መኢአድ-ኢህአፓ- እናት፡ፓርቲ
Press Release

መንግሥት በአማራ ህዝብ ላይ የጀመረውን ጥቃት በአስቸኳይ ያቁም!

በወቅታዊ ጉዳይ ከእናት ፓርቲ፣ ኢሕአፓ እና መኢአድ የተሰጠ የጋራ መግለጫ

ባለፉት 30 አመታት የተከተልነው “የጎሳ ፌደራሊዝም” የኢትዮጵያ ህዝብ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች በሰብዓዊነቱ ሁለንተናዊ ተሳትፎ እንዳያደርግ አግዶታል፡፡ የሠላምና የጸጥታ ዕጦት፣ መረን የለቀቀ ሙስና፣ አድሏዊ አሠራር፣ ዘውገኛነትና ጎጠኝነት ሥር ሠዶ የገነገነበት ዘመን ላይ እንድንደርስም አስገድዶናል። በዚህ ላይ ስለሀገሩ ኅላዌ፣ አንድነትና ሉዓላዊነት የሚገደው ዜጋ ደግሞ ተብከንካኝና ባይተዋር እንዲሆን ተፈርዶበታል። ኢትዮጵያውያን ዛሬ የምንገኝበትን የብሶት ደረጃ “አላውቅም” የሚል የገዥው ፓርቲም ሆነ የመንግሥት ባለሥልጣን ካለ ያለበትን የኃላፊነት ሥፍራ የዘነጋና እውነታውን የካደ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በከፍተኛ ችግር፣ ምስቅልቅልና ብሶት ዉስጥ ነው።

ማንኛውም ዜጋ በሀገሩ ዉስጥ የህይወት ዋስትና ሊኖረው ሲገባ፣ ዛሬ ዘውግን ወይንም ሃይማኖትን፣ ወይንም ደግም ከገዥዎች ፍላጎት የተለየ ሃሳብ መግለጽን መሠረት ባደረጉ ፍረጃዎች የተነሳ በዜጎች ላይ ከባድ ጉዳት እየደረሰ ይገኛል። በሠላም ወጥቶ መግባትም ፈታኝ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ በተለይም ማንነትን መሰረት ባደረገ የጥላቻ እሣቤ የአማራ ህዝብ ለመፈናቀል፣ ስደትና እንግልት ተዳርጓል፡፡ በኦሮሚያና ቤኒሻንጉል-ጉምዝ ክልሎች ዜጎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፤ ተደብድበዋል፣ ታስረዋል፣ በጅምላ ተጨፍጭፈዋል፡፡

ሕወሓት መራሹ ኢህአዴግ በ1983 ዓ.ም. የፖለቲካ ሥልጣን ከጨበጠበት ወቅት ጀምሮ አማሮች በጠላትነት ተፈርጀው በተደጋጋሚ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ደርሶባቸዋል፡፡ የብልጽግና መንግስትም ይህንኑ ፈለግ ተከትሎ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡ የዚህ ጦስ የዜጎች ህይወት በሰብአዊነት መንጠፍ ውስጥ እንዲወድቅ አድርጓል። ከዚህ አኳያ የሁሉም ዜጎች ህይወት እኩል ዋጋ፣ እኩል ክብርና ዋስትና ሊያገኝ ይገባል ብለን እናምናለን። የመንግሥት ግንባር ቀደም ሃላፊነትና ሥራ የዜጎችን ህይወት መጠበቅ ሆኖ ሳለ ባለፉት አምስት አመታት የዜጎች ህይወት በእየለቱ ሲቀጠፍ መንግስት ያሳየው ዳተኝነት አሳፋሪ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጡ ሰሞን የነበረው የለውጥ ፍላጎትና ጠንካራ ትግል የተወሰነ ለውጥ መሣይ ብልጭታ በመፍጠሩ፣ ዜጎች ሀሳባቸውን በነፃነት ለመግለጥ የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። “ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ይቻላል” የሚል ተስፋም አጭሮ ነበር። ይሁን እንጂ “ላም አለኝ በሰማይ …” በሆነ መልኩ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ተክዶ በተለመደው መልኩ በጎሳ ስሁት ትርክት ውስጥ የምትታሽ ሀገርና ሥርዓት ውስጥ እንድንኖር ተገደናል፡፡ ጋዜጠኞች፣ ምሁራንና ማኅበራዊ አንቂዎች፣ በተናገሩትና በጻፉት ህግን ጥሰው ከሆነ በፍርድ ቤት እንደሚጠየቁ እናውቃለን፡፡ ከዚህ ውጭ በሆነ መልኩ ዜጎችን በግፍ ማሰር፣ መደብደብ፣ ማንገላታት እና አፍኖ-መሰወርን ግን ምን አመጣው?

በቅርቡ ዳግም ጅምላ እስሩ መፈናቀሉ ግድያውና አፈናው የበረታው በአማራው ህዝብ ላይ መሆኑ ምሬትና ብሥጭት እንዲጨምር አድርጓል። በሀገራችን ዋና ከተማ አዲስ አበባ ሣይቀር ማንነትን ማዕከል ባደረገ ሁኔታ ማፈናቀልና ማሣደድ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ የብልጽግና መራሹ መንግስት የነዋሪዎችን መኖሪያ ቤቶች በላያቸው ላይ ማፍረስና ማባረር ከጀመረ ሰነባብቷል። በተለይም የዜጎችን በሀገራቸው ዉስጥ በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት በሚደፈጥጥ መልኩ አማሮች ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ እየተደረጉ ለከፍተኛ ችግርና እንግልት መዳረጋቸውም ሀገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው። የአማራው ህዝብ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር በመሆን በደሙና በአጥንቱ በሠራት አገር ባይተዋርና አገር አልባ ተሳዳጅ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን በግልጽ ተገንዝበናል፡፡ ከዚህ በላይ የተገለጡት እውነታዎች፣ በአማራው ህዝብ ላይ ከፍተኛ ብሶቶችን እንደፈጠሩ፣ የዚህ ችግር ባለቤት በመሆን የወረራ ስልትና ፈጠራውን ያቀነባበሩ ኃይሎች ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ ከዚህ ቀደም ሦስቱም ፓርቲዎች (እናት ፓርቲ፣ ኢሕአፓ እና መኢአድ) ቀደም ሲል የተዘረዘሩትን ጉዳዮች እየገለጡ ችግሮች እንዳይባባሱ መንግስትን ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።

በሕወሓት እና በፌደራል መንግስት መካከል የተከናወነው ከባድ የእርስበርስ ጦርነት አገርንና ህዝብን ከፍተኛ ጉዳት ላይ ጥሏል። የትግራይን፣ የአማራን፣ የአፋርን ህዝብንም የበለጠ ጎድቶታል። ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚገመቱ ወገኖቻችን የጦርነቱ ሰለባ ሆነዋል፡፡ በመቶ ሺ የሚቆጠሩት የአካል ጉዳተኛ ተደርገዋል፡፡ ዜጎች በገዛ ሐገራቸው ተፈናቃይና ስደተኛ ሆነዋል። የመሠረተ-ልማት አውታሮችና ተቋማት ወድመዋል። ህዝቡ ገና ከጦርነቱ ቁስል አላገገመም። ታዲያ ገዥው መንግስት ይህንን መራር እውነት ዘንግቶ እንዴት በአማራ ህዝብ ላይ ጥቃት ሊከፍት ቻለ!? ይህ አይነቱ አካሄድ አገር አፍራሽ በመሆኑ ከወዲሁ ጊዜው ሳይሄድ መንግስት እጁን ሊሰበስብ ይገባል፡፡

ነገሮች እንዲህ በተወሳሰቡ ሁኔታዎች ውስጥ እያሉ የፌዴራል መንግሥት ችግሩን በሚያባብስ መልኩ ወደ አማራ ክልል ሠራዊት አዝምቶ “ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶችን መቆጣጠርና ትጥቅ ማስፈታት” በሚል ሽፋን በየቦታው በከባድ መሣሪያ ጭምር በዜጎች ላይ ተኩስ ከፍቷል። የተረጋጋና አስተማማኝ ሁኔታዎች ሳይፈጠሩ፣ ተቻኩሎ፣ በሃይል ትጥቅ ለማስፈታት መሞከር ሌላ ጦርነት ከመቀስቀስ የተለየ ውጤት የለውም። ሠላም የተነፈጉና እየተሳደዱ ያሉ ዜጎችን፣ በቅድሚያ ትጥቅ ማስወረድ ለምን አስፈለገ? ኢትዮጵያ ከተዘፈቀችበት የጎሰኝነት አረንቋ ሳትወጣ፣ በዘውግ በተደራጁ ሃይሎች በሚመራ መንግሥት የሚወሰዱ ማናቸውም እርምጃዎች ወደ ሌላ ችግር የሚያስገቡ ናቸውና ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ስለሆነም መንግስት በአማራ ክልል ዉስጥ የጀመረውን ህገ-ወጥ ጥቃት በአስቸኳይ አቁሞ ውይይትን መሰረት ባደረጉ አካሄዶች ብቻ ችግሮችን እንዲፈታ አጥብቀን እናሳስባለን።

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ

ሚያዝያ ፳፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *