Balderas
News Press Release

ባልደራስ : : ለሠላማዊና ህጋዊ ትግል ያለን ታማኝነት በሀሰት ውንጀላ አይገታም – አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ

 

የኢትዮጵያ ሕዝብ በተባበረ ትግል ጨቋኝ፣ ፀረ ኢትዮጵያና ፀረ-ዲሞክራሲ የነበረውን የሕወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ አስወግዶ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲሰፍን መጠነ ሰፊ ትግል ማድረጉ ይታወቃል፡፡ ይህን ተከትሎ በዶ/ር አብይ የሚመራው የኦዴፓ/ብልጽግና አመራር የህዝቡን የለውጥ ፍላጎት ከዳር ለማድረስ በአደባባይ ቃል ገብቶ ኃላፊነቱን መረከቡም ይታወሳል፡፡ ሆኖም ይህንን ወደ ነፃነትና ወደ ዲሞክራሲ የሚደረግ የሽግግር ጥያቄ በተገቢው ሁኔታ ለመመለስ በጣም አቅቶታል፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት በገሀድ እንደታየው የብልጽግና ፓርቲ እየተከተለ ያለው ፖለቲካ በተረኝነት መንፈስ የተቃኘ ነው፡፡ ለዚህም ነው ፓርቲው የኢትዮጵያን ፖለቲካ ማረጋጋት፣ የህዝቡን ሰላምና ፀጥታ ለማስከበርና ብሄራዊ መግባባት ለማስፈን ያቃተው፡፡

ፓርቲያችን ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ እውቅና አግኝቶ ለኢትዮጵያ የተሻለ የፖለቲካ አማራጭ ለህዝብ አቅርቦ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ ለወደፊት ምርጫው በሚቃረብበትም ጊዜ ደግሞ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲዎችን አጠናቅሮ ለኢትዮጵያ የተሻለ ፍኖተ ካርታውን ለሕዝብ በይፋ ለማቅረብ ናፍቁዋል፡፡ ይሁን እንጂ በዶክተር አብይ የሚመራው መንግስት ሃገሪቱን ለምርጫ ለማዘጋጀት በብቃት ሲሰራ አይታይም፡፡ ይልቁን ጽንፈኝነትና ተረኝነት እያደገ እያደገ መጥቷል፡፡

ሰሞኑን አዲስ አበባን ጨምሮ በአገራችን የተለያዩ ክፍሎች ጽንፈኞች በቀሰቀሱት አመጽ ከፍተኛ የሰብአዊ እልቂትና የአገር ሃብት ውድመት ተከስቷቱዋል፡፡ ባልደራስ ይህንን ውድመት የአንድ ጀምበር ወለድ ችግር አድርጎ አያየውም፡፡ ችግሩ ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት የተዘራው ክፉ ዘር መራራ ፍሬ ነው፡፡ የስርአተ ትምህርቶቻችን ችግሮች ፍሬ ነው፡፡ ገበሬ የዘራውን ያንኑ አይነት ያጭዳል፡፡ መቼሰ ገበስ ዘርቶ ጤፍ ሊያጭድ እንደማይወጣ ከሃያ ሰባቱ አመት ብሎም ተለውጠናል ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት ሁለት አመታት ከፖለቲካችን እርሻ ያመረትነው ነገር ግጭትና መፈናቀል ነው፡፡

ባልደራስ ከጥቂት ቀናት በፊት በከተማችን አዲስ አበባና በሌሎች የሃገራችን ክፍሎች የተነሳውን የጽንፈኞች ሁከት በጽናት ያወግዛል፡፡ በሰኔ 22 ቀን 2012 አመተ ምህረት በአዲስ አበባና በሌሎች የሃገራችን ክፍሎች የተነሳው ብጥብጥና ውድመት ያሳሰበው ፓርቲያችን የሰላም፣ የመረጋጋትና የፍትህ ጥሪ ለማድረግ ወስኖ መግለጫ ለማዘጋጀት የፓርቲያችን ፕሬዚደንትና ሌሎች ሃላፊዎች ሲዘጋጁ አቶ እሰክንድር ነጋ በፌደራል ፖሊስ ድንገት ታፍነው ከቢሮአቸው ተወስደዋል፡፡ አቶ እስክንድር ከቢሮአቸው ሲያዙ ይህንን መግለጫ ለማውጣት ደፋ ቀና ሲሉ ነበር፡፡ ፕሬዝደንት እስክንድር በ24/10/2012 10፡30 ላይ ከተያዙ በሁዋላ የአደረጃጀት ጉዳይ ኃላፊ የሆኑት አቶ ስንታየሁ ቸኮል በደቂቃዎች ልዩነት ወደ ቤታቸው በማቅናት ላይ እያሉ ከመንገድ ተይዘዋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የፓርቲያችን የክፍለ ከተማ አደራጅ የሆኑት ወይዘሮ ቀለብ ሰዩም በሰኔ 26 ቀን 2012 አ.ም በመንግስት ታስረዋል፡፡ ወይዘሮ ቀለብ ስዩም ማለት በቅርቡ በዋልታ ቴሌቪዠን ላይ ሲተላለፍ በነበረው ዶክመንተሪ በህወሃት የደረሰባቸውን ግፍ እያነሱ ሲያነቡ የታዩት አባላችን ናቸው፡፡ ወይዘሮ ቀለብ ቀደም ባለው ጊዜ ለመስማት የሚዝገንን ግፍ የተቀበሉ ሴት ናቸው፡፡

የዶክተር አብይ መንግስት የእኚህን ሴት ብሶት ለፖለቲካ ፍጆታ ለማዋል የተጠቀመበት መሆኑ ወይዘሮ ቀለብን አሳዝኖ ነበር፡፡ ፈጽሞ ሊታመን በማይችል መልኩ መሪዎቻችንን በሁከት ወንጅሎ አስሩዋል፡፡ አቶ እስክንድርና አቶ ስንታየሁ

በተያዙበት ጊዜ በፖሊስ ከፍተኛ የሆነ አካላዊ ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሁለት በሁለት ተኩል ገደማ በሆኑ ክፍሎች ከሌሎች እስረኞች በተለየ ሁኔታ እንዲታሰሩ ተደርገው እና ለሰው ልጅ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ተነፍገው በአለም አቀፍና በአገራችን ህግ ከተደነገገው የእስረኞች ሰብአዊ አያያዝ ውጭ ተይዘው በመከራ ላይ ይገኛሉ፡፡ በበቂ ሁኔታ አየር በማይገባባቸው ክፍሎች ውስጥ በመታሰራቸው ምክንያት በፓርቲያችን አመራሮች ማለትም በአቶ እስክንድር፣ በአቶ ስንታየሁ፣ በወይዘሮ ቀለብ ስዩምና እንዲሁም ቀጥሎ በታሰረው የክፍለ ከተማ አመራራችን አቶ ቢኒያም ላይ የጤና እክል ቢደርስ ፓርቲያችን የብልጽግናን ፓርቲ አመራሮችን በኃላፊነት ይጠይቃል፡፡ የተያዙት አባሎቻችን በህጉ መሰረት በወቅቱ ፍ/ቤት እንዲቀርቡና መብታቸው እንዲጠበቅ እንጠይቃለን፡፡ በተጨማሪም የሰላማዊ ትግል መሪ አቶ እስክንድር ነጋ እና አቶ ስንታየሁ ቸኮል በተያዙበት እለት በአዲስ አበባ በፖሊስ የተፈፀመባቸውን ከፍተኛ አካላዊ

ድብደባ ያስፈጸሙ እና የፈጸሙ አካላት ተጣርቶ በሕግ ፊት እንዲጠየቁ ፓርቲያችን በጥብቅ ያሳስባል፡፡

በባልደራስ አመለካከት ከላይ የተገለፀው በአመራሮቻችን ላይ የተፊፀመው ኢ-ሰብአዊነትን የተላበሰ አያያዝና የጥበቃ ሁኔታ በአጋጣሚ የተፈፀመ ሳይሆን ከዚህ ቀደም በፓርቲው ላይ በተከታታይ ሲደርስበት የነበረው ወከባና እንግልት ቀጣይ እርምጃ ነው፡፡ በባልደራስ ላይ የሚደርሰው ማቆሚያ የሌለው ግፍ የባልደራስ ፓርቲ በበልጽግና ፖለቲካ ላይ ያስመዘገበውን የፖለቲካ የበላይነት በፈጠረው መጥፎ ቅናትና ቁጭት የተፈፀመ የቂም በቀል ድርጊት ነው፡፡

ለነዚህ በደሎች እንደማሳያ እንዲሆነን ለአብነት የሚከተሉትን ሃቆች እናቀርባለን፡-

1ኛ/ በፓርቲው ምስረታም ሆነ ከዚህ ቀደም ይሰጡ የነበሩ ጋዜጣዊ መግለጫዎቻቸንን ማወክ፣ እንዳይከናወኑ መከልከልና ማዋከብ እንዲሁም ማንነታቸው የማይታወቁ ሰዎች ሁከት ሲፈጽሙ የመንግስት የፀጥታ ተቋማት በቅርብ እርቀት ሆነው ምንም አይነት ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ሳይፈለጉ ሲቅሩና ዳተኛ ሲሆኑ መቆየታቸው፣

2ኛ/ ለፓርቲው ቅድመ ምስረታ ስብሰባ በኢንተርኮንቴንታል ሆቴል ውሰጥ ፓርቲው ሊያደርገው የነበረውን ስብሰባ በመንግስት አካላት መታገዱ፣

3ኛ/ የአገር ባህል፣ እሴትና ትውፊት ማሳያ የሆኑ ቅርሶች በመንግስት በተደጋጋሚ ሲፈርሱና ሲወድሙ ፓርቲያችን በመቃወምና ለህዝብ ለማሳወቅ ባደረገው ያላሰለሰ ጥረት ምክንያት በመንግስት እስርን ጨምሮ ከፍተኛ እንግልትና መዋከብ እንዲደርስበት ሲደረግ መቆየቱ፣

4ኛ/ አዲስ አበባ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች የነበሩ ክፍት ቦታዎች ላይ በህገወጥ መንገድ እየተደረገ ያለውን የመሬት ወረራ በማውገዝ፣ እንዲሁም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከእለት ጉርሳቸው ቆጥበው የገነቡትን የጋራ መኖሪያ ቤቶች በግፍና በዘረኝነት ነጥቆ ተረኛ ነን ለሚሉ ማደሉን በመቃወም፣ የድሀ ድሆች የሆኑ ዜጎች በተለያዩ አካባቢዎች ያቆሙትን ጎጆ በማንአለብኝነት ሲያፈረሱ ለህዝብ በማጋለጣችን፣ በወረርሽኝና በክረምት ወቅት ሲያፈናቅሉ ፓርቲያችን በመቃወሙ በተለያዩ የመንግስት አካላት ከፍተኛ ማስፈራሪያና ጫና በአባላቱና በአመራሮቹ ላይ ሲደርስ መቆየቱ፡፡

5ኛ/ በአገራችን ላይ በተከሰተው የኮረና ወረርሽኝ (Covid 19) ምክንያት በህዝባችን ላይ ዘርፈ ብዙ ሰብአዊ ቀውሶች ተከስተዋል፡፡ ይህንን ከግንዛቤ የከተተው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ከበጀቱ ቀንሶ እርዳታ ለሚያሻቸው ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለማደል ሲንቀሳቀስ ከመንግስት ከፍተኛ አካል የመጣ ትዕዛዝ ነው በሚል የፀጥታ አካላት እርዳታውን እንዳንሰጥ ከልክለውናል፡፡ በተጨማሪም ፓርቲያችን በገንዘቡ የገዛውን የእርዳታ እህልና ቁሳቁስ በማገትና በአደባባይ እንዳይታደል በማድረግ በደል ተፈጽሙዋል፡፡

6ኛ/ በከተማችን በሚገኙ እድሜ ጠገብ ሀውልቶችና ታሪካዊ ቦታዎች አቅራቢያ ፓርቲያችን ጽዳት ለማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ራሳቸው በሚያበረታቱት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር መሰረት ፓርቲያችን የችግኝ ተከላ ለማካሄድ በሚያደርገው እንቅስቃሴ የፀጥታ ሀይሉ ሌላ ስራ የሌለው እስኪመስል ድረስ እግር በእግር እየተከታተለ ሲያደናቅፈን ቆይቷል፡፡ ለቅርሶቻችን ጠበቃ መሆናችን እያስጠቃን ነው፡፡ የምንሰራቸው ቅዱስ ስራዎች ሁሉ መንግስትን ሲያበሳጩ እናያለን፡፡ የተሻለ ራእያችን ስለምን ያስከስሰናል ለጋራው ቤታችን አስተዋጾ ለማድረግ ስንነሳ መንግስት ለምን ያሰቃየናል፡፡ ሊወገዝ የሚገባውና ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሊያወግዙት የሚገባ ተግባር ነው የመንግስት ተግባር፡፡

ከዚህ በላይ ያመላከትናቸው ድርጊቶች በፓርቲያችን አመራሮች ላይ በመንግስት ሲደረግ የቆየው መጠነ ሰፊ ወከባና እንግልት እየደረሰብን ያለው በተረኛነት መንፈስ የሚመራው የኦዴፓ/ብልጽግና አመራር የሚወስዳቸውን የተሳሳቱ የፖለቲካ እርምጃዎች ያለምንም ለዘብተኛነት መርህን መሠረት በማድረግ ስለምንታገል ነው፡፡ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማና በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች ጽንፈኞች ባደራጁትና በቀሰቀሱት መንጋ እየደረሰ ያለው ኢ-ሰብአዊ እልቂትና የአገር ሀብት ውድመት እንዲሁም እየቀጠለ ያለው የአካላዊና የስነልቦናዊ ወከባ መነሻው በአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ላይ በታቀደ መልኩ የተፈፀመውና በማናቸውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው የፖለቲካ ግድያ ብቻ እንደሆነ አድርጎ መንግስት ሙሉ በመሉ በሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎች አማካይነት ቀን ከሌሊት በማስተጋባት ላይ ይገኛል፡፡፡ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ይህን የመንግስት አቀራረብ አይጋራም፡፡ በፓርቲያችን አመለካከት በሰሞኑ አዲስ አበባን ጨምሮ በአገራችን በተለያዩ ቦታዎች በደረሰው ኢ-ሰብአዊ ፍጅትና የአገር ሀብት ውድመት በጽንፈኛ ብሔርተኞች ጉዳይ ፈፃሚዎች እንደተፈፀመ መንግስት

በገለፀው በሚታመነው የሃጫሉ ሁንዴሳ የፖለቲካ ግድያ አማካይነት የተጫረ ቢሆንም በክብሪት የተሞላውን ሳጥን በጋራ ባለቤትነት የያዙት ጽንፈኞች ብቻ ሳይሆኑ የኦህዴድ/ኦዴፓ/ብልጽግና አመራሮች ጭምር ናቸው፡ ፡ ለዚህ አባባላችን የሚከተሉትን ጭብጦች በአስረጂነት ማቅረብ ይቻላል፡-

1ኛ/ ከኦነግ ወደ ሃገር መግባት ጋር ተያይዞ ወደ አዲስ አበባ ከተለያዩ አካባቢዎች ለአቀባበል የመጡ በርካታ ዜጎች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ ሆኖም ይህንን ተገን በማድረግ የመጡ የጥፋት ኃይሎች ወይም አሸባሪዎች በከተማዋ መሀከል የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶችን ለማፈራረስ እንዲሁም በከተማዋ ዳርቻ በተለይ በቡራዩ የሚኖሩ ንፁሀን ዜጎችን በማሸበር “ወደመጣችሁበት ተመለሱ” በማለት ባስነሱት ረብሻ ዘግናኝ የሆኑ ግድያዎችን፣ የንብረት ማውደምና ዜጎችን ማፈናቀል ተከስቷል፡፡ ይህንን የሽብር ተግባር ተቃውሞ የወጣውን የአዲስ አበባ ህዝብ በተለይም ወጣቶችን መንግስት በፀጥታ ኃይሉ አማካኝነት ገድሎና አብዛኞችን አፍሶ በካምፕ ውስጥ ማሰሩ ይታወቃል፡፡ በወቅቱ የሽብር ተግባር የፈፀሙትን ግን እስከዛሬ በፍትህ አደባባይ አላስቆማቸውም፡፡

2ኛ/ በአዲስ አበባ ዙሪያ በተለይም በለገጣፎ አካባቢ ለበርካታ አመታት ይኖሩ የነበሩ ዜጎችን ማንነታቸው እየተመረጠ ሲገደሉ፣ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ስትቃጠል ዜጎች ላቀረቡት አቤቱታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልስ የሰጡት እጅግ ዘግይተው ነበር፡፡ መልስ በሰጡበትም ጊዜ የተጠቀሙበት አባባል ስለ ጉዳዩ አልሰማሁም አላየሁም የሚል ሆኑዋል፡፡ ከዚያም በኋላ ተገቢና ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ አላደረጉም፡፡ ይህ በወቅቱ በህግ የበላይነት ላይ የተፈፀመ ዳተኝነት ጽንፈኞች ይበልጥ እንዲበረታቱ አድርጓቸዋል፡፡

3ኛ/ ከዚህ ቀደም በእሬቻ ክብረ በዓል አከባበር ላይ ተደርጎ በማይታወቅ መልኩ ለበዓሉ በጽንፈኛ ብሔረተኞች ሐሰተኛ የታሪክ ትርክት ላይ በመመስረት በወቅቱ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የሆኑት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በአደባባይ ባደረጉት ንንግር ላይ “ከ150 አመት በኋላ ነፍጠኞች ኦሮሞን በሰበሩበት በፊንፊኔ መልሰን አከርካሪያቸውን በመስበር እንዳይነሱ አድርገናቸዋል” በማለት በማንነት ላይ የተመሰረተ የተቆራኙ ማህበረሰቦችን እርስ በርስ እንዲፋጁ የሚያነሳሳ ንግግር በአደባባይ ተናግረዋል፡፡

4ኛ/ ምክንያቱ በውል ባልታወቀ ሁኔታ አቶ ጅዋር መሀመድ ጥበቃዎቼ ተነሱብኝ በማለት ባስነሳው አመጽ መንግስት ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት ቁጥራቸው 86 የሆኑ ንፁሀን ዜጎች ሕይወት ተቀጥፏል፣ በበርካታ ዜጎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ በርካቶች ተሰደዋል፣ እንዲሁም ከፍተኛ መጠን የነበረው ንብረት ወድሟል፡፡ ይህንን ግፍ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወዲያውኑ መልስ መስጠትና ጥፋተኞችን ለህግ ማቅረብ ሲገባቸው እስካሁን ይህ አልተደረገም፡፡ በወቅቱ ስለተፈፀመው ድርጊት ቆይተውም ቢሆን መልስ በሰጡበት ጊዜ የተፈፀመው ነገር ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ሳይሆን ግጭት እንደሆነ አርገው አሳንሰው ነው ያቀረቡት፡፡ የተጣለባቸውን የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅና የማስጠበቅ ከፍተኛ መንግስታዊ ኃላፊነት ቸል በማለት ስለተፈፀመው አስከፊ ድርጊት ከ14 ቀን በኋላ ባቀረቡት ትንተና የሟቾችን የዘውጌ ማንነት በማብራራት ሌሎችን ለበቀል የሚያነሳሳ ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩ እንደ አንድ አገር መሪ አገሪቱ ላይ መከራ ሲዘንብ ምንም ባለመናገርና ለዜጎች መልእክት ለረጅም ጊዜ ባለመድረስ ግዴለሽነታቸውን አሳይተዋል፡፡ ይህም አልበቃ ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩና የመከላከያ ሚኒስትሩ ሀረር ላይ ግጭቱን አስመልክቶ ባደረጉት ስብሰባ ከበቡኝ በሚል ለብዙሀን ዜጎች እልቂትና ለንብረት መውደም ምክንያት የነበረን ግለሰብ ‹‹በመሃላችን ግጭት የለም፤ የቃላት አለመግባባት ተፈጥሮ ነው ፣ ትላንትም አብረን ስንሰራ ነበር ዛሬም ሆነ ነገ አብረን እንሰራለን›› በማለት አሸባሪዎቹን የሚያበረታታ ጥፋተኞችም ከህግ በላይ እንዲሆኑ የልብ ልብ የሰጠ ፍፁም ከመሪ የማይጠበቅ ድርጊት ሆኖ አልፏል፡፡

5ኛ/ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ የፓርቲያቸውን የኦዴፓ/ብልጽግናን ድርጅታዊ አቋም በማንፀባረቅ “አዲስ አበባ የኦሮሞ የፖለቲካ ትግል ማዕከል ናት” የሚል ንግግር በአደባባይ አሰምተዋል፡፡ ምክትል ከንቲባው የከተማ ግብርና በሚል በተዘጋጀ የከተማውን መሬት የማደል ፕሮግራም ላይ ያደረጉት ንግግር የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን በዜግነት ላይ የተመሰረተ የይዞታ ባለቤትነት የካደ ነው፡፡ ይህ የፖለቲካ አባባል ጽንፈኞች የተነሱበትን አላማ የሚያጠናክር፣ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ስጋት የጫረ በየጊዜው ለሚደረገው ብጥብጥ በማዳበሪያነት ያገለገለ ነው፡፡ በከተማው ውስጥ በተረኛነት ስሜት እየተስፋፋ ያለው የመሬት ወረራ የኦዴፓ/ብልጽግና ድጋፍ ያለው ስለመሆኑ የአደባባይ ሚስጢር ነው፡ ፡ የመሬት ወረራን በማጋለጥ አቤቱታ ያቀረቡ ሰዎች በወረዳ አመራሮች ከሚሰጣቸው መልስ ለመታዘብ የሚቻለው ይህንኑ ነው፡፡

ከላይ ከተራ ቁጥር አንድ እስከ አምስት የገለጽናቸው ማሳያዎች ከብዙ በጥቂቱ ሲሆኑ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት በአገራችን እየታየ ለሚገኘው ስርዓት አልበኝነትና ሲልም ሽብርተኛነት ቀጥተኛ ተጠያቂዎች እንደሆኑ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አበክሮ ያምናል፡፡

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በማንም ዜጋ ላይ የሚደረግ ግድያን በፍፁም ያወግዛል፡፡ በዘፋኝ አጫሉ ሁንዴሳ ላይ የተፈፀመውንም ግድያ ያወግዛል፡፡ ገዳዮቹንም በፍትህ እንዲዳኙ አበክሮ ይጠይቃል፡፡

እንደሚታወቀው በህገ መንግስቱ ውስጥ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ማዕከል እንደመሆኑ ልዩ ጥቅም ይከበርላታል የሚለውን የህገ መንግስቱን አንቀጽ ባልደራስ በጽኑ ይቃወማል፡፡ ይህንን አንቀጽ ብቻ ሳይሆን ባልደራስ ህገ-መንግስቱ ሙሉ በሙሉ ተሽሮ አዲስ ህገ-መንግስት እንዲዘጋጅ በተደጋጋሚ ሲገልጽ እንደቆየ ይታወቃል፡፡ ወደፊትም ትግሉን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ኦህዴድ ብልጽግናን ከመቀላቀሉ በፊት በአዲስ አበባ ላይ ፍፁም የተሳሳተ ደረጅታዊ አቁዋም ‹‹አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት›› በሚል መግለጫ ማውጣቱ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ይህም አቁዋም ጽንፈኛው አካል አሁን እያደረሰ ላለው ሽብር እንደመነሻነት ወስዶታል፡፡ ይህ ጉዳይ ለሃገራችን ህልውና ከፍተኛ ኪሳራ ያመጣል፡፡ የሚሻለውና ለኢትዮጵያ ሃገራችን መጻኢ እድል የሚበጀው የተባበረች ኢትዮጵያን በጋራ መገንባት ነውና ባልደራስ ለዚህ ሳይታክት ይሰራል፡፡

ባልደራስ የአዲስ አበባን ሕዝብ ለፖለቲካ ተሳትፎ ሲያደራጅ ቆይቷል፡፡ አሁንም በዚሁ ህጋዊና ሰላማዊ መንገድ ህዝብን ማደራጀት ይቀጥላል፡፡ ፓርቲው የቆመለትና የተቋቋመበት አላማም ይህ ነው፡፡ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የዘፋኝ ሀጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ ለደረሰው የህይወት፣ የአካልና የንብረት ጉዳት ሙሉ ለሙሉ ተጠያቂሙ መንግስት መሆኑን በድጋሚ እየገለፀ የሚከተሉትን ህጋዊ ጥያቄዎችን ያቀርባል፡፡

1ኛ/ ለጠፋው የንፁሀን ዜጎች ህይወት፣ ለንብረታቸው መውደም፣ ስደት፣ የስነ ልቦና ቀውስና የኢኮኖሚ ድቀት መንግስት ሙሉ በሙሉ ኃላፊነት በመውሰድ ህይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦቻቸው ተገቢውን ካሳ በመክፈል፣ የተሰደዱ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ተመልሰው ሰላማዊ ህይወት እንዲጀምሩ አስፈላጊውን ሁሉ በአስቸኳይ እንዲያደርግና እንዲሁም አስተማማኝ ፀጥታና ሰላም የማስፈን ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ እንጠይቃን፡፡

2ኛ/ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፀጥታ ምክር ቤት በሚል ከከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር ባደረጉትና በቴሌቭዥን በተላለፈ ውይይት ላይ የጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ሚኒስቴርና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር የሰጡት አስተያየት የተጠርጣሪዎችን በፍርድ ፊት ንፁህ ሆኖ የመታየት ሰብአዊ መብታቸውን የጣሰ ከመሆኑም በላይ እንደቀድሞው ከፍትህ በፊት ዜጎችንና ድርጅቶችን የማሸማቀቅና የዳኞችን ነፃነት በእጅጉ የሚጋፉ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ በመሆኑም በእለቱና ከዚያ ተከትሎ የተከሰቱት ጉዳዮችን የሚያጣራ ገለልተኛ አጣሪ አካል ተቋቁሞ የደረሰውን መጠነ ሰፊ ውድመት እንዲመረመር አበክረን እንጠይቃለን፡፡

3ኛ/ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተከሰተው የንብረት መውደም የፀጥታ አካል ምንም አይነት ምላሽ ሳይሰጥ ቆሞ ተመልካች እንደነበረ የከተማው ነዋሪ የሚያውቀው ሀቅ ነው፡፡ እንደ ባልደራስ እምነት ይህ ፍፁም ተገቢ ያልሆነ ቸልተኛነትና እሱን ተከትሎ የመጣ የማህበረሰቡ እራሴን ከሽብርተኛ ጥቃት ልከላከል ብሎ መነሳት ፍፁም ተፈጥሯዊ ግዴታ በመሆኑ የሚደገፍ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ፖሊሶችና የፀጥታ ኃይሎች በተደጋጋሚ በከተማ ውስጥ የተከሰተውን ሁከት በሚመለከት የከተማውን ፀጥታ በማስከበር ረገድ በተደጋጋሚ ቸልተኛነት ማሳየታቸውን ነዋሪው ሕዝብ በትዝብት ተመልክቶታል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት በአዲስ አበባ ውስጥ በፖሊስነት እየተመለመሉና እየሰለጠኑ ያሉት የከተማው ነዋሪ ስነ ልቦና የሌላቸውና ከሌላ አካባቢ የመጡ በመሆናቸው እንደሆነ ባልደራስ በጽኑ ያምናል፡፡ ይህ ሁኔታ መለወጥ እንደሚኖርበትና የአዲስ አበባ ሠላምና ፀጥታ ከነዋሪዎቿ በተውጣጣ የፖሊስ ኃይል መጠበቅ እንዳለበት ፓርቲያችን በጽናት ያምናል፤ ለዚህም ይታገላል፡፡

በዚህ አጋጣሚ የአዲስ አበባ ነዋሪ በባልደራስ ሳይሆን በራሱ ተነሳሽነት እራሱን ለመከላከል የወሰደውን እርምጃ ባልደራስ እያደነቀ፣ ይህ የአዲስ አበባ ህዝብ እራሱን ለመከላከል የወሰደውን እርምጃ ለጽንፈኞችና ለደጋፊዎቻቸው የእግር እሳት እንደሆነባቸው ይገነዘባል፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪ ለወደፊትም ከሞግዚት አስተዳደር ነፃ ለመውጣት እራሱን በሰላማዊ ትግል አደራጅቶ አዲስ አበባን ራሷን የቻለች ፌዴራላዊ ክልል እንድትሆን ሊታገል ይገባል፡፡

በመጨረሻም ገዢው ፓርቲ የህግ የበላይነትን ባለማስከበሩ የተፈጠረውን ከፍተኛ በሃገር ደረጃ የደረሰ ውድመትና ክስረት በሌሎች ላይ ለማላከክ የተጉዋዘበት ርቀት እና የጦስ ዶሮ የማድረግ ተውኔት ክሹፍ ሃሳብነት ከትናንት አንዳች ያለመማር ውጤት መሆኑና ባልደራስ ለማስገንዘብ ይወዳል፡፡ የድርጅታችን አመራሮችም ከህግ ውጪ የፈጸሙት አንዳች ወንጀል የለም፡፡

ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ለተሻለች ኢትዮጵያ ትግሉን የሚቀጥል ሲሆን በመሪዎቻችን ላይ የሚደረግ ግፍ ከትግላችን ወደኋላ

እንድናፈገፍግ አያደርገንም፡፡ የፓርቲያችን መሪ አቶ እስክንድር ነጋና አብረውት የታሰሩት ጓዶቹ በሀሰት ተወንጅለው ሲታሰሩ ይህ የመጀመሪያ አይደለም፡፡ ጀግናው እስክንድር በህወሓት /ኢህአዴግ ዘመን በኢትዮጵያ ሐቀኛ ዲሞክራሲና ለእውነተኛ ህገ መንግስታዊ ስርዓት በሰላማዊ መንገድ ሲታገል በሀሰት ተወንጅሎ ከ1ዐ ዓመት በላይ መታሰሩ ይታወሳል፡፡

አሁንም የቀጠለው ይኸው የቀድሞ በሐሰት ወንጅሎ የማሰር አባዜ ነው፡፡ ይህ እውነታ የሚያመለክተው ገዢው ፓርቲ ለራሱ ብልጽግና የተሰኘ የዳቦ ስም ቢሰጥም፣ በተግባር ከብልጽግና ይልቅ ኢህአዴግ ቁጥር ሁለት ሆኖ መቀጠሉን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ እውነት ለተወሰነ ጊዜ ተሸፍኖ ይቆይ ይሆናል እንጂ አይጠፋም፡፡ የፓርቲያችን አመራሮች የሚያምኑበት እውነት ነፃ ያወጣቸዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ሃገራችን ኢትዮጵያ በከፍተኛ ውጥረት ላይ ትገኛለች፡፡ በአንድ በኩል የአባይ ጉዳይ፣ በሌላ በኩል የክልልነት ጥያቄ፣ ድህነትና የፖለቲካ አለመግባባት ሃገራችንን ወጥረት ውስጥ ከቱዋታል፡፡ በዚህ ጊዜ መንግስት ልበ ሰፊ ሆኖ ለተሻለ ሽግግር መስራት ሲገባው ጽንፈኝነትን ሲያራምድ እንዲሁም ፖለቲከኞችንና የመብት ታጋዮችን ሲያስር ይታያል፡፡ ይህ ሁኔታ ሃገሪቱን ወደ በለጠ አለመረጋጋት ከመውሰዱ በፊት ሊቆም ይገባል ብሎ ፓርቲያችን ያምናል፡፡

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በተከሰተው ቀውስ ወዳጅ ዘመዶቻችውን ላጡ መጽናናትን፣ አካላቸው ለተጎዳ ቶሎ ማገገምን፣ ንብረታችው ለጠፋ ካሳን ይመኛል፡፡

ፈጣሪ አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ!

ድል ለዴሞከራሲ!

ሃምሌ 1 ቀን 2012 አመተ ምህረት

አዲስ አበባ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *