የኛ ሰው በሊባኖስ
News

ኮሮናቫይረስ፡ በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለከፋ ችግር ተጋልጠናል እያሉ ነው

በሊባኖስ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ሙሉ በሙሉ የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሏል። የተጣለው የሰዓት እላፊ ከነገ ምሽት ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን እስከ ሰኞ ማለዳ ድረስ ይቆያል ተብሏል።

ከዚህ ቀደም የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ከተነሳ በኋላ ለአንድ ወር ያህል በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። ዜጎች ” ቤታቸው መቀመጥ አለባቸው አስቸኳይ ጉዳይ ካልገጠማቸው በስተቀር ወደ የትም መሄድ የለባቸውም” ያሉት የአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ማናል አብደል ሳማድ ናቸው።

እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ ከሆነ በአገሪቱ 870 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ ከእነዚህም መካከል 26 ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል።

የኛ ሰው በሊባኖስ
በሊባኖስ በርካታ ኢትዮጵያውያን በዝቅተኛ ሥራ ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ ያነጋገርናቸው ኢትዮጵያኖች ይናገራሉ። ስማቸው እንዳይገለፅ የጠየቁን በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን “ችግራችን የጀመረው ባለፈው ጥቅምት ወር የአገሪቱ ምጣኔ ሃብት በተጎዳበትና የዶላር መወደድ ሲጀምር ነው” ብለውናል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በየሰዉ ቤት ተቀጥረው የሚሰሩ የተባረሩበት፣ ደሞዛቸውን በግማሽ ቀንሰው መስራት የጀመሩበት እስካሁን ድረስም ሳይከፈላቸው የሚሰሩ መኖራቸውን ይገልፃሉ።

ቤይሩት፡ ባለፉት 7 ወራት 34 ኢትዮጵያዊያን ህይወታቸውን አጥተዋል
የኮሮናቫይረስ ክራሞት በኢትዮጵያ፡ ከመጋቢት እስከ ግንቦት
“ያለ ክፍያ ለመስራት የመረጡት ቢያንስ የተገኘውን እየበሉ በሕይወት መቆየት ይሻላል ያሉ ናቸው” በማለትም ይህንን ተቋቁመን አልፈነው ነበር ብለዋል።

የዓለምን ሕዝብ ያስጨነቀው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት “ሕይወታችንን ከድጡ ወደ ማጡ ከቶብናል” የሚሉት ኢትዮጵውያኑ፣ ልጅ ኣላቸው ልጃቸውን መመገብ፣ ቤት ኪራይ መክፈል ፈተና እነደሆነባቸው ይገልፃሉ።

ሊባኖስ የኮሮናቫይረስን ወረርሽኝ ስርጭት ለመከላከል ጥላው የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ ማንሳቷን ተከትሎ ያገኙትን ሰርቶ ለማደር ተስፋ ሰጥቷቸው የነበረ ቢሆንም ዳግም በወረርሽኙ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍ ማለቱን ተከትሎ መንግሥት ለተከታታይ አምስት ቀናት ከቤት መውጣትም መከልከሉን በመናገሩ ሌላ ስጋት እንደተደቀነባቸው ለቢቢሲ ያስረዳሉ።

እገዳው ለአምስት ቀናት የተጣለ ሲሆን ከዛሬ ምሽት ጀምሮ እስከ ሰኞ ማለዳ ድረስ የሚቆይ ነው በማለትም “ሳይሰራ እንዴት ቤት ኪራይ ይከፈላል?” ሲሉ ይጠይቃሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃሰን ዲያብ ፣ ባለፉት አራት ቀናት ብቻ 100 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ገልፀው ነው የአምስት ቀኑ የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉን የተናገሩት።

መንግሥት አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ላይ ያወጣውን መመሪያ ተግባራዊ የማያደርጉ ሰዎችንም ” ግዴለሽና ሃላፊነት የጎደላቸው” በማለት ወርፈዋቸዋል።

በሊባኖስ ተጥሎ የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ ከተነሳ በኋላ የአካላዊ ርቀት መጠበቅ ተግባራዊ እንዲሆን በማሳሰብ ሱቆችና የአምልኮ ስፍራዎች ተከፍተዋል። ይህ የሆነው ከሁለት ወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል።

በቫይረሱ የተያዙ አዳዲስ ሰዎች የተገኙት በአብዛኛው ከአገር ውጪ የነበሩ ሊባኖሳውያን በመመለሳቸው መሆኑ ተገልጿል።

ከአምስት ቀናት በፊት ከናይጄሪያ፣ ሌጎስ የመጡ ሁሉም ተሳፋሪዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው የአገሪቱ ጤና ሚኒስትር አስታውቆ ነበር።

በስፔን የ113 ዓመት አዛውንት ከኮሮናቫይረስ አገገሙ
የእንቅስቃሴ ገደቡ ከተነሳ በኋላ ዜጎች በመገበያያ ስፍራዎች አካላዊ ርቀታቸውን ሳይጠብቁ ሲገበያዩ የታዩ ሲሆን፣ በአውራ ጎዳናዎችም ላይ ከተጠበቀው በላይ በርካታ ሰዎች ወጥተዋል።

በሊባኖስ ተጥሎ የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ እየወደቀ የነበረው የአገሪቱ ምጣኔ ሃብትን ይበልጥ አባብሶታል ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ
ቢቢሲ ያነጋገራትና ሊባኖስ ውስጥ ለ12 ዓመታት መኖሯን የምትናገረው ኢትዮጵያዊት በበኩሏ “እኔም ሆንኩ ጓደኞቼ ፓስፖርትም ሆነ የመኖሪያ ፈቃድ የለንም” ስትል የስጋታቸውን መደራረብ ታስረዳለች።

ከዚህ በፊትም ቢሆን የተለያዩ ችግሮችን አልፌያለሁ ያለችን ይህች ሴት የአሁኑ ግን ከምንጊዜውነም የከፋ ነው ትላለች።

የኮሮናቫይረስ ከመከሰቱ በፊት ጀምሮ በሰዓት የሚከፈላት በግማሽ ተቀንሶ እየሰራች እንደነበር የተናገረችው ይህች ስደተኛ፣ የኮሮናቫይረስ ከመጣ በኋላም እጅጉን መታመሟን ታስታውሳለች።

“ምናልባትም ኮሮና ይሆናል፤ እንደ ጉንፋን ያለ ነው” ትላለች በወቅቱ የነበራትን ሕመም ስታስታውስ።

ሱዳን በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የኢትዮጵያን ሃሳብ አልቀበልም አለች
ለመመርመርም ሆነ ወደ ሆስፒታል ለመሄድና አገልግሎት ለማግኘት ፓስፖርትና የመኖሪያ ፈቃድ እንደምትጠየቅ በዚህም የተነሳ መታከም እንዳልቻለች ገልፃለች።

ለተከታታይ 11 ቀናት ሳል እንደነበራት የምትናገረው ይህች በሊባኖስ የምትገኝ ስደተኛ፣ በአንድ ክፍል ውስጥ ስምንት ልጆች ሆነው እንደሚኖሩና እርሷ በቫይረሱ ብትያዝ ወደ ሌሎቹ የመተላለፍ እድሉ ሰፊ እንደነበር ታስረዳለች።

“እኔ ብቻ ሳልሆን ሌሎችም ኢትዮጵያኖች አሉ ለአራትና ለአምስት በአንድ ክፍል የሚኖሩ” በማለትም ሕገወጥ ሆነው ሲኖሩ ኣለውን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጫና ታስረዳለች።

ታምማ በነበረበት ሰዓት ከስራዋ ገበታ መቅረቷን የምታስታውሰው ይህች ሴት፣ እርሷና ጓደኞቿ ሕገወጥ ሆነው በመስራታቸው ለተለያዩ ጥቃቶች ተጋላጭ መሆናቸውን ትናገራለች።

እነዚህ ኢትዮጵያውያን ሥራ በመፍታታቸው ያላቸውን እየተጠቀሙ፣ መስራት ባለመቻላቸው የቤት ኪራይ የሚከፍሉት እንደሚቸግራቸው ወደ ጎዳና እንወጣለን የሚል ስጋት እንዳላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ልጅ ያላቸው ሴቶች መኖራቸውን በመጥቀስም ያለስራ፣ የቤት ኪራይ ሳይከፍሉ መኖር ሕይወታቸውን ማክበዱንና ነገን በተስፋ ለማየት መቸገራቸውን ይገልፃሉ።

በቤትዎ በቀላሉ ስለሚሠራ ጭምብል ማወቅ የሚገባዎት ነጥቦች
በሊባኖስ ቤሩት በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ የሚናገሩት እነዚህ ስደተኞች በእስር ቤት፣ በሆስፒታል፣ ሞተው አስከሬናቸው ማቆያ ውስጥ ያለ በርካቶች መኖራቸውን ይናገራሉ።

እነዚህ ኢትዮጵያውያን የሊባኖስ የምጣኔ ሃብት ሁኔታ ወድቋል፣ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ደግሞ ሕገወጥ ሆኖ ለመስራትም ስላላስቻለ ወደ አገራችን ብንመለስ ፈቃደኛ ነን ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምን ይላል?
በቤሩት ሊባኖስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ቆንስል የሆኑት አቶ አክሊሉ ታጠረ ውቤ ለቢቢሲ እንደገለፁት በቤይሩት ሊባኖስ ያሉ ኢትዮጵያውያን ከአራት መቶ ሺህ በላይ ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ “በሕገወጥ መልኩ” እንደሚኖሩ ተናግረዋል።

በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አብዛኞቹ በሕጋዊ መንገድ ከመጡ በኋላ ከአሠሪዎቻቸው ጋር በተለያየ መንገድ ሳይግባቡ ሲቀሩ በመውጣት ቤት ተከራይተው “በሕገወጥ መልኩ” እንደሚኖሩ ይናገራሉ።

ከእነዚህ መካከል ሰማንያ በመቶ ያህሉ ሕጋዊ ፓስፖርት፣ የመኖሪያም ሆነ የሥራ ፈቃድ የሌላቸው መሆናቸውን ይናገራሉ። ይህ ሊሆን የቻለው ከአሰሪዎቻቸው ጋር ሲጋጩ እዚያው ጥለው በመውጣታቸው መሆኑን ያስረዳሉ።

በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ያነሷቸው ችግሮች እውነት መሆናቸውን የተናገሩት አቶ አከሊሉ ኤምባሲው በተለያዩ ማህበረሰብ ቡድኖችና በኃይማኖት ተቋማት በኩል ስለወረርሽኙ ግንዛቤ ለመፍጠር ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

አክለውም ዜጎች ችግር ላይ እንዳይወድቁና እርስ በእርሳቸው እንዲረዳዱ ድጋፍ የመስጠት ሥራ መስራታቸውን ይገልፃሉ።

በተጨማሪም ወደ አገር ቤት መመለስ ያለባቸው እስር ቤት፣ በተለያዩ መጠለያዎች ውስጥ የነበሩት ከአሁን በፊት ተመዝግበው የነበሩ 905 ዜጎችን ከሊባኖስ ለማስወጣት ከመንግሥት ጋር የመነጋገር፣ በረራ እና ለይቶ ማቆያ የማዘጋጀት ሥራዎች እየሰሩ መሆናቸውን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ነገር ግን ይላሉ አቶ አክሊሉ “ከእነዚህ መካከል ስማቸው ተላልፎ የጉዞ ሰነድ ተዘጋጅቶ፣ ፎቶ ኑና ተነሱ ሲባል፣ 54 ሰዎች ስራ አግኝተናል መሄድ አንፈልግም በማለት የመጣውን እድል ሌሎች እንዳይጠቀሙበትም አስቀርተዋል።” ብለዋል

ኢትዮጵያውያን በሊባኖስ የሚገጥማቸውን የምግብ ችግር፣ የቤት ኪራይ መክፈል አለመቻልን በተመለከተ የተለያዩ ኃይማኖት ማህበራትና ተወካዮች የሚሰሩትን ስራ እንደሚደግፉ ገልፀዋል።

ኤምባሲው የመኖሪያ ፈቃዳቸውን ሳያሳድሱ ቀርተው ቅጣት ለሚጠብቃቸው ዜጎች ከሊባኖስ መንግሥት ጋር ተነጋግሮ ምንም ያህል ዓመት ሳያሳድሱ ቢቆዩ የአንድ አመት ብቻ እንዲከፍሉ ስምምነት ላይ መደረሱንም አክለው ተናግረዋል።

አሁን ደግሞ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ይህ የቅጣት ክፍያ እንዲቀ ርእየተነጋገሩ መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል።

በቫይረሱ የሚያዙ ኢትዮጵያውያን ቢኖሩ ቀይ መስቀልና የአገሪቱ መንግሥት ኃላፊነት ወስዶ እንደሚያሳክም የገለፁት አቶ አክሊሉ፣ ምንም ዓይነት ሰነድ ለሌላቸውና የተለያዩ የጤና ችግር ለሚገጥማቸውም ኤምባሲው ደብዳቤ እንደሚጽፍላቸውና በዚያ መታከም እንደሚችሉ ጨምረው አስረድተዋል።

በሊባኖስ እስካሁን ድረስ በኮሮናቫይረስ የታመመ አንድም ኢትዮጵያዊ አለመኖሩን አቶ አክሊሉ ጨምረው ተናግረዋል።

Source: bbc.com/amharic

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *