National Movement of Amhara
Press Release

ገዥው ፓርቲ የውስጥ ልዩነቱን ወደ ሕዝብ ለሕዝብ ግጭት ለማውረድ የሚያደርገውን ኃላፊነት የጎደለው ሙከራ ያቁም! ከ(አብን) የተሰጠ መግለጫ!

ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ!

ገዥው ፓርቲ የውስጥ ልዩነቱን ወደ ሕዝብ ለሕዝብ ግጭት ለማውረድ የሚያደርገውን ኃላፊነት የጎደለው ሙከራ ያቁም!
**

ሰሞኑን በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አውራ ጎዳና ከተማ ተፈጥሮ በነበረ ግጭት የበርካታ ሰዎች ሕይወት ማለፉ ይታወቃል፡፡ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሕይወታቸው ላለፉ ወገኖቻችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ሐዘኑን ይገለጻል፤ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን ይመኛል፡፡

የአማራን ሕዝብ ማኅበራዊ እረፍት ይነሳል፣ በሂደትም ኢትዮጵያን ይበትናል ተብሎ ስራ ላይ የዋለው ሕገ-መንግሥት እና የአስተዳደር መዋቅር የአማራ ሕዝብ ከፍተኛ ዋጋ የከፈለበት እና እየከፈለበት የሚገኝ ቢሆንም ሥርዓቱ ሁሉንም ኢትዮጵያውንን ከባድ ዋጋ እያስከፈለ እና የጋራ ቤታችን የሆነችውን ሀገራችን ኢትዮጵያን ኅልውናም ከመቸውም ጊዜ በበለጠ አደጋ ላይ እንደጣለ አብን ያምናል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያን ለመበትን፣ ኢትዮጵያውያንን በብሔር፣ በቋንቋ፣ በኃይማኖት ከፋፍሎ የማያቋርጥ የቀውስ አዙሪት ውስጥ ለማኖር በአሸባሪው ትሕነግ ስራ ላይ በዋለው ሥርዓትና መዋቅር ምክንያት የንጹሃን ደም በከንቱ ሳይፈስ የነጋ ሌሊት፣ የመሸ ቀን የለም፡፡

ሰሞኑን የአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ በምንጃር- ሸንኮራ ወረዳ፤ አሞራ ቤት ቀበሌ፤ አውራ ጎዳና ከተማ ውስጥ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ የሚታይ ሆኖ ሳለ ግጭቱን የተለየ ክስተት ለማስመሰል እና ችግሩን ወደ ሕዝብ ለሕዝብ ግጭት ለማውረድ የተሄደበትን ርቀት አብን ያወግዛል።

ገዥው ፓርቲ በውስጡ ያሉ ልዩነቶቹን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት ሲገባው፣ የዜጎችን ሞት በማስታከክ ሕዝብ ከሕዝብ የሚያጋጭ እና ሀገራችንን ወደከፋ ቀውስ ውስጥ የሚከት የመግለጫ ጋጋታ ማውጣት ኃላፊነት የጎደለው እና እጅግ አደገኛ አካሄድ በመሆኑ በቶሎ እንዲታረም አብን አጥብቆ ይጠይቃል::

ሕብረ-ብሄራዊነት የሀገር ጌጥ መሆን የሚችለው በሴራም ሆነ በብልጣብጦች መንገድ ሳይሆን በእውነተኛ አስቻይ አማካይ የፖለቲካ መንገድ ነው፡፡ ወንድማማችነት የሚኖሩት የሕዝብ እውነታ እንጂ በየመድረኩና በየመግለጫው የሚደሰኩሩት ልፋፌ ሊሆን አይገባም፡፡

ኢትዮጵያ የበርካታ ማንነቶች ሀገር ነች፡፡ በቋንቋ፣ በባህል፣ በኃይማኖት፣ ብንለያየም አንዳችን ከሌላችን የሚያስተሳስሩን ማህበራዊ አንጓዎች ብዙ ናቸው፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ የጋራ ቤታችን ነች፡፡ ኢትዮጵያ በመከባበር ስሜት የሁላችንም መሆን ካልቻለች የማናችንም ልትሆን አትችልም፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከልሂቃን ሽኩቻ ወጥቶ ዜጎች የመብት ባለቤት የሚሆኑበትን አስቻይ የፖለቲካ ሥርዓት መፍጠር ካልተቻለ ከፊት ለፊታችን ያለው ሀገራዊ አደጋ ከእስካሁኑ የከፋ ከባድ ዋጋ እንዳያደስከፍለን ያሰጋል፡፡

የትኛውንም የፖለቲካ ቅራኔ ሰበብ እየፈጠሩ ወደሕዝብ ለሕዝብ ማውረድ ከፍ ሲል መንግሥታዊ ኃላፊነትን የመዘንጋት፤ ዝቅ ሲል የፖለቲካ ሸፍጥ ነው፡፡ ከአሸባሪው ትሕነግ የውድቀት ገፊ-ምክንያቶች መማር ለራሱ ለገዥው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ለሕዝብና ለሀገርም ይጠቅማል፡፡

የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ በኢትዮጵያ የሀገር ምስረታም ሆነ የሀገር-ግንባታ ታሪክ ውስጥ የገዘፈ ሚና ያላቸው ከቋንቋ ማንነት በላይ በጋራ የሚጋሯቸው ማህበራዊ ትስስራቸው የጎላ ሁለት ቋንቋ ተናጋሪ አንድ ቤተሰብ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው አብን በዚሁ መግለጫው ላይ “በሁለቱ የሸዋ ህዝቦች መካከል” የሚል አግባብ ያለው አገላለጽ የተጠቀመው፡፡ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ገዥው ፓርቲ በውስጡ ያለበትን የፖለቲካ ልዩነት ተከትሎ ግጭትን ወደሕዝብ ለሕዝብ ለማውረድ የሚያደረገው ኃላፊነት የጎደለው ሙከራ በሕግም ሆነ በታሪክ ያስጠይቀዋል፡፡

በርግጥም የሚያስጨንቀን የዜጎች ሞት ከሆነ የተፈጠረውን ግጭት እና የሕይወት መጥፋት በተገቢው ገለልተኛ አካል ማጣራት እየተቻለ ጉዳዩን የተለየ ምስል ለመስጠት፣ በግልፅ አማራ ክልል ውስጥ ያለን የአስተዳደር ክልል ሌላ ስያሜ በመስጠት እና ባልተገባ ሁኔታ የእኔ ክልል አካል ነው በማለት ጸብ አጫሪ የሆኑ መግለጫዎችን መስጠት በአስቸኳይ እንዲቆም እየጠየቅን ገዥው ፓርቲ እና የሚመራው መንግሥት የሕዝብን ደኅንነት አደጋ ላይ ከሚጥሉ እንቅስቃሴዎች እራሱን እንዲያቅብ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

ገዥው ፓርቲ የውስጥ ልዩነቱን ወደ ሕዝብ ለሕዝብ ግጭት ለማውረድ የሚያደርገውን ኃላፊነት የጎደለው ሙከራ ያቁም!

መጋቢት 27/2014

አዲስ አበባ፣ ሸዋ – ኢትዮጵያ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *