ዶክተር-ሲሳይ-መንግስቴ
Opinion

“መንግሥት ህወሓት እየሠራ ያለውን ግፍና በደል ሊቀለብስ የሚችል ሥራ እየሠራ አይደለም” – ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ

መንግሥት ይህንን ሊቀለብስ የሚችል ሥራ እየሠራ አይደለም ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ አስታወቁ።
‹‹በጉዳዩ የፌዴራል መንግሥት ብዙ ጊዜ ጥያቄና ወቀሳ ቀርቦበታል። ዝምታው ግን ለምን እንደሆነ አይገባኝም።በተለይም የትግራይ ክልል የተደራጀ ኃይል ያለው እንደመሆኑ ያንን መመከት የሚያስችል እንቅስቃሴ እየተደረገ አይደለም›› ብለዋል።

ዝምታው ህዝቡ እንዳይጎዳ ከማሰብ የተነሳ ቀስ በቀስ አመራሩን ማዳከም የፈለገ እንደሚመስል በመጠቆምም፤ ሂደቱ በአንድ በኩል ትክክል ነው። ነገር ግን አንድ ቦታ ላይ ከሚወሰደው ዕርምጃ አኳያ አድሎ ሊመስል እንደሚችል አመልክተዋል።
የቀድሞ የሱማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አብዲ መሀመድ ኡመር በሱማሌ ክልል ችግር በፈጠረበት ጊዜ ወዲያውኑ ዕርምጃ መወሰዱን በምሳሌነት አስታውሰው፤ ትግራይ ላይ እንዲህ ዓይነት ችግር ሲፈጠር ለምንድን ነው ዝም የሚባለው? ሲሉም ጠይቀዋል።

ህወሓት በራያና በወልቃይት ህዝብን እያፈነ ይገኛል፣ እየተፈፀመ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው፤ ጉልበት ያለው እንዳሻው እያፈነ ሊቀጥል፤ ብዙም ጉልበት የለውም ተብሎ የሚታሰበውን ዕርምጃ የሚወሰድበት ሁኔታ መኖር የለበትም ብለዋል።
የህውሓት አክራሪ አመራር ላይ ጠበቅ ያለ ህጋዊ፣ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ዕርምጃ መወሰድ አለበት። በሂደት ደግሞ እያዳከመ ሄዶ ህዝብንና ድርጅቱን ለይቶ ጠንከር ያለ ዕርምጃ የሚወሰድበትን ሁኔታ ማሰብ በጣም አስፈላጊ እንደሆነም አመልክተዋል።

ህወሓቶች ምርጫ እናደርጋለን ብለው እያደረጉት ያለው የማዋከብ ሥራ በህዝቡ ላይ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ሁሉ ሌላ ተጨማሪ የጎን ውጋት ሆኖበታል። በምርጫ ያልተመዘገበ ሰው በክልሉ መኖር እንደማይችል ተነግሮታል። በተለይም ፍቃደኛ ያልሆነ ወጣት በቤተሰቡ በኩል በግድ እንዲመዘገብ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

‹‹ምርጫውን ልክ የትግራይ ህዝብ የነፃነት መገለጫ አድርገው ነው እየቆጠሩት ያሉት። ህወሓት የአገሪቱን ህገመንግሥት ብቻ ሳይሆን የራሳቸውን ህገመንግሥት ጭምር የሚጥስ ሥራ እየሠራ ነው›› ሲሉም ነው የተናገሩት።

የክልሉን ልዩ ኃይል ቁጥር በመጨመር የማሳፈንና የማሰር ሁኔታ ተስፋፍቷል ያሉት ዶክተር ሲሳይ፤ በተለይ ሰሞኑን ‹‹ምርጫውን ይቃወማሉ፣ ያደናቅፋሉ ብለው የሚያስቧቸውን በርካታ ቁጥር ያላቸውን ወጣቶችን እያሰሩና እያስፈራሩ ናቸው። ማሳደዱና እንግልቱ በጣም በሚያስፈራ ሁኔታ የበለጠ ጨምሯል ብለዋል።

ወደትግራይ ክልል ለመሄድ በየአምስት ኪሎ ሜትሩ ባሉ ኬላዎች ላይ አስፈሪ ፍተሻ ይደረጋል፤ በገዛ አካባቢሽ ላይ ደርግ ያደርገው እንደነበረው ገበያ ቦታ ሳይቀር መታወቂያ ይጠየቃል። ከአንዱ ቀበሌ ወደ ሌላኛው ቀበሌ ለመንቀሳቀስ መታወቂያ ካልያዝሽ ከፍተኛ እንግልት ይደርሳል ሲሉም ተናግረዋል።

ራያ ቆቦና ራያ አላማጣ የተዋሃደ ቤተሰብ ቢሆንም በሁለት ክልሎች የሚተዳደሩ ናቸው። በመሆኑም የራያ ቆቦ አካባቢ ነዋሪ የአማራ ክልል መታወቂያ ይዞ ከተገኘ ተጨማሪ እንግልት ይገጥመዋል። እንዲህ ዓይነት ግፍና በደል በጣም ጎልቶ ወጥቷል። በመሆኑም ምርጫው ህገወጥ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ህዝቡን እያንገላቱበትና እያሰቃዩበት ያለ በመሆኑ በእጅጉ የሚወገዝና በእዚህ መልክ መቀጠል የማይገባው ነው ሲሉም አመልክተዋል

Source: አዲስ ዘመን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *