አገራችን ኢትዮጵያ ብዙ የተፈጥሮ ሃብት በውስጧ አምቃ የያዘች አገር ናት። ይሁን እንጂ የተለያዩ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በፈጠሩት ተግዳሮቶች ምክንያት ዕምቅ ሃብቷን በበቂ መጠቀም ያልቻለች አገር መሆኗ ደግሞ እሙን ነው። ከነዚህ እምቅ የተፈጥሮ ሃብቶቿ አንዱ የዓባይ ውሃ ነው።
ዓባይ የኢትዮጵያን ለም አፈር ተሸክሞ አገር አቋርጦ በመጓዝ የታችኛው ተፋሰስ አገሮችን ሲመግብ መኖሩ ይታወቃል። እነዚህ ጎረቤት ተፋሰስ አገሮች የዓባይን ውሃ በመጠቀም ዘመናዊ እርሻና የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት አገራቸውን በከፍተኛ ደረጃ አበልጽገዋል። ያለማንም ጠያቂ ግድብም ገድበው እየተጠቀሙ ይገኛሉ።
ግብፆች ወደ ሃገራቸው የሚፈሰውን 86% ውሃና ተሸክሞት የሚነጉደውን ለም አፈር በረከት የሚሰጣቸው ጥቁር ዓባይ የሚመጣው ከኢትዮጵያ መሆኑን በትክክል ያውቃሉ። ይሁን እንጂ የውሃው ባለቤት እኛ እንጂ ኢትዮጵያ አይደለችም በማለት በዓለም መድረክ ላይ ከግብረአበሮቻቸው ጋር በመሆን የዓለምን ሕዝብ ለማሳመን ከፍተኛ የገንዝብና የሰው ኃይል መድበው ሲዘምቱብን ኖረዋል።
ለልጆቻቸውም ዓባይ መነሻውም ግብፅ ውስጥ፣ መድረሻውም ግብፅ እንደሆነ አድርገው የተሳሳተ ትርክትን ሲያስተምሯቸው ኖረዋል። ግብፅ ያመቸኛል ባለችበት ጊዜም ዓባይን ከምንጩ ለመቆጣጠርና ኢትዮጵያን አዳክማ ወይም አጥፍታ ለመግዛት በተለያዩ ጊዜያት ወታደር አዝምታ፣ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ከፍታ ነበር።
ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ የአገሩ ዳር ድንበር ሲነካበት ቀፎው እንደተነካበት ንብ በአንድ ላይ ተነስቶ እንዳመጣጧ በተደጋጋሚ አሳፍሮ መልሷታል። ግብፅ ኢትዮጵያ የሌለችበትን የቅኝ ግዛት የውሃ ክፍፍል ውል አገራችን እንድትቀበል ለማድረግ ከፍተኛ ወጭ በማውጣት ይኽው እስካሁን ትሞግታለች። ይህንኑ ለማሳካት በዲፕሎማሲው ረገድም የማትፈነቅለው ድንጋይ የላትም። አገሯን በእርሻና በመብራት ኃይል ስታለማ ኢትዮጵያ ግን በተደጋጋሚ በከፍተኛ ድርቅና ረሃብ ትጠቃለች።