በቺካጎ የኢትዮጵያውያን ማኅበር መስራች አቶ መንግሥቴ አስረሴ ህይወታቸው በኮሮናቫይረስ ምክንያት ማለፉን ማኅበሩ ከሰዓታት በፊት በፌስቡክ ገፁ አስታውቋል።
ማኅበሩ በመስራቹና የመጀመሪያው ፕሬዚዳንቱ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገልፆ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ እንደነበሩም አስታውሷል።
ኢትዮጵያውያንን በማሰባሰብ፣ ለማኅበረሰቡ የቅርብ ደራሽ የነበሩት አቶ መንግሥቴ በቺካጎ የኢትዮጵያውያንን ማኅበር የመሰረቱትም ከ36 ዓመታት በፊት ነበር።
በቺካጎ አካባቢ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዋልታ በመሆን፣ ድጋፍን በመቸር ይታወቁ ነበር የተባሉት አቶ መንግሥቴ ትንሽ፣ ትልቅ ሳይሉ ከሁሉ ጋር በመቀራረብ አንድነትን፣ ህብረትን በማምጣት በብዙዎች ዘንድ መወደድ የቻሉ ናቸው ተብሏል።
በብዙዎችም ዘንድ ጋሽ መንግሥቴ ተብለው ይጠሩ እንደነበርም ማኅበሩ አስታውሶ በአሁኑም ወቅት በቦርድ አባልነት እያገለገሉ ነበር ብሏል።
የአቶ መንግሥቴ ሞት በቺካጎ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤና ሃዘንን ያስከተለ ሲሆን በርካቶችም በፌስቡክስ የተሰማቸውን አስፍረዋል።
“እኔም ሆነ ቤተሰቤ በጣም ነው የደነገጥነው። ወዳጄ ነበር፣ የማኅበረሰቡም ዋልታና ማገር ነበር። ሞታቸውንም አሁንም ማመን አልቻልኩም። ጋሽ መንግሥቴ በሁላችንም ህይወት ውስጥ የማይረሳ ትውስታን ጥሏል። በልባችንም ለዘላለም ይኖራል። ነፍሱን በሰማይ ያሳርፍ” ብለዋል ኪሮስ ተወልደ ገብርኤል የተባሉ ኢትዮጵያዊ።
“እኔም ሆነ ባለቤቴ የተሰማንን ሃዘን ለመግለፅ ቃላት ያጥረናል። የተከበሩ፣ የረዥም ጊዜ ወዳጃችንን ጋሽ መንግሥቴ ማጣታችን ልባችንን ሰብሮታል። ነፍስዎን በሰማይ ያኑር። መቼም ቢሆን አይረሱም። ለቤተሰባቸው መፅናናትን ያምጣላቸው” በማለት አቶ ብርሃነ ሺፈራው አስፍረዋል።
“ጋሽ መንግሥቴ አብሮ የመስራት እድል አግኝቼ ነበር። በጣም ታላቅ ሰው ነበሩ። ማመን ይከብዳል፤ በጣምም ያሳዝናል። አላህ ነፍሳቸውን በሰማይ ያሳርፍ። ለቤተሰባቸውም ሆነ ለማኅበረሰቡ ጥንካሬና ፅናት ይስጣቸው” ብሏል አቢቹ ኢድሪስ።
ብዙዎችም በህይወት እያሉ ምን አይነት ታላቅ ሰው እንደነበሩ የዘከሩ ሲሆን ለቺካጎ ማኅበረሰብ ታላቅ ሰው፣ መካሪ፣ ታላቅ አባት እንዳጡም ገልፀዋል።
ማኅበሩ እንዳሳወቀው የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውንም በተመለከተ ለኮቪድ-19 ህሙማን በሚደረገው የአቀባበር ሥርዓት መሰረት እንደሚሆን ገልፆ፤ በዚህም መሰረት የቅርብ ቤተሰቦች እንደሚገኙም አስፍሯል።
ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ እንደተናገሩት ከአንድ መቶ በላይ ኢትዮጵያዊያን በበሽታው መሞታቸውን መናገራቸው ይታወሳል።
በኮሮናቫይረስ ክፉኛ ከተጠቁ አገራት መካከል ቀዳሚዋ እንደሆነች የተነገረላት አሜሪካ ውስጥ እስካሁን ከ46 ሺህ በላይ ሰዎች በበሽታው ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን ከ841 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ በወረርሽኙ መያዛቸው ተረጋግጧል።
Source: BBC Amharic