የጥምቀት በዓል
News

በጎንደር የጥምቀት በዓል መቀመጫ ሰገነት ላይ በደረሰ መደርመስ የአሥር ሰዎች ሕይወት አለፈ

በሳሙኤል ጌታቸው

በየዓመቱ የጥምቀት በዓል ከሚከበርባቸው ሥፍራዎች አንዱና ዋነኛ በሆነው ጎንደር ከተማ በደረሰ የመደርመስ አደጋ፣ አሥር ሰዎች መሞታቸውና በርካቶች ቀላልና ከባድ ጉዳት ደረሰባቸው፡፡

ባህረ ጥምቀቱ በተዘጋጀበት የአፄ ፋሲል መዋኛ ገንዳ አካባቢ ለእንግዶች መቀመጫ ተብለው ከተሠሩ የእንጨት ርብራቦች መካከል በአንዱ በደረሰ መደርመስ፣ የአሥር ሰዎች ሕይወት ማለፉን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል አስታውቋል፡፡

ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ሰባቱ ሆስፒታል የደረሱት ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ከአንድ ሰዓት ቆይታ በኋላ ያረፉ ናቸው፡፡

ጉዳት ከደረሰባቸው 230 ሰዎች 150ዎቹ ሕክምና ከተደረገላቸው በኋላ ወደየቤታቸው ሲመለሱ፣ ሕክምና ከሚከታተሉት 80 ጉዳተኞች መካከል 13 የደረሰባቸው አደጋ ከፍተኛ በመሆኑ ሕክምናቸውን እየተከታተሉ ናቸው፡፡

በክብረ በዓሉ ከተገኙ የውጭ አገር ቱሪስቶች መካከል ጉዳት ከደረሰባቸው አራት አሜሪካውያን ሦስቱ ታክመው ወደ ሆቴላቸው ሲመለሱ፣ የ70 ዓመቱ የሕክምና ዶክተር የሆኑት አሜሪካዊ ግን የደረሰባቸው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ በኦክስጅን ድጋፍ ሕክምና እያደረጉ ናቸው፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው አሜሪካዊት፣ ባለቤታቸውን ወደ አገራቸው ለመውሰድ ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አደጋውን አስመልክቶ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምርያ ማክሰኞ ጥር 12 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፣ አደጋው ሊፈጠር የቻለው ለክብረ በዓሉ ከተዘጋጁት አራት እንጨት መቀመጫዎች መካከል አንዱ በከፍተኛ የሰው ብዛት በማስተናገዱ ነው፡፡ የአደጋውን መንስዔ የሚያጣራ ቡድን መቋቋሙንና ውጤቱን ይፋ እንደሚደረግም ገልጿል፡፡

በሌላ በኩልም በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ታቦታቱ ወደ ባህረ ጥምቀት በሚጓዙበት በጥር 10 ቀን የከተራና በጥር 11 የጥምቀት በዓል ወቅት ችግሮች መከሰታቸው ታውቋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የጥምቀት በዓል ከሞላ ጎደል በመልካም ሁኔታ ተከብሮ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ውጪ በተለይ በሐረር ከተማና ሌሎች አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ችግሮች ነበሩ፡፡

በተለይ በሐረር ከተማ ታቦት በሚሸኙት ላይ የደረሰ ጥቃት እንደነበረ፣ በተለያዩ የንግድ ተቋማት ላይ የንብረት ውድመት መድረሱ፣ ታቦት አጅቦ መጓዙ ላይ መስተጓጎል ተፈጥሮ እንደነበር ተወስቷል፡፡

የሐረሪ ፖሊስ ኮሚሽን ለኢዜአ እንዳስታወቀው ከጥር 10 ቀን ጀምሮ የጥፋት ተልዕኮ ያነገቡ አካላት በዓሉን ለማወክ ያደጉት ጥረት፣ በፀጥታ አካላትና በኅብረተሰቡ ቅንጅት የከፋ አደጋ ሳይደርስ ለመቆጣጠር ተችሏል፡፡ በተፈጠረው የፀጥታ ችግርም በ19 ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት ማጋጠሙንና በንብረት ላይ ግን ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል፡፡

የሐረሪ ክልል ፖሊስ ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን 20 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ማዋሉንና ለደረሰው የንብረት ውድመትና የአካል ጉዳት ተጠያቂ እንደሚያደርግም ተናግሯል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለም የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን አንድ ሰው በድንጋይ ተደብድቦ መገደሉን፣ ሰባት ሰዎች በጥይት መቁሰላቸውን፣ ሁለት መኪኖች መቃጠላቸውን፣ አንድ መኖሪያ ቤትና የከብቶች ማደሪያ መቃጠሉን፣ ሦስት የንግድ መደብሮች መዘረፋቸውን፣ 14 ፖሊሶች መደብደባቸውንና ግለሰቦችም መዘረፋቸውን አስታውቋል፡፡

የአዲስ አበባ አስተዳደር ሹምሽር እንደሚያደርግ ተሰማ
ምንጭ፡ ሪፖርተር

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *