bati
News

በአፋር ክልል ገበያ ላይ በተፈጸመ ጥቃት የአምስት ሰዎች ህይወት አለፈ

ምንጭ፡ የቢቢሲ የአማርኛው ድህረ ገጽ

ዛሬ [ማክሰኞ] ከባቲ ወረዳ ወደ አፋር ክልል ወደ ሚገኝ አደ አራ ወረዳ ለገበያ የሄዱ 7 ሰዎች በጥይት መመታታቸውን እና የአምስቱ ሰዎች ህይወት ማለፉን የባቲ ወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ መሐመድ አብዱ ለቢቢሲ ገለፁ።

በጥይት የተመቱት 7ቱ ሰዎች የባቲ አካባቢ ነዋሪዎች መሆናቸውን አቶ ሞሐመድ ተናግረዋል::

በተተኮሰባቸው ጥይት የተጎዱ ሁለት ሰዎች ወደ ሆስፒታል መላካቸውን ጨምረው አስረድተዋል።

አቶ መሐመድ ሰዎቹ መሃል ገበያ ላይ ተተኩሶባቸው እንደተገደሉ ገልጸው፤ “ግድያ የተፈጸመባቸው በማንነታቸው ምክንያት ነው” ብለዋል።

“ዛሬ [ማክሸኖ] ሙዴ ኢና የሚባል ስፍራ ላይ ገበያ ነበር” ያሉት ኃላፊው የሞቱት ሰዎች ከባቲ ወረዳና ከባቲ ከተማ መሆናቸውን ጨምረው ገልፀዋል።

ተኩሱን በነጋዴዎቹ ላይ የከፈቱት ታጣቂዎች ከአፋር የመጡ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ መሐመድ ከመኪና አውርደው ጥቃት እንዳደረሱም ጨምረው አስረድተዋል

የግድያው ምክንያት ማንነታቸውን ብቻ መሰረት ያደረገ ነው የሚሉት ኃላፊው በአሁኑ ጊዜ ለዚህ ጥቃት የሚያበቃ በአካባቢው ግጭት አለመኖሩን ይናገራሉ።

ግጭት የነበረው ድንበር አካባቢ ነው በማለት “ገበያው የጋራ ገበያ ነው፤ ሁሉም እየሄደ ይገበያያል፤ ዛሬ ግን ይህ ተፈጥሯል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ካርታ

የሞቱት ሰዎችን አስከሬን የመከላከያ ሠራዊት ወደ ቦታው ገብቶ ማውጣቱን የሚናገሩት ኃላፊው የሞቱት ሰዎች ቀብርም መፈፀሙን አስረድተዋል።

እስካሁን ድረስ ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለ ሰው ስለመኖሩም የሚያውቁት ነገር አለመኖሩን ገልፀው፤ ከአፋር ክልል ኃላፊዎች ጋር በስልክ መነጋገራቸውን ነገር ግን መፍትሄ እንዳላገኙ ገልፀዋል።

ቢቢሲ የአምስት ሰዎች ህይወት ስለጠፋበት ጥቃት ከአፋር ክልል በኩል መረጃ ለማግኘት ወደ ክልሉ ኮምኒኬሽን ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ቢያደርግም ባለመነሳቱ ሳይሳካ ቀርቷል፤ ጥረታችን ግን ይቀጥላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *