ ድንጋይ ዘመን እንዲመለስ ተደርጎ የመሰረተ ልማት ግንባታዎቹ፣ የህዝብ የአገልግሎት ተቋማቱ እንዲወድሙ የተደረገበትን፣ የፕሮፓጋንዳና የጦር እስትራተጂ የነደፉና ያስፈጸሙ ናቸው።

የሚገርመው ግን የታሪክ ቧልት የሚል ትርጓሜ ሊያሰጠው በሚችል ደረጃ፣ ጌታቸውና ጻድቃን፣ የአንደኛ ደረጃ የአውሮፕላን ቲኬት ተቆርጦላቸው፣ ሲኦል ድረስ ወርደንም ቢሆን እናወድመዋለን ባሉት የኢትዮጵያ መንግስት፣ የቪአይፒ እንክብካቤ ተደርጎላቸው ወደ አሜሪካ ተጉዘው፣ በከፍተኛ እብሪትና መንደላቀቅ ስለሰራዊታቸው አቅምና ስለቀጣይ ጦርነት፣ ስለትግራይ አሸናፊነት በአሜሪካን ከተሞች ሲደሰኩሩ፣ ሲዘፍኑ፣ እስክስታ ሲወርዱ፣ ከሀገር ያሸሹትን ሃብት ቦታ ቦታ ሲያስይዙ ከአሜሪካን መንግስት ጌቶቻቸውና እመቤቶቻቸው ጋር ሴራ ሲሸርቡ ከርመው በክብር ወደ መቀሌ ተመልሰዋል።

በሌላ በኩል እነዚህ ግለሰቦች በአሸናፊነት ስሜት መናገሻ ከተማቸው በገቡ በቀናት ልዩነት፣ የእነዚህን እብሪተኞች ሃገር የማፍረስ ተልእኮ በመመከት፣ በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት መንበር በማጽናት፣ በተኛበት ለተጨፈጨፈው የሃገር መከላከያ ሰራዊት አለኝታ በመሆን፣ በንብረቱ፣ በደሙና በአጥንቱ በህይወቱ መስዋእትነት የከፈለው የአማራ ህዝብ በወታደራዊ አገዛዝ ስር እንዲወድቅ ተፈርዶበታል።

የአማራ ህዝብ፣ የአማራ ሚሊሽያ፣የአማራ ልዩ ሃይል፣ የአማራ ፋኖ ከወያኔ ጋር በተደረገው ጦርነት የከፈለው መስዋትነት ያነሰው ይመስል፣ ክልሉ ወደ ሁከትና ትርምስ ከዛም አልፎ ወደሌላ ዙር እልቂትና ውድመት እንዲያመራ ተፈርዶበታል። ተፈርዶበታል የምለው ያለምክንያት አይደለም።

ባለፉት አምስት ወራት በአማራ ክልል ውስጥ የተቀሰቀሰው ህዝባዊ መከፋትና የተከተለው ቀውስ እንዴት መከሰት እንደቻለ ዛሬ የፌደራሉ መንግስት ጣልቃ ይግባልን የሚል ጥያቄ ያቀረቡትም ሆነ ጥያቄውን ተቀብያለሁ በማለት ጦሩን ያዘመተው የክልሉና የፌደራል መንግስት ባለስልጣናት ያውቁታል።

እውነቱን እንነጋገር ከተባለ የፌደራል መንግስቱ የአማራን ልዩ ሃይል ለማፍረስ ውሳኔ እስከአስተላለፈበት እለትና ይህን ውሳኔ ተፈጸሚ ለማድረግ የክልሉ ባለስልጣናት “ለምን” የሚል ጥያቄ ሳያነሱ እስከተንቀሳቀሱበት እለት ድረስ ከአብዛኛዎቹ የሃገሪቱ ክልሎች በላይ ይህ ክልል ሰላም የሰፈነበት፣ ማንም ኢትዮጵያዊና የውጭ ዜጋ ያለምንም ስጋት የሚንቀሳቀስበት ክልል ነበር። ህዝቡ መገፋት፣ መገደልና መደህየት እያመረቀዟቸው ያሉትን የሩቅና የቅርብ ዘመን በርካታ ቁስሎችን እና ስቃዮችን በጽናት ችሎ፣ የፍትህ፣ የእኩልነትና የሰላም ቀን በኢትዮጵያ ምድር ይሰፍናል በሚል ተስፋ ይኖር የነበረበት ክልል ነበር።

ከዚህ ቀደም “ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ” በሚል ርእስ በጻፍኩት ጽሁፍ ላይ እንደገለጽኩት የአማራ ህዝብ የልዩ ሃይሉን መፍረስ የተቃወመው በመርህ ደረጃ ከፌደራሉ መንግስት ጋር ልዩነት ስላለው አልነበረም። አሁንም ሳንሸፋፈጥ እንነጋገር ከተባለ ከየትኛውም ክልል ህዝብ በላይ የአማራ ህዝብ የልዩ ሃይሎችን መፍረስና ሃገራዊ ወታደራዊ ጉልበት በማእከለዊ መንግስት የመከላከያ እጅ ብቻ እንዲሆን የሚመኝ ህዝብ ነው።

ቀደም ብዬ ርእሱን በጠቀስኩት ጽሁፌ እንደገለጽኩት የአማራ ህዝብ ያንን ውሳኔው የተቃወመው ወያኔ እስከጥርሱ በታጠቀበትና አማራን እወራለሁ ብሎ በሚደነፋበት ወቅት በመሆኑ ነው።

የወልቃይትና የራያን ጥያቄ የአማራን ህዝብ ፍላጎትና ጥቅም ባላከበረ መንገድ መንግስት መልስ ሊሰጥ ነው የሚል ጥርጣሬ በማህበረሰቡ ውስጥ በነገስበት ወቅት መሆኑ ነው።

አማራን በማንነቱ እየለዩ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች እንደከብት የሚያርዱ፣ የሚያፈናቅሉ፣ የሚዘርፉና የሚያፍኑ መንግስታዊና መንግስታዊ ያለሆኑ አካላት በሚርመሰመሱበት ሃገር ውስጥ የሚኖር በመሆኑ ነው።

በሃገር ውስጥና ከሃገር ውጭ ባሉ መደበኛና መደበኛ ያልሆኑ ሚድያዎች አማካኝነት የአማራን ህዝብ ለማያቋርጥ የህልውና አደጋ የሚዳርጉ፣ በአማራ ላይ ያነጣጠሩ የጥላቻ ትርክቶች ተጠናክረው የቀጠሉበት ወቅት በመሆኑ ነው።

የፌደራል መንግስቱና የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት በአማራ ህዝብ ላይ ከፍተኛ ግፍ ለፈጸሙ፣ ወደፊትም ለመፈጸም የሚያስችል ሰራዊትና ትጥቅ ላላቸው፣ ይህን ከማድረግ እንደማይመለሱ ለሚፎክሩ የትግራይ የፖለቲካና ወታደራዊ አመራሮች፣ በሰላም ስም ሽልማት እየሰጡ፣ የትኛውንም ህሊና ያለውን ሰው በሚቀፍ ደረጃ እየተቃቀፉና እየተሳሳቁ በጦርነቱ ባለቀው እና አካል ጉዳተኛ በሆነው የሀገሪቱ ዜጋ የሚያሾፉ ሆነው የታዩበት ሁኔታ በመከሰቱ ነው።

እነዚህን እና ሌሎችም በወቅቱ የዘረዘርኳቸውን የአማራን ህዝብ ለጥርጣሬ የሚዳርጉ በርካታ ጉዳዮች በአንድ ላይ ተደምረው፣ የአማራ ህዝብ ከፍተኛ የህልውና ስጋት እንዲሰማው በመደረጉ፣ የክልሉን ልዩ ሃይል ለማፍረስ የተወሰነው ውሳኔ የሚዋጥለት አልሆነም።

ይህ ልዩ ሃይሉን የማፍረስ ውሳኔ መወሰኑ በአማራ ክልል በተሰማበት እለት በአማራ ክልል አስተዳደር ውስጥ ባሉ፣ ጉዳዩ ባሳሰባቸው የጸጥታና የደህንነት አካላት፣ በራሱ በልዩ ሃይሉና በህዝቡ ውስጥ የቀሰቀሰው ቁጣ ክልሉን ለሚመሩት የብልጽግና ሰዎች ግልጽ እንደነበር በቂ መረጃ አለ። የውሳኔው አደገኛነት የሚያሳዩ በቂ መረጃዎች ለክልሉ መሪዎች እንደደረሳቸውም ይታወቃል።

የፖለቲካ ብስለትና የመወሰን ነጻነት ያለው አመራር ማድረግ የነበረበት በፍጥነት ውሳኔው ተግባራዊ እንዳይሆን፣ ከዛም አልፎ ውሳኔው እንዲከለስ በማድረግ ህዝቡን ማረጋጋት ነበር። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ከልዩ ሃይሉ መካከል ውሳኔውን ተቃውመው ያፈነገጡትን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ታጣቂዎችን ህገወጦች የሚል ታርጋ ተለጥፎባቸው፣ መሳሪያ ለማስወረድ በሚል ሰበብ፣ ያለክልሉ ምክር ቤት ፈቃድ የፌደራል ሰራዊት ወደ ክልሉ እንዲገባ ተደረገ።

የአማራ ህዝብ እንደህዝብ፣ ልዩ ሃይሉ ሚሊሺያውና ፋኖው ከሃገር መከላከያ ሰራዊት ጎን በአንድ ግምባር ተሰልፈው የሃገርን ህልውና ለማስከበር በጋራ እንዳልሞቱና እንዳልቆሰሉ፣ መከላከያውና የአማራ ክልል ህዝብ በጥርጣሬ፣ ከዛም አልፈው በስጋት እንዲተያዩና ደም እንዲቃቡ ተደረገ። ይህ በሀገር ክህደት ደረጃ የሚያስጠይቅ ወንጀል ነው።

ለአማራ ክልል ቀውስ መጠናከርና መባባስ የክልሉና የፈደራል መንግስቱ በርካታ ችፍቻፊ ምክንያቶች ሊያቀረቡ ይችላሉ። ለዚህ የሚሆኑ መረጃዎችን ማሰባስብ እንደማያቅታቸው አውቃለሁ። ይህን ሃቅ እኔ ብቻ ሳልሆን በርካታ ሰዎች የሚክዱት አይሆንም። ሆኖም ግን የትኛውም አይነት ማስረጃና መረጃ በፈለገው ደረጃ ተቀነባብሮ ቢቀርብም ግን ችፍቻፊ ከመሆን የሚዘል አይሆንም።

በአማራ ክልል ለተከሰተው ቀውስ ዋናው እና መሰረታዊ ምክንያት የአማራውን ህዝብ የህልውና ስጋት ከመጤፍ ባለመቁጠር፣ አርቆ አሳቢነት፣ ህዝባዊ ወገንተኛነት የጎደለው ውሳኔ በመንግስት አካላት መወሰኑ እንደሆነ መታመን አለበት። ይህን የምለው ቀውሱን የፈጠረውን ዋንኛውን ምንጭ አድበስብሶ ማለፍ ከችግሩ መውጫ መንገዶቹን በሙሉ የሚዘጋ ስለሚሆን ነው።

በትናንትናው እለት በክልሉ ለተከሰተው ችግር መፍትሄ ይሆናል በሚል የወጣው አዋጅ አሁንም በድጋሚ “ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ” በሚል ርእስ ከዚህ ቀደም ላወጣሁት ጽሁፍ ማጠቃለያ በማድረግ የጻፍኳቸውን ቃላት በድጋሚ እንድጠቅም የሚያስገድደኝ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።

“አሁን በአማራ ክልል ከልዩ ሃይሉ መፍረሰ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ችግር ፣ ወያኔዎች ሲያደርጉ እንደኖሩት፣ የክልሉን መሪዎች በስልጣን እና በጥቅም በመደለል፣ ህዝቡንም ሆነ አንዳንዶቹን ከህዝቡ ጎን ለመቆም የወሰኑትን የአስተዳደርና የጸጥታ አካላት በማስፈራራት፣ ወይም ከእውነታው ጋር በተጣላ የፕሮፓጋንዳ ውርጅብኝና በሌሎችም ዘለቄታዊ መፍትሄ ማምጣት በማይችሉ መንገዶች ሄዶ ለማቃለል የሚደረግ ሙከራ የትም እንደማያደርስ መታወቅ ይኖርበታል።”

በመጨረሻም የሚያዳምጥ ካለ፣ “እንዲህ አይነት ችግር በኢትዮጵያ ውስጥ ሲከሰት የመጀመሪያው አይደለም። የመጨረሻውም ላይሆን ይችላል። እንዲህ አይነት፣ በተለይ ከእውነተኛ የህዝብ ብሶት ጋር የተያያዙ ችግሮች ሲፈጠሩ፣ ችግሮቹን ለመፍታት በተለያዩ ዘመናት ያለፉ መንግስታት ከሄዱበትና ውጤት ካላመጡ አደገኛ አካሄዶች መማር ተሸናፊነትን ሳይሆን ብልህነትን የሚያሳይ ይሆናል።” እላለሁ።

 

አንዳርጋቸው ጽጌ

አዲስ አበባ

ኢትዮጵያ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *