News Perspective

ኢሕአፓ: የሴቶች ጥያቄ ዛሬም አልተመለሰም

የሴቶች ጥያቄ ዛሬም አልተመለሰም

የካቲት 29 ቀን 2013 ዓ.ም.

የዴሞክራሲ ሥርዓት ተጀመረ፣ ተግባራዊም ሆነ ከሚባልባት ከጥንታዊቷ ግሪክ ጊዜ ጀምሮ ሴት ልጅ አደባባይ አትወጣም፣ የመምረጥም ሆነ የመመረጥ መብት አይገባትም፣ በሀብት ክፍፍልም ወንድ ላቅ ያለውን ድርሻ ይወስዳል እየተባለ ነው የተኖረው።  ይህ ኅብረተሰቡ ለዘመናት የኖረበት መንገድ የኅብረተስቡን ግማሽ አካልና የቤተሰብ መሥራቾችን ቅስም ስብሮ የጓዳ ሠራተኛ ወይም “የቤት እመቤት” ሆነው እንዲኖሩ አድርጓቸዋል።

ሳይንስና የቴክኖሎጅ በማደጉ እንዲሁም የኅብረተሰቡ ንቃተህሊና ከፍ እያለ በመምጣቱ የሴቶች ጥያቄ በአደባባይ መውጣት ጀመረ።  ቅርጻቸውና ይዘታቸው ይለያይ እንጂ በራሺያና በተለያዩ የአውሮጳ አገሮች ውስጥ በ18ኛው ክፍለ ዘመን የሴቶችን መብት ለማስከበር ከፍተኛ እንቅስቃሴ ይካሄድ ጀመር።    እንቅስቃሴውም እያደገ ሄዶ ከፍተኛ የሕይወትና የአካል መስዋዕትነትንም አስከፍሎ አሁን ከደረስንበት እመርታዊ ለውጥ ላይ ደርሷል።  በራሺያ፣ በፈረንሳይ፣ በጣሊያንና በአሜሪካ በርካታ ታጋይ ሴቶች ትግሉ ዓለማቀፋዊ እንዲሆን ውድ ሕይወታቸውን ከፍለዋል። በረጅሙ የትግል ሂደት ውስጥ አንዳንድ አወንታዊ ለውጦችን ማስመዝገብ ቢቻልም መሠረታዊው የሴቶች ጥያቄ ግን ዛሬም አልተመለሰም።

የሀብት ፍትሃዊ ክፍፍል፣ የመምረጥና የመመረጥ መብት፣ የፆታ እኩልነት መብትና ለተመሳሳይ ሥራ እኩል ክፍያ የሚሉት ቁልፍ ጥያቄዎች በምዕራቡም ሆነ በምሥራቁ ዓለም ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ አልሆኑም።  ብዙ አገሮች በህገ መንግሥታቸው ውስጥ የሴቶችን የእኩልነት መብት እንደሚያከብሩ ያሰፈሩ ቢሆንም ተግባራዊ ግን አላደረጉትም።  የሶሻሊስ አብዮት ያካሄዱ አገሮች ለሴቶች የእኩልነት ጥያቄ ከፍተኛ ክብደት የሰጡት ቢሆንም በተግባር ከምዕራቡ አገሮች የተለዩ አልሆኑም።

በሌላ መልኩ በአንዳንድ ሀገሮች ውስጥ ዴሞክራሲና የእኩልነት መብት በማይታወቅበት ዘመን ብዙ ታጋይ ሴቶች ከፍተኛ ድል አስመዝግበዋል፣ የዲፕሎማሲ ክህሎታቸውንም አሳይተዋል።  የውጪውን ዓለም እንተወውና በአገራችን ውስጥ የዴሞክራሲያዊ መብቶች ወይም የእኩልነት መብት ጠረኑም በማይሸትበት ዘመን ታዋቂና ዓለምን ያስደመሙ ሴት ንግሥቶች በጦር ሜዳና በአስተዳደር የሚመሰገኑና ምሳሌ የሚሆኑ አኩሪ ድሎችን አስመዝግበው አልፈዋል።  ለምሳሌ ንግሥት እሌኒ በፖለቲካና በዲፕሎማሲ እጅግ የተራቀቁ ንግሥት እንደነበሩ ታሪከ-መዋዕላቸው ያስረዳል።  እቴጌ ጣይቱ ብጡልም ብልህ የጦር መሪና ፖለቲካ አዋቂነታቸውን ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ ጠላቶችም ሳይቀሩ መስክረውላቸዋል።

ሀገራችን ውስጥ በተደረጉ የመንግሥት ምሥረታ ውጣ ውረዶች የሴቶች አሻራ ያላረፈበት ታሪክ የለም።  የነፃነት አንፀባራዊው የአድዋ ጦርነት ሲካሄድ እናቶቻችን በየጦር ግንባሩ እየገቡ ውኃ እያቀበሉ፣ ምግብ እያጎረሱ፣ ቁሰለኛ እያሸሹ፣ የሰነፈውን እያበረታቱ፣ ለተዋጊው ጦር ምግብ በማብሰል፣ አርበኞች አባቶችን መግበው ዛሬ የጥቁር ሕዝብ ኩራት፣ የቅኝ ገዥዎች ውርደት የሆነውን ድል አስመዝግበዋል።  በአድዋ ጦርነት ወቅት ሴቶች ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ እየታወቀ፣ ሽልማቱም፣ ሙገሳውም፣ ቀረርቶውም፣ የአዝማሪው ዜማም፣ የሁሉም ነገር የታሪክ ቁንጮ ሆኖ የተመዘገበው ለወንዱ ነው።

ወደ ቅርብ ጊዜ ታሪካችን ስነመለስ ደግሞ በ60ዎቹ ለለውጥ የጀርባ አጥንት ሆነው የታገሉና ያታገሉ፣ ተፋልመው መስዋዕትነት የከፍሉ ያ ትውልድ እየተባለ በሚጠራው ትውልድ ውስጥ ሴቶች ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው የዛሬው ትውልድ የሚመሰክረው ሃቅ ነው።  በኢሕአፓ የትግል መሥመር ተሰልፈው ከተራ አባልነት ጀምሮ የአመራር አባል በመሆን የታገሉ፣ የመሩ፣ የተሰዉ ጀግኖች ጓዲቶቻችንን እናደንቃለን።  ጓዲቶቻችን የታገሉት የሴቶችን የእኩልነት መብት ለማስከበር ብቻ ሳይሆን ጨቋኙን ሥርዓት ለመገርሰስና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመመሥረትም ነበር።  የኢትዮጵያ ሴቶች ትግል የዓለምአቀፍ የሴቶች ትግል አካል በመሆኑ በየዓመቱ የካቲት ኝን (March 8) እናከብራለን።  በእናቶቻችንና በእህቶቻችን ከፍተኛ ትግል የተወለደውን የካቲት ን ስናከብር የሴቶች ጥያቄ ዛሬም መልስ ያለገኘ በመሆኑ፣ ቀጣይና ጠንካራ ትግል ለማድረግ ቃልኪዳናችንን እያደስንም ጭምር ነው።

ከገጠር እስከ ከተማ እናቶቻችንና እህቶቻችን በደል እየተፈጸመባቸው እንደሆነ የሚታወቅ ነው።  የሴቶች መብት ባልተከበረበት፣ ለእኩል ሥራ እኩል ክፍያ ባልተረጋገጠበት፣ ለጤንነት አስጊ በሆኑ የሥራ መስኮች ውስጥ የሚሠሩ እናቶቻችንና እህቶቻችን የጤና ዋስትናም በሌለበት ኅብረተሰብ ውስጥ የሴቶች እኩልነትና ለእኩል ሥራ እኩል ክፍያ፣ አሁንም የመታገያ መፈክራችን ነው።  ኢሕአፓ ዛሬም ለሴቶች መብት ይታገላል፣ የተለያዩ የኅብረተስብ ክፍሎችንም በጋራ እንታገል በማለት ጥሪውን ያቀርባል።  የሴቶች ጥያቄ መልስ ያላገኘበት ኅብረተሰብ ኢሕአፓ ጎደሎ ነው ብሎ ያምናል።

 

የሴቶች እኩልነት ተግባራዊ ይሁን!

eprpSupportfooter

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *