ዶ/ር ዓቢይ አሕመድ
Current Opinion

ግልፅ ደብዳቤ ለኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓቢይ አሕመድ – የዳላስ ቴክሳስ ኢትዮጵያውያን ማሕበረሠብ መድረክ ፅሕፈት ቤት

ግልፅ ደብዳቤ ለኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓቢይ አሕመድ::

አዲስ አበባ:
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር::

በመጋቢት 2018 ማብቂያ በኢሕአዴግ አውራ ፓርቲ ትህነግ የመዝቀጥ አደጋ በተደረገው የስልጣን ሽግሽግ ፓርቲዎን ወክለው ወደ ጠቅላይ ሚኒስቴርነት ሲወጡ ዝቅ ብለው ኢትዮጵያን ከፍ በማድረግዎ በግዜው የኢትዮጵያን ሕዝብ ድጋፍ ሙሉ በሙሉ በሚያሰኝ ሁኔታ አግኝተዋል::

በአስከአሁኑ ሁለት አመት ባልሞላ ቆይታዎ ለሀገርዎ ላበረከቷቸው ታላላቅ አስተዋፅኦዎች ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው አብዛኛው ሀገር ወዳዱ ኢትዮጵያዊ አንደ አይኑ ብሌን የሳሳልዎት የወደድዎትና የተከተልዎት በአነጋገርዎ ረክቶ ተስፋ ሠንቆ በድርጊትዎ ኮርቶ ሃገራችንም ካለችበት የተወሳሰበና ዘርፈ ብዙiችግር ባነሰ መስዋአትነት ሊያሻግር የሚችል በአሁኑ ግዜ ከርስዎ የተሻለ መሪ የለም ብሎ ፈጥጠው የሚታዩ ችግሮችን በድጋፍና በወገንተኛነት እንዳላየ ሆኖ ሊያልፍ ቢሞክርም ዛሬ በየአግጣጫው በሚሰማው የሕዝብ አልቂት መገፋፋትና ጉዳት ደጋፊዎ ሕዝብ በሀዘንና በተስፋ መቁረጥ መሃከል ሲባዝን ይስተዋላል::

በቀደሙት ሶስት አስርተ አመታት የዘር ፖለቲካ ሲያራምድ ትውልድ ሲገድል ሀገርን በጎሳና በቁአንቁአ ሲሸነሽን ሲገርፍ ሲያሠድድና ሐገሪቱን በጭካኔ ሲዘርፍ የነበረ ዛሬ መውጫው የጠበበበት መቀሌ የተሸነቆረው የወንጀለኛ መንጋ ምንም ይቅርታ ቢደረግለት ሐጥያቱ ስለሚያባንነው ከገባበት አጣብቂኝ ማእዘን ለመውጣት የማይፈነቅለው ድንጋይ እንደማይኖር አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሚረዳው ነው::

የኢትዮጵያን አንድነት ጥንካሬ የምስራቅ አፍሪካን ቀጠና ውሕደትና የኤኮኖሚ ትብብር: ፍቅርና ይቅር ባይነትን መስበክዎ መደመር ብለው አዲስ ጥምር የፖለቲካ ፓርቲ ማሠብዎ አክራሪ ብሔረተኞችንና ፅንፍ የረገጡ የመገንጠል አባዜ የተጠናወታቸውን የትንንሽ መንደር መሪ ናፋቂዎችን ሊያስነሳብዎ እንደሚችል በሐዘንና በጉዳት አንገታቸውን የሰበሩት አያሌ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን ወገንዎችዎ ይረዳሉ::

ክቡር ጠ/ሚኒስትር ::

ታድያ እነዚሕ ሁለት የኢትዮጵያ ጠላቶች በግዚያዊ ወዳጅነት ተጣምረው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያ የሚልን ሁሉ ለማጥፋት አምርረው እየታገሉ ይገኛሉ:: በየግዜውም የሚታየው የጅምላ ግድያ ሕዝብን ማፈናቀል ማሠደድ የጥላቻ የሃሠት ዜና ማሠራጨት ሕዝብን ሕዝብ ላይ በማስነሳት አብያተ ክርስትያናትን ማቃጠል የሐይማኖት አባቶችን መግደል መስጊዶችን ማቃጠል እኩይ ተግባራቸው በርስዎ የተለሳለሠ የፍቅርና የይቅርታ ሠበካ ሊሸነፍና ሊከስም ቀርቶ ያተረፈልዎ ከሠሞኑ የታየውን በአምቦ ከተማ ወጣቶች “አቢይ ነፍጠኛ” ነው ጫጫታና ከፍተኛ ተቃውሞን ነው:: ያተረፈልዎ በትሕነግ አመራሮችና አንድም ጥይት ሳይተኩሱ በየ ሐገሩ ተሰደው ታጋይ ነበርን በሚሉ ደካማ ሠዎች መገሰፅን ነው:: ያተረፈልዎ በራስዎ ላይ ከተደረገው የግድያ ሙከራ ጀምሮ በኢንጂነር ስመኘው በአማራ ክልል በወንድማማችዎች በነ ዶ/ ር አምባቸው መሐከልና አዲስ አበባ በነ ጄነራል ሠአረ የተደረገውን ግድያ የትሕነግ ረጅም እጅ በደም የተለወሠ ሆኖ ራሳቸው ባቀናበሩት ወንጀል እርስዎ የሚመሩትን መንግስት ደካማ ከማሠኘት ባለፈ በነዚሕ ሁሉ ወንጀሎች ጀርባ እንዳሉበት በከፈቱት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ አነስተኛ ቁጥር የማይባል የዋሕ ሕዝብ ማሳሳትን ነው :: ያተረፈልዎ የአጋርዎን የለማ መገርሳና በዙሪያዎ የሚገኙትን የኦሮሞ ኢሊቶችን በመከፋፈልና አርስዎን ከሕዝብ የመነጠል ስራ ተሠርቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሪው ደካማ መሆኑን በድርጊት እንዲያምን ማድረግን ነው::

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር::

ያንድ ሐገር ዜጎች ወይም ማሕበረሰብ ወይ ቡድን በሕግ መገዛትን በጋራ ሊያከብሩት የሚገባ ጉዳይ ሆኖ ማንኛውም መንግስት እንደ መንግስት ተቁአማቱን አጠናክሮ ባለው መንገድ ሁሉ ፍትሕን ለዜጎቹ በእኩልነት ሲያስከብር የሐገርንም ሰላም ማረጋጋትና እድገት የተመቻቸ ሁኔታን መፍጠር ዋነኛ ግዴታውና ሐላፊነቱ ነው::

ሕጉን በሚጥሱ ሕዝብን ወደጅምላ ጭፍጨፋ የሚያነሳሱትን የሐሠት ወሬ በመንዛት የሐይማኖት ግጭቶችን የሚፈጥሩትን 78 የንፁህ ዜጎችን ሕይወት በአሠቃቂ ሁኔታ የሚያስገድሉትን 26 ባንኮች የሚያዘርፉትን በረጅም እጃቸው መቀሌ ተቀምጠው ሐገር ለማፍረስ ሕዝብ ለማጫረስ ሌት ተቀን የሚሠሩትን ወንጀለኞችን ማባበልና ሕግን ተከትለን እርምጃ እንወስዳለን አካሄድ በአንድ በኩል: እንደ እስክንድር ያሉ አክትቪስቶችን ማስፈራራት የአብን አመራርን ጋዜጠኞችንና የተለየ ሃሳብ ያላቸውን ሕግ በማስከበር ስም ቀለል ያለውን እየመረጡ እርምጃ መውሰድ የተሄደበት ፍርደ ገምድል አካሄድ በሌላ በኩል ሲታይ አሳዛኝ የፍትሕ ውርጃ ከመሆኑም በላይ የመንግስትን አቅም ማጣት የሚያሳይ አለያም ሠብአዊ መብት በማክበር ስም የፖለቲካ ምህዳር በማስፋት ስም ሕዝብ ሲያልቅ የመንግስት ድፍረትና ቁርጠኝነት ማጣት ያለ መምሠሉ አሳዝኖናል::

በሰሜን አሜሪካ የምንገኝ የኢትዮጵያውያን ማሕበረሠብ መድረክ (ኢትዮጵያንስ ኮሚይኒቲ ፎረም) አባሎች ከማናቸውም የፖለቲካ ድርጅት ነጻ የሆንን በጋራ የሐገራችን የወደፊት እጣ ፈንታ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሠላምና ደሕንነቱ በጥልቅ የሚያሳስበን ወገኖች ውስብስብ የሆነውን የሀገራችንን ማሕበራዊ ፖለቲካና ኤኮኖሚያዊ አካሄድ ስንመረምር በሌሊት ከሚያባንኑን በቀን ከሚያስጨንቁን የሀገራችን አስከፊ ጉዳዮች መሃከል ጥቂቶቹን እናንሳ

አሁንም ግዜው የመሸ አይመስልም ቁርጠኝነቱ ካለ:: ጅብ ከሚበላህ በልተኸው ተቀደስ ይላል የሀገራችን ሰው::
ሐገር እንደ ሀገር እንድትቀጥል ከታሰበ በአስቸኩአይ የዚሕ ሁሉ ችግር ጠንሳሽ የሆነው መቀሌ የከተመው የዘራፊው ትህነግ ቡድን ላይ

መንግስት አቅሙን አሠባስቦ ሁሉን አቀፍ ጠንካራ እርምጃ መውሠድ ችግሩን ከምንጩ ማድረቅ ነው ብለን እናምናለን:: ባንድም ይሁን በሌላ መንገድ ይሕን ማድረግ መንግስት ከተሳነው ግን የተሰነቀልንን የርስ በርስ ዕልቂትና የሀገር መፍረስ ዕጣ ቆመን እየጠበቅን ቀስ አያልን እየሞትን ወንድሞቻችንን ዛሬ በአስር ነገ በመቶ ከነገ ወዲያ በሺህዎች እየቀበርን የሐገራችንን መበተን እያየን ወደ ውድቀት እንደምንጉአዝ የሚያሳይ የማስጠንቀቂያ ደወል ነው::

ባለፈ ታሪካችን ላይ ተመርኩዞ በየጊዜዉ ለሚከሰተዉ ጭቅጭቅ መፍትሄ ይሆን ዘንድ ከሁሉም ብሄር ብሄረሰብ የተውጣጡ የሃገር ሽማግሌዎች፣የሃይማኖት አባቶች፣አባገዳዎች፣የጎሳ መሪዎች፣ምሁሮች እና ፖለቲከኞች ያሉበት አገር አቀፍ ጉባኤ እንዲቋቋም እና ለታሪካችን
የመዝጊያ ምዕራፍ (Closure) እንዲኖረው ማድረግ ያስፈልጋል። በ100 ቀን ዉስጥ 800ሺ ዜጎችን ካጣችው ሩዋንዳ ትልቅ ትምህርት መውሰድ ይቻላል።

በህገ መንግስቱ አንቀጽ 52 ንኡስ አንቀፅ ሰ ላይ የተጠቀሰው “የክልሉን የፖሊስ ሐይል ያደራጃል ይመራል የክልሉን ሰላምና ፀጥታ
ያስጠብቃል” የሚለው ንዑስ ክፍል በትግራይና በአንዳንድ ሌሎች ክልሎች ከሚገባው በላይ ትርጉሙ ተለጥጦ የተደራጀው የልዩ ሃይልና የሚሊሺያ ሰራዊት አደረጃጀት ፖሊስ ከመሆን ባለፈ የፌደራሉን መከላከያ አቅም የሚገዳደር አቅም ያጎለበተ በፌዴራል መከላከያ ውስጥ ሌላ መከላከያ መፈጠሩ የከፍተኛ ስጋትና የአርስ በርስ ብጥብጥ መንስዔ ስለሚሆን መንግስት ሊያተኩርበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ለማሳሠብ እንወዳለን::

ዛሬ በሐገራችን እየታየ ያለው የሕግ የበላይነት መጥፋት እንደዚህ ዓይነት ኢሰብ አዊ ድርጊት በአገራችን ተፈጽሞ ማየት በጣም የሚያሳዝን እና በታሪካችንም እጅግ የሚያሳፍር እኩይ ተግባር ነው። በተለይም ደግሞ በጉዲፈቻ እና በሞጋሳ ባህሉ በአቃፊነቱ በሚታወቀው በታላቁ የኦሮሞ ህዝብ ክልል ውስጥ መፈጸሙ ብዙዎቻችንን ያስደነገጠ እና እስክ አሁን ለማመን ያቃተን ጉዳይ ነው። በፍጹም የኦሮሞን ህዝብ የሚመጥን አይደለም። የዚሕም ኢሠብአዊ ድርጊት መንስኤው ከስር መሰረቱ መመርመር አለበት ። ምርመራውን የሚመራ ገለልተኛ አካል እንዲቋቋም ፣ ተጠሪነቱም ለፓርላማ እንዲሆንና ዉጤቱን ለህዝብ ይፋ እንዲያደርግ እንጠይቃለን::
ሀገርንና ህዝብን ወደማያስፈልግ አግጣጫ አየገፋ ያለው የወንጀለኞች ሴራ አያያዙን አይተሕ ዳቦውን ቀማው ጦርነት አውጀው ለአያሌ
የሀገራችን ሕዝብ ሞት ስቃይ ከቀዬው መፈናቀል ስደትና ሰላም መደፍረስ የማያባራ ምክንያት ሆኗል:: ይሕ በትሕነግና በኦሮሞ አክራሪ ቡድኖች ለኢትዮጵያ የተደገሰው እኩይ ድርጊት አግጣጫውና መዳረሻው ሩዋንዳ ወይ የመን ወይ ሶርያ አለመሆኑን መንግስት በተለሳለሠ ስብከትና መግለጫ ሳይሆን በተጠናከረ ተግባር ሊያረጋግጥ ይገባል::

) ዛሬ የሚታየዉን ቅጥ ያጣ የሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ተከትሎ ሀገር ቀውስ ውስጥ ከገባችና ሕግን ማስከበር በመንግስታዊ ተቁዋማት ሳይሆን በጎበዝ አለቃና በሰዎች መዳፍ ስር ከወደቀ የሚቀረው አንሽራታች ቁልቁለት በቅፅበት ሕዝብንና ሃገርን እንደ ሰደድ እሳት የሚያዳርስ የከፋ አደጋ ያለው መሆኑን መንግስት በመገንዘብ ከሚቀጥለው ምርጫ በፊት የሕዝብን ተሳትፎ ያማከለ ዘመቻ አድርጎ ያለውን የጦር መሳሪያ በአዋጅ ወይም መልሶ በመግዛት ይሕን እሳት ከሕዝቡ ጉያ ውስጥ ለማውጣት ከፍተኛ ሥራ ያስፈልጋል::

ዛሬ የሚታየውን የጅምላ ፍጅት ወደሚቀጥለው ላቅ ያለ ደረጃ ለማሸጋገር በውጭ የሐገራችን ጠላቶች በሚታገዙ አሸባሪዎች ታላላቅ ተፅእኖ ፈጣሪዎችን ለማስገደል የስናይፐር መሳርያ አካሎችን ወደሐገር ለማስገባት ሙከራው ሕግ በሌለበት በሕግ አካሄድ ማለት ተገቢ አይመስልም:: ተቀድሞ ምክንያት ከመደርደርና ሙሾ ከማውረድ ጠንክር ያለ መከላከልና ማጥቃት መጀመር ሐገር ያድናል ስርአትም ያስከብራል ዜጎቻችንም ካላስፈላጊ መቀጠፍ ያድናል ብለን እናምናለን:: አሁን እጅን አጣጥፎ ከዛሬ ነገ ይሻል ይሆን ተስፋ መሰነቅ ከሩዋንዳ ክሶማሊያ ከየመንና ከሶርያ ላለመማር ቤታችን አሳቱ እስኪገባ የመጠበቅ ያክል ሆኖ ይሰማናል:: አይመጣምን ትተሽ ይመጣልን ባሰብሽ የቅደመ ጥንቃቄ ሃገራዊ ብሂል ላለንበት ሁኔታ ጥሩ ማሳያ ነው::

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር::

በመላው አፍሪካ ተወዳጅ የሆነችዉ ዶ/ር ሙምቢ ሴራኪ ኦክቶበር 30/2019 ለ 11 ደቂቃ በ“Dr.Mumbi Show” ስለ እርስዎ ባዘጋጅችዉ ፕሮግራም ላይ ኢትዮጵያ ዉስጥ የተከሰተዉን መጥፎ አጋጣሚ “የኖቤል እርግማን” (The Curse of Nobel) ካለች በኋላ ምናልባትም አገራችን ላይ የሚካሄድ የዉጭ ሴራ ሊኖር እንደሚችል ገምታ በእርስዎ ዘመነ መንግስት ኢትዮጵያ እንዳትበታተን ስጋቷን በሃዘን በመግለጽ ህዝቡ ወደ ፈጣሪ እንዲጸልይ መክራለች ።

በታሪክ አጋጣሚ ሃገራችን አሁን ባለችበት የመበታተን አደጋ ወቅት የእግዚአብሄር ፈቃድ ሆኖ በያዙት ሃላፊነት የኢትዮጵያ ዕጣ በእጅዎ ላይ ወድቋል፡፡ በዚህ ስጋትና ተስፋ በተቀላቀለበት ስሜት ዉስጥ ስላለ ነዉ ህዝባችን “ሙሴ” እና “ነቢይ” እያለ እርስዎን እስክማምለክ የደረሰው፡፡ይህን እድል ከተጠቀሙበት ኢትዮጵያን ከውድቀት ሊያድኗት ይችላሉ፡፡ አለበለዚያ ግን ይህ ሳይሆን ቀርቶ ኢትዮጵያ ወደ 10 እና ከዛ በላይ ባሉ ትናንሽ አገሮች ከተከፋፈለች በታሪክ ተወቃሽ በመሆን የጎርባቾቭን ቦታ ይወስዳሉ።እንዲህ ዓይነቱ መበታተን ደግሞ መጨረሻዉ በበርካታ ትናንሽ መንግስታት መካከል በሚነሳ የድንበር ጥያቄ ማለቅያ ወደሌለው ጦርነት ማምራት ነው ። ደቡብ ሱዳንና ኤርትራ ለዚህ ምሳሌ ናቸው።

በመጨረሻም ፀጥ ያለው ብዙሃን የኢትዮጵያ ህዝብ እስከዛሬ ለሀገርዎ ያበረከቱትን በአድናቆት የሚከታተልና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላምና ደህንነት ለሀገራችንም እንደሀገር በሰላም ለመቀጠል ለሚያደርጉት ሁሉን ስለምንረዳ ኢትዮጵያውያን ከጎንዎ እንደምንቆም በአፅንዎት ልንገልፅልዎ አንወዳለን::

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን አብዝቶ ይባርክ::

የኢትዮጵያውያን ማሕበረሠብ መድረክ ፅሕፈት ቤት

ዳላስ ቴክሳስ

7 ኖቬምበር 2019

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *