የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ
News

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መስራች ጉባኤ መግለጫ

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መስራች ጉባኤ መግለጫ

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) –የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) ከ1987ዓም በውጭ አገር ሆኖ የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ)ን አፋኝ ስርዓት ሲታገል የቆየ ድርጅት ነው። በኢትዮጵያ በተገኘው የለውጥ ሁኔታ ከሰኔ 2010 ዓ/ም ጀምሮ አገር ቤት በመግባት በሰላማዊ መንገድ ዓላማውን ሲያራምድ እና አባሎችን ሲመለምል ቆይቷል። አሁን ደግም የኢትዮጵያ የፓርቲዎች ምዝገባ ህግ በሚጠይቀውና በሚፈቅደው መሰረት 1ኛ ጉባኤውን ከኅዳር 27 – 28, 2012 ዓ/ም አካሂዶ አጠናቋል።

መስራች ጉባኤው አገራዊ ወቅታዊ ሁኔታዎችን ሲገመግም በኢትዮጵያ በ2010 ዓ/ም በህዝብ መስዋእትነትና ግፊት የተጀመረው እንቅስቃሴ ከገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ለውጥ የሚፈልጉ ሃይሎች ድጋፍ በማግኘቱ ብዙ ለውጦችን አካሂዷል። ፖለቲካዊ እስረኞችንና ጋዜጠኞችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ፈትቷል፣ በውጭ በሰላምም ይሁን በትጥቅ ሲታገሉ የነበሩ ተቃዋሚ ድርጅቶችን አገር ቤት ገብተው በሰላም እንዲታገሉ ፈቅዷል፣ የመናገር የመጻፍና የሚዲያ ነጻነትን ፈቅዷል።

ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶችን ሲጥሱ የነበሩትን ህጎች/አዋጆች እንደ `የፀረ ሽብር አዋጅ፣ የሲቪል ማኅበርሰብ ድርጅቶች አዋጅ ፣ የሚዲያ አዋጅ፣ የፓርቲዎችና የምርጫ ቦርድ አዋጅ፣` የመሳሰሉቱም እንዲሻሻሉ ወይም እንዲቀየሩ እየተደረጉ መሆናቸው መልካም የለውጥና ተስፋ ሰጪ ጅምሮች መሆናቸው ጉባኤው ግንዛቤ ወስዷል። ሆኖም የለውጡ ሂደት ብዙ ደንቃራዎች እንደገጠሙትና ብዙ ተግዳሮቶች እንዳሉትም ጉባኤው ተገንዝቧል።

በለውጡ ሂደት ጥቅማቸው የተነካባቸው ግለሰዎችና ድርጅቶች እንዲሁም ጽንፈኛ ብሄራዊ ድርጅቶች በወሰንና በተለያዩ መንገዶች ህዝብ ከህዝብ ጋር በማጋጨት ብዙ ሰዎች እንዲገደሉ፣ እንዲደበደቡ፣ እንዲፈናቀሉ ተደርጓል። በዚሁም ብዙ የትግራይ ተወላጆች ሰላባ ሆኗል። ይህ ሁኔታ ከአጀማመሩ አሁን እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም አሁንም በአገሪቱ ገና የተረጋጋ ሰላም የለም። የፈደራል መንግስትም በአገር ደርጃ የተገኘውን ለውጥ በሁሉም ክልሎች እንዲተገበሩ ለማድረግ አልቻለም። በዚሁም ዋነኛ አፈንጋጭ ሆኖ የሚገኘው ህወሓት ነው። በትግራይ ክልል በለውጡ የተገኙት ትሩፋቶች የሉም ለማለት ይቻላል። ትግራይ አሁንም እንደ ድሮው በህወሓት አፈና ላይ ነው ያለው።

ያለንበት አካባቢ የቀይ ባህር አዋሳኝ  በመሆኑና ኢትዮጵያም የጥቁር ዓባይ መነሻ በመሆኗ የሌሎች አህጉሮች ፍላጎት የሚስብና ጥቅማቸውን ለማረጋገጥ የሚፎካከሩበት ቀጠና/ሪጅን ነው። ቀይ ባህርን ለመቆጣጠር አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ ቻይና እንዲሁም የዓረብ አገሮች እሽቅድድም እየታየ ነው። የዓባይ ግድብን አስመልክቶ ደግሞ ግብጽ ትልቅ ተቃውሞ እያስያች ያለችበት ሁኔታ ነው። እነዚህ የውጭ አህጉሮች ጥቅማቸውን ሊያሟሉላቸው የሚችሉትን ሃይሎች በመደገፍ ይሁን በማደራጀት በሃገራችን ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ሊያረጉ እንደሚችሉ ጉባኤው ተገንዝቧል።

ጉባኤው በፕሮግራሙና በህገ ደንቡ ላይ ሰፊ ውይይት አድርጓል። የትግራይ ህዝብም ሆነ የተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያነሳቸውን የስራአጥነትና ድህነት፣ የፍትህ እጦት፣ የዲሞክራሲና ሰብአዊ ጥሰቶች፣ ሙስና፣ የጤና ግልጋሎት ማነስ፣ የትምህርት ጥራት ጉድለት፣ የብሄር ጥያቄ፣ የመሬትና የግብርና ጥያቄ የመሳሰሉትን መልስ ሊሰጥ የሚችል ፕሮግራምና አቅጣጫ ቀይሷል። የመድብለ ፓርቲ ፓርሊያመንታዊ ስርዓት የሚከተል ያለውን የፈደራል አወቃቀር ማለትም የህዝብ ተወካዮችና የፈደረሽን ምክር ቤት ይቀበላል።

በፈደረሽን ምክር ቤት ሁሉም ክልሎች እኩል ድምጽ እንዲኖራቸው ያምናል። በህግ አውጪ፣ ሕግ አስፈጻሚ እና ህግ ተርጓሚ ያለው የስልጣን ወሰን በግልጽ ተቀምጦ ሁሉም ነጻ ሆነው ከስልጣናቸው ውጭ እንዳይሄዱ አንዱ ሌላውን የሚቆጣጠርበት ስርዓት እንዲኖር ያደርጋል። በኢኮኖሚ ዘርፉ ፍትሓዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር በማድረግ  ባለ ሃፍቶች ዋስትናቸው በተጠበቀ ኢንቨስት የሚያረጉበትና መንግስትም ተገቢውን ሚና የሚጫወትበት የሶሺያል ዴሞክራቲክ መርህ ይከተላል።

ረሃብንና ድህነትን ለመቀነስ እና እድገትን ለማሳደግ እርሻ ላይ ትኩረት ይሰጣል። መንግስት አርሶአደሩን የማይረባ ዋጋ እየሰጠ በማፈናቀል ራሱ መሬቱን በከፍተኛ ዋጋ በመሸጥ የሚነግድበትን ስርዓት ያስወግዳል። የብሄሮች እኩልነት ብሎም የኢትዮጵያ አንድነት እንዲጠናከር ይሰራል።

ከሌሎች ድርጅቶች በትግራይ ክልል ካሉትም ይሁን ከክልሉ ውጪ ካሉት ዴሞክራሲያዊ ድርጅቶች ጋር ፕሮግራምና ዓላማን መሰረት ባደረገ በቅንጅት ወይም በግንባር ወይም በውህደት ደረጃ ትብብር ያደርጋል። ቅንጅትና ግንባርን በሚመለከት ማእከላዊው ኮሚቴ የሌላ ጉባኤ ውሳኔ ሳይጠብቅ እንዲፈጽም ውሳኔ አሳልፏል።

ህገ ደንቡንም በዝርዝር ከተወያየ በኋላ አጽድቋል። የድርጅቱ ስም `የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) በእንግሊዝኛ Tigray Democratic Party (TDP)` እንዲባልና የድርጅቱንም አርማ አጽድቋል።

በመጨረሻም 12 አባሎች ያሉበት ማእከላዊ ኮሚቴ፣ ከነዚሁም 5 ስራአስፈጻሚ ኮሚቴ አባሎችን መርጧል። በመቀጠልም 3 የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚቴ አባላትን በመምረጥ ጉባኤውን አጠቃሏል።

የተከበርክ የትግራይ ህዝብ ሆይ፤

ለፍትህ፣ ለዲሞክራሲ፣ ለነጻነት፣ ለብሔራዊ እኩልነት፣ ለመልካም አስተዳደር፣ ለእድገት ብለህ ለ17 ዓመት የታገልክበትና ልጆችህን የገበርክበት ሂደት በመቀልበስ ህወሓት ይባሰውን ጨቋኝና አፋኝ በሆነ ስርዓት ስቃይህን እያየህ መሆኑን ለቀባሪ ማርዳት ይሆንብናል። ሌላው ቀርቶ አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ እያገኘ ያለውን የዲሞክራሲ መብት በነጻ የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመደራጀት፣ የመሰብሰብ፣ ነጻ ሚድያ መብቶች የተከለከለበት ሁኔታ መሆኑ ለበለጠ ትግል የሚጋብዝ ነው።

ከዚህ ካልህበት መቀመቅ ለመውጣት ያለህ አማራጭ ተደራጅተህ የበሰበሰውን የህወሓት ስርዓት በመጣል ብቻ ነው። ለዚሁም አንተ ያነሳቸኸውን ጥያቄዎች አንስቶ በመታገል ላይ ያለውን ድርጅት የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን በመርዳት እና በመቀላቀል ነው።

የትግራይ ወጣት ሆይ፤ 

ወላጆችህ ያካሄዱት ትግልና ያሳለፉት መከራ ታውቀዋለህ ። የህወሃት አመራር በስልጣን ብልግናና  በሙስና የተካነ አዲስ መደብ ፈጥሮ ህዝብህን ቁም ስቃይ እያሳየው ይገኛል። ከዚህ አልፎም በአገርህ ኢትዮጵያ ተንቀሳቅሰህ እንዳትማርና እንዳትሰራ ጋሬጣ ፈጥረውብሃል። እነሱ ግን ሸሽተው የትግራይ ህዝብን መሸሸግያ ምሽግ ኣድርገውታል ። ከዚህ የከፋ ክህደት የለምና ፣ ለዴሞክራሲ፣ ለፍትህ፣ ለብሔራዊ እኩልነትና ለጋራ እድገት ከሚታገለው የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ጋር ተቀላቅለህ ለነጻነትህ ታገል።

መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ፤

የህወሓት/ኢህኣዴግ አመራር በትግራይ የፈጠረውን የኣፈና ስርዓት በሃገሪቱ እንዲያንሰራራ አድርጎ ለብዙ መከራ እንደዳረገህና አልፎም ወገን ከወገኑ ጋር እንዲጋጭና ደም እንዲፋሰስ ማድረጉ በሚገባ ታውቀዋለህ ። ህወሓት ኣሁንም ከማህል አገር ኮብልሎ፣ ትግራይ ውስጥ መሽጎ ወደ ፈጠረው የኣፈና ስርዓት ለመመለስ ጥረት እያደረገ ይገኛል። ትዴፓ በብኩሉ ይህ የኣፈናና የከፋፍለህ ግዛ ስርዓት ተወግዶ በምትኩ የዴሞክራሲ፣ የፍትህ፣ የእኩልነትና የአንድነት ስርዓት ይመሰረት ዘንድ በትግል ላይ ስለሚገኝ ያልተቆጠበ ትብብርና እርዳታህን እንዳይለየን በትህትና እንጠይቃለን ።

 

ድል ለዴሞክራሲያዊ ሃይሎች!!!                                     ኅዳር 28, 2019

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *