juhar mohammed
Analysis Politics

በጀዋር የሰሞኑ  ቃለ መጠይቅ ላይ አንዳንድ ነጥቦች

Aklilu Wondaferew

ከአክሊሉ ወንድአፈረው

June 1, 2022

 

ጥንካሬውና አበረታች ጎኑ

ጀዋር እንደ አንድ የኦሮሞ ብሄረተኛ ኢትዮጵያና ኢትዮጰያዊነትን ሁሉ ሲያጥላላ ዝቅ አድርጎ ሲያሳይና ለኦሮሞ ማህብረረስብ የችግሩ የስቃዩ የኋላቀርነቱ….ወዘተ ምክንያት ሁሉ በኢትዮጰያ ውስጥ መቆየቱ እንደሆነ አድርጎ ሲተርክ  ረጅም ጊዜ ቆይታል፡፡ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይም ኦ ኤም ኢን (OMN) የተሰኘውን የቴሌቪዝን ጣቢያ ከመሠረተና መምራት ከጀመረ በኋላ በዚህ አኳያ የአንበሳውን ድርሻ ጀዋር ይዞ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ አንድ ሌላ የኦሮሞ ብሄረተኛ ፖለቲከኛ (አቦ ሌንጮ ባቲ) “የኦሮሞ ብሄረተኛነትን ለማጠናከር ኢትዮጰያንና ኢትዮጰያዊነትን አጣጥለናል ዝቅ አድርገናል፣ አዳክመናል (ዲ ኮንስትራክት አድርገናል) እንዳለው ጀዋርም በዚህ ጎዳና ሲጓዝ ረጅም ጊዜ ቆይቷል ፡፡

ከረጅም ጊዜ በኋላ በግንቦት 18፣2014 (ሚይ 26፣ 2022)  ከኡቡንቱ ቴሌቪዥን ጋር ባካሄደው ቃለ መጠይቁ ጀዋር “ሀገራችን”  የሚለውን ቃል በተደጋጋሚ መጠቀሙ “ በሀገራችን “ (ኢትዮጰያ) ውስጥ የምንገኝ ሁሉ የጋራ የሚባል ነገር እንዳለን ማመኑ ለመግባባት የመጀመሪያውና መሠረታዊውን እንድ በጎ እርምጃ ተራምዷል ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡

ይህ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ብሎ ባይጠራትም ይህችው “ሀገራችን” በየቦታው ተቆሰቁሶ እየተቀጣጠለ የሚገኝ ሰፊ ችግር ውስጥ እንደሆነች ከመገንዘብም አልፎ የአንድ አካባቢ ሰላም ማጣት ይዋል ይደር አንጂ የሌላውንም ሰላም ማጣት እንደሚያስከትል መግለጹ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ደህንነትና ህልውና በተለያየ ደረጃም ቢሆን የተያያዘና የተጋመደ መሆኑን መቀበሉና አጽንዖት ስጥቶ ማሳየቱ ከስሜት ባሻገር እውነታውን ለመመርመር በር ስለሚከፍት ጠቃሚ ጅማሮ ነው፡፡

የሀገራችንን ውስብስብ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ በውይይት መፈታት ይኖርባቸዋል የሚለው አቋሙ እንደ መርህ እኔም የምስማማበት ጉዳይ ነው፡፡ ችግሩ ዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ ሲገባ ብቻ ሳይሆን በርግጥ ሰላምንና ችግርን በውይይት መፍታት በአንድ በኩል ብቻ በሚካሄድ ምኞትም ሆነ ጥረት ተፈላጊውን ውጤት ሊያስገኝ የመቻል ዕድሉ እጅግ ዝቅተኛ ነውና ይህንንም በግንዛቤ ውስጥ ማስገባቱ ይጠቅማል፡፡

ተፋላሚ ወገኖች ሁሉ የሰላም ፍላጎት አላቸው የሚለው በየዋህነት አመለካከት ለተጠቂነት እንዳይዳርግ ተገቢውን ጥንቃቄ ሁሉ ማድረግ እንደሚያሻ ግልጥ ነው፡፡ ሁሉንም ነገር ከሚገባው ባላይ መጠራጠር ወደፊት ለመራመድ አስፈላጊ የሆነውን ድፍረት የተሞላው ጉዞ ከማካሄድ የሚያግት የሥነ ልቦና እንቅፋት የመሆኑን ያክል ሁሉንም ነገር እንደወረደ መቀበልም የራሱ ችግር አለውና  በሀገራችን ሁኔታ ስለሰላም፣ መግባባትና ድርድር ሰናነሳ ሚዛን የጠበቀ እርምጃ ጠቃሚነቱ ከፍተኛ  ሆኖ ይታየኛል፡፡

በአጠቃላይ ጀዋር ያነሳቸውና ለመንደርደሪያነት ሊሆኑ የሚችሉ ጋባዥና አበረታች ነጥቦች ሆነው ካገኘኳቸው ውስጥ እነዚህን ከላይ ያነሳኋቸውን ተመልክቻለሁ፡፡

በጀዋር ከተነገሩት ውስጥ  መስተካከል አለባቸው ቢያንስ ይበልጥ ማብራሪያን ይሻሉ ከምላቸው፡ውስጥ የሚከተሉትን ልጥቀስ

የሰሜኑ ጦርነት

ሰለሰሜኑ ጦርነት ጀዋር ሁለት ዋና ዋና ነጥቦችን አንስቷል

ጀዋር ጦርነቱ በገዥው ብልጽግና  የአያያዝ ጉድለት ምክን ያት የመጣ እንደሆነና  ለየት ያለ  ሂደት ህወሓትን ማካተት ቢቻል ኖሮ ጦርነቱ ባልተቀሰቀስ ነበር ይላል፡፡ በሀገራችን ውስጥ ከ 27 ዓመታት የግፍ አገዛዝ በኋላ ለውጡ በዋናነት እውን የሆነው በሕዝብ የ27 ዓመታት ተከታታይ ትግልና በመጨረሻም እጀግ እየጠነከረ በመጣው የሕዝብ መስዋእትነት ጭምር  ነው፡፡ ይህ ትግል ህወሓት መራሹ መንግሥት ሀገሪቱን በብዙ መልክ ይገዛበት የነበረውን አጀንዳ በመቃወም የተደረገ ትግል ውጤት ነበር፡፡

ይህ በሆነበት ሁኔታ የህወሓት የፖለቲካ አጀንዳና የሕዝብ ፍላጎት የማይጣጣምበት ደረጀ ላይ ደርሶ እንደነበር ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋለ፡፡ ስለዚህም “ ህወሓትንማካተት “ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ግልጥ ማደረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ለውጡ የህወሓት መሠረታዊ አጀንዳ፣የሆነውን የርሱን ፍጹም የበላይነት የርሱን ከፋፋይና ረጋጭ ፖሊሲዎች….ወዘተ እክ እንትፍ ባለበት ሁኔታ ማካተተ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ማሳየት ተገቢ ነው፡፡በዚህ አንፃር ጀዋር አመልካከቱን በበቂ ግልጥ ሳያደርግ ዶከተር አብይን ወደ መውቀሱ ላይ ብቻ ማትኮሩ ለተለያየ ትርጉም ብዙ በርን ከፍቷል፡፡

የሰሜኑ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ህወሓት የተጀመረውን የለውጥ ሂደት በፍጹም እንዳልተቀበለውና በሰላምም በጉልበትም ሊያስቆመው እንደሚጥር ደግሞ ደጋግሞ በግልጥ ያቀረበው ጉዳይ ነው፡፡ በተለይም ኢህአዴግ ፈርሶ ብልጽግና ሲመሠረት ህወሓትየሚወስደው እርምጃ ሁሉ በቀጥታ ወደ ጦርነት እየተጓዘ እንደነበር በግልጽ ቋንቋ እየተነገር  ነበር፡፡ ራሱ ጀዋር በአንድ ቃለ ምልልስ እንደገለጠው ከጦርነቱ መነሳት በፊት ህወሓ ትመቀሌ ላይ ያካሂድ የነበረው ተከታታይ ወታደራዊ ትርኢት ከቶውንም የሚረሳ አይደለም፡፡

ይህ ደግሞ በግለስብ ድንገት በሚነገር መግለጫ ብቻ ሳይሆን በድርጅቱ በህወሓት አመራርና የጉባዔዎቹ ውሳኔዎች ደረጃም የተደገፈ ድርጅታዊ አቋም እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

ቅድመ ጦርነት የነበረው ሁኔታ ምን ያክል ለጦርነቱ አስተዋጽዖ አደረገ ማን ምን ሠራ የሚለውን ለጊዜው ወድጎን ትተን ራሱ ጦርነቱን ሰንመለከት ሁለት ምዕራፍ ነበረው ማለት ይቻላል፡፡

የመጀመሪያውምዕራፍ ጥይት ተተኩሶ በወታደራዊ ኃይል ህሕይወት ማጥፋት፣ ንብረት ማውደም የተጀመረበት ጊዜ ነው፡፡ ይህም  በሰሜን ዕዝ የሀገራችን ሠራዊት ላይ ቀን ከትግራይ ምድር አንበጣ ሲያባርርና ሰብል ሲሰበስብ የዋለውን ሠራዊት በኖቨምበር 4፣ 2021 በመላ ትግራይ በሚባል ደረጃ ህወሓት ድንገተኛ ጥቃት ከፍቶ (መብረቃዊ ብሎ በሰየመው) ከፍተኛ የግፍ ተግባር በመፈጸም አዲስ አበባን ለመቆጣጣር በዚያኑ ዕለት ወደ አማራ ክልል በዘመተበት ጊዜ የተጀመረ ነበር፡፡

የኢትዮጰያ ሠራዊት ይህን ሁኔታ ለመቀልበስ ያደረገውን መልሶ ማጥቃት (በሰብዓዊ  መብትና  ሌላ ሌላም ወደኋላ  ላይ የደረሰ አሳዛኝ ሁኔታ ሁሉ እንዳለ ሆኖ)  ከዚህ አሳዛኝና አሳፋሪ የክህደትና ከኔ በላይ ተዋጊ ለአሣር ብሎ የተነሳ ቡድን ጋር በአንድ ደረጃ መመደብ የጀዋርን የሞራል ሚዛን  የተዛባ ያደርገዋል፡፡

ሁለተኛው የጦነቱ ምዕራፍ የተጀመረውም ብልጽግና የትግራይ ገበሬ እርሻ እንዲያርስ ዕድል ለመስጠት በሚል ምክንያት ሠራዊቱ ትግራይን ለቆ እንዲወጣ ካደረገ በኋላ ህወሓት በመቶ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ አሰልፎ በአማራና በአፋር ላይ ግልጽ ጦርነት በክፈተበት ጊዜ የተጀመረ ሲሆን በቀጣይም እስክ ጣርማ በር (ስሜን ሽዋ) ድረስ በወታደራዊ ኃይል በመቆጣጠር በመዝረፍ፣ መመገደል ሴቶችን አስገድዶ በመድፈር የገሰገሰበት ወቅት ነው፡፡

ጀዋር ስለጦርነቱ ሲያነሳ እነዚህን እውነታዎች በምንም መልኩ እውቅና አለመስጠቱና ብልጽግናን በመኮነን ላይ ብቻ ማተኮሩ  ግምገማውን ወይም አመለካከቱን ሚዛናዊነት ያነሰው ያደርገዋል፣ እውነታውን ፊት ለፊት ተመልክቶ በሚገባው ስም ጠርቶ መፍትሄ ፍለጋው ላይ ከማተኮር ይልቅ ነገሮችን አድባብሶ ደጋፊ ፍለጋ ላይ ያነጣጠረ  አስመስሎታል፡፡

ጀዋር ሰለወልቃይት

የፖለቲካ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ ከሚናገሩት ይልቅ ያልተናገሩትን ለይቶ በማየት ስለሚያሳስባቸው ጉዳይና አጀንዳዎቻቸው ብዙ መገንዘብ ይቻላል፡፡

ጀዋር ወደ ሁለት ሰዓት በወሰደው የሰሞኑ ሰፊ ቃለምልልሱ፡ የወልቃይትን ጉዳይ አላነሳም፡፡ የማኅበራዊ ፍትኅ ተሟጋቹ ጀዋር የመፍትሄ ሀሳብ ባይሰነዝርም እንኳ፣ የወልቃይት ጉዳይ ዛሬም የችግሩን ህያውነት አሳሳቢነትና የሕዝቡንም ስቃይ እውቅና ሰጥቶ ማለፍ በተገባው ነበር፡ ጀዋር በዚህ አጋጣሚ ይህን አለማድረጉም ትልቅ አጋጣሚ እንዳመለጠው እስባለሁ፡፡ የዚህ ቃለ ምልልሱ አድማጭ አድርጎ የመደበው ማንን ነው? ሊያስተላልፍ የፈለገውስ መለዕክት ለማን ነው ብዬ ደጋግሜ እንዳስብ አድርጎኛል፡፡

ጀዋር ሰለ ብሄራዊ መግባባት

የሀገራችንን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት ብሄራዊ ምክክርና መግባባት ያስፈልጋል የሚለው አጅንዳ ከሞላ ጎደል ተቀባይነት ያገኘ ሆኖ ይታያል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በፕሮፊሰር መስፍን አርዓያ መሪነት የተጀመረው የብሄራዊ ምክክር ሂደትን በተመለከት ጀዋር በመርኅ ደረጃ እንደሚደግፈው ካሳየ በኋላ አሁን የተመሠረተውን ኮሚሽን ገና ከጅምሩ የሞተ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ለዚህም እንደ ዋና ምክንያት አድርጎ ያቀረበው የሂደቱን አሳታፊ አለመሆን ሳይሆን በሀገሪቱ ውስጥ ጦርነት እየተካሄደ ብሄራዊ መግባባት ሊካሄድ አይችልም የሚል አመክከት ነው፡፡

በተለይም በኦሮሚያ ኦነግ ሸኔ፣ በትግራይ ህወሓት ተኩስ አቁም ተደርጎ ወደ ውይይቱ እንዲገቡ ካልተደረገ ይህ ሂደት የትም አይሄድም ገና ከጅምሩም የሞተ ጉዳይ ነው ሲል ተደምጧል፡፡

ከዚህ ውጭ ግን ከብሄራዊ መግባባት አኳያ ሁለት ጉዳዮችን ማንሳት ያስፈልጋል

እኔ እስከምረዳው የተለያዩ ሀገሮች ልምድ እንደሚያሳየውም ብሄራዊ መግባባት ክየልሂቃን ድርድር (elite bargaining ) የተለየ ነው፡፡ የሊሂቃን ድርድር የብሄራዊ መግባባት ሂደት አንድ አካል ሊሆንም ይችላል፡፡ ሆኖም ብሄራዊ መግባባት የተለመዱ ልሂቃንን በማግባባት ከላይ ወደ ታች የሚፈስ ሂደት ሳይሆነ ከውሳኔ አስጣጥ ከትርክት ፈጠራ…. ወዘተ ርቀውና ተገልለው የኖሩ የኅበረተሰብ ክፍሎችን በዋናኛነት በማሳተፍ አዲስ የሕዝብ ተሳትፎና፣ የሕዝብ ድምፅ በሀገር ችግር አፈታት ላይ ቁልፍ ቦታ እንዲኖር የሚያደረግ ሂደት ነው፡፡

በዚህ አኳያ የተለያዩ ሀገራት ሁሉን አቀፍ ልምድ እጅግ የተለያየ እንደመሆኑ፣ አንድን ሂደት ይህን ካልመሰለ ገና ከመጀመሪያው የሞተ ጉዳይ ነው የሚል አካሄድ ለብሄራዊ መግባባት ከጠቀሜታው ጉዳቱ ሰፊ ነው፡፡በኔ በኩል ይህ ሂደት በተቻለ መጠን ሰፋ ያለ የኅበረተሰብ ክፍሎችን የፖለቲካና የሲቪክ ማኅበራትን ሊያከትት ይገባዋል፡፡

ሆኖም እንድ ድርጅት የአንድ ማኅበረስብ “ብቸኛ ወኪል” የሆነ ይመስል፣ እገሌ ካልተገኘ ነገሩ ፈረስ ማለት የዚህን ዓይነት እጅግ ጥንቃቄ የሚሻ ሂደትን ከፍተኛ አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል፡፡ ስለዚሀም፣ በተለይም ተደማጭነት ያላቸው ግለሰቦችም ሆኑ የተደራጁ ኃይሎች ይህን እጅግ ጥንቃቄ የሚሻ ሂደት አውቀውም ሆነ ሳያውቁት እንዳያመክኑት ከሚናገሩት ነገር ጀምሮ ታላቅ ጥንቃቄ  ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ጀዋርም እንደ አንድ ተጽዕኖ ፈጣሪና በተወሰነ ማኅበረስብ ውስጥምተከታይ እንዳለውየፖለቲካ ድርጅት መሪ  ማስጠንቀቂያና ማስፈራሪያ  ዘመም ንግግር ከማደርግ ይልቅ አማራጭ በማፍለቅ የተጀመረው ሂደቱ የተሻለና ወጤታማ እንዲሆን የሚያስችሉ ሀሳቦችን በማፍለቅ ቢያግዝ የተሻለ ውጤት ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሀገራችን አሁን ያለችበትን እጅግ ውስብስብ ችግር፣ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚገኙበትን የመጠፋፋት አዝማሚያና ችግሮቻችንን  ለመፍታት ያለውን ጠባብ ዕድል ግምት ውስጥ አስገብቼስመለከት የብሄራዊ ምክክሩ ሂደት ገና ከጅምሩ የሞተ ነው ብሎ በመነሳት ጉዳዩን ወደ መቃብር ለመሸነት የሚሯሯጥ ክፍል ይህን ሲያደርግ በመትኩ በተጨበጭ ተግባራዊ የሚሆን አማራጩ  ምን እንደሆነ ማሰብ፣ ይህንንም ለሕዝብ ዕይታ ማቅረብ እጅግ አስፈላጊና ሀላፊነት የተሞላው ተግባር ሆኖ ይታየኛል፡፡ በዚህ በኩል ከኦቦ ጀዋርም ሆነ ከሚመሩት ኦፊኮ የቀረበ ተጨበጭና ዝርዝር አማራጭ አለማየቴ ባያረካኝም የተሻለ ነገር ለማየት በጉጉጉት እጠብቃለሁ፡፡

ቃል በተግባር ሲፈተሽ

ጀዋር በተደጋጋሚ ላነሳቸው የተለያዩ ተግዳሮቶች በአብዛኛው በዶክተር አብይ የሚመራውን ገዥውን ብልጽግናን በሀላፊነት ተጠያቂ አድርጎ አቅርቧል፡፡ አዎ ብልጽግና ላለፉት አራት ዓመታት የሀገር መሪነትን ይዞ የቆየ ስለሆነ በሀገሪቱ ውስጥ ለሚታየውጥሩም መጥፎም ጉዳይ በዋናነት የእርሱ ስም አብሮ እንደሚጠራ ግልጽ ነው፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን በአራት ዓመቱ ሂደት ውስጥ አልተፈጸሙም ወቀሳ ያስነሱ ብዙ ችግሮች በብለጽግና እምቢተኛነት ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚውና ብዙ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች በፈጠሯቸው ችግሮች ጭምር የተደናቀፉ መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል፡፡ ለምሳሌም ህወሓት ከአዲስ አባባ ሥልጣኑ ሲወገድ ሁሉን አቀፍ የሸግግር መንግሥት እንዳይመሠረት ለሆነበት ክስተት የተቃዋሚው ወገን አስተዋጽዖ ነበረው፡፡

የሀገራችንን ችግሮች እጅግ ወደተወሳስበ ደረጃ ያሳደገውና የብዙ ሰው ሕይወት እንዲጠፋ፣ ብዙ ሺዎች እንዲፈናቀሉ፣ በመቶ ሚሊዮኖች የሚገመት የድሆች ንብረት እንዲወድም ታላቅ አፍራሽ አበርክቶ ያደረገው በከፊልም ቢሆን  በዚሁ በተቃዋሚው ጎራ የተሰለፉ አንዳንድ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ጭምር እንደሆኑ  በሰፊው መረጃ ማቅረብ ይቻላል፡፡

በዚህ ሂደት ጀዋር ከነበረው ተጸዕኖ ፈጣሪነት አኳያ ለተሠሩ ስህተቶች ሀላፊነት ለመቀበል ምሳሌ ሆኖ ቢቀርብ እጅግ ታላቅ እርምጃ በሆነ ነበር፡፡ አሁንም  በቀጣይ አጋጣሚዎች ይህንን እንደሚያደርግ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የውስብስብ ችግሮቻችን መፍትሄ በተለያያ ደረጃ የተሠሩ አሁንም እየተደረጉ የሚገኙ ጉዳዮች መሆናቸውን መቀበል ለመፍትሄ ፍለጋው አንዱና ትልቁ  እርምጃ ይሆናል፡ ብዬ አስባለሁ፡፡

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ ውሱን ቢሆንም ጀዋር ያሳያቸው መልካም ጅማሮች እንዲቀጥሉ ሊበረታቱ የሚገባ ሆኖ ይታየኛል፡፡ የተሰበረውን ማኅበራዊ ግንኙነት ለመጠገን ከመጠን በላይ የተካረረውን የፖለቲከኞች አለመተማመን ለማርገብ እንዲሁም አጠቃላዩን ጭንቅ ለማሰወገድ  በየደረጃው በየቡድንም ሆነ እንደግለስብ ልንወስዳቸው የሚገባ እጅግ ብዙ እርምጃዎች አሉ፡፡

በሀገራችን ሰላም ወርዶ ወደ የተሻለ ሁኔታ በመጓዝ ተጠቃሚዎቹ ሁላችንም ነን በተቃራኒው ለሚሆነው ደግሞ ተጎጂዎቹ ሁላችንም ነን፡፡ ጀዋር በዚህ አዃያ ሊጫወተው የሚችለው ሰፊ  ሚና አለ ብየ አምናለሁ፡፡ ይህን ማድረግ የታላቅነት ምልክት ሲሆን ይህን በጎ ሚና በአግባቡና በወቅቱ ይጠቀምበት ይሆን የሚለውን በጋራ የምናየው ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *