መኢአድ-ኢህአፓ- እናት፡ፓርቲ
Press Release

አገር በሕግና ሥርዓት እንጂ በጉልበት አትመራም! – እናት ፓርቲ፣ ኢሕአፓ እና መኢአድ በጋራ

ከእናት ፓርቲ፣ ከኢሕአፓ እና ከመኢአድ በጋራ የተሰጠ መግለጫ

ብልጽግና ፓርቲ በምርጫ አሸንፍያለሁ ብሎ ስልጣን ቢረከብም እንደ መንግሥት መምራት ተስኖት ሀገራችን ኢትዮጵያን ማስተዋል ባልታከለበት እና ኃላፊነት በጎደላቸው የፓርቲ ውሳኔዎች ለመከራ በመዳረግ ላይ ይገኛል፡፡ መከራው ያልነካው ኢትዮጵያዊ ማን አለ!? እድሜና ጾታን ያለየ የጅምላ ጭፍጨፋዎች፣ ማፈናቀል፣ ስደት፣ ለቅሶና ዋይታ የምስኪኑ ህዝባችን የዕለት ተዕለት ዜና ከሆነ ሰነባብቷል፡፡  ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አቢይ አህመድ ስልጣን በተረከቡበት ወቅት “መግደል መሸነፍ ነው …” ቢሉንም በተግባር እየተፈፀመና እየሆነ ያለው ጉዳይ ግን ከንግግራቸው በተቃራኒ ሆኖ “መንግሥት” ዜጎችን ከመጠበቅ ይልቅ አፈናቃይ፣ አሳዳጅና ገዳይ  ሆኗል።በዚህም የሚመሩትን መንግሥት የተሸናፊነት ጉዞ እያረጋገጡልን ይገኛሉ፡፡ በተለይ አይነኬ ሃይማኖታዊ እሴቶችን በመጣስ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እና በሙስሊም አብያተ እምነቶች ላይ እየፈፀመ የሚገኘው አፍራሽ ተግባር ለኢትዮጵያ መጭው ጊዜ ምን ያህል አስቸጋሪና ውስብስብ እንደሆነ ያሳያል፡፡

ግንቦት ፲፰ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም “ከሸገር ከተማ ግንባታ” ጋር በተያያዘ የፈረሱ መስጅዶችን አስመልክቶ ድምጻቸውን በሰላማዊ መንገድ ባሰሙ የእስልምና እምነት ተከታይ ወገኖቻችን ላይ ከተፈፀመው ግድያና ድብዳባ ከደረሰበት ሀዘን ህዝባችን ሳይጽናና፤ ግንቦት ፳፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በታላቁ አንዋር መስጂድ ለጁመዓ ሰላት በተሰባሰቡ ሙስሊሞች ላይ የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች መስጂድ ውስጥ ድረስ ዘልቀው በመግባት የፈፀሙት ግድያና ድብደባ ህዝባችንን መሪር ሐዘን ውስጥ እንዲወድቅ አድርጎታል፡፡ በህዝበ ሙስሊሙ ላይ የተፈፀመው ድብደባ፣ አፈና እና እንግልት ዓለምን አሳዝኗል፡፡ በጎጃም ደብረ ኤሊያስ ገዳም አባቶች ላይ መንግሥት የወሰደው በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት እንዲሁም በአርሲ ዴራ አማኑኤል አጥቢያ ቤተ-ክርስቲያን ቀሳውስትና ምዕመናን ላይ በታጣቂ ኃይሎች የተፈፀመው ግድያ ፈሪሀ ፈጣሪ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ ስልጣንና ወንበራቸውን ጣኦት ባደረጉ  መሪዎች ላይ እንደወደቀ ያመለክታል፡፡ አንድ “መንግሥት” ነኝ የሚል አካል እንዴት የሚያስተዳድረውን ህዝብ ሃይማኖት ማክበርና መጠበቅ ይሳነዋል!? በተለይ በሁለቱ ታላላቅ ሃይማኖቶች ላይ መንግሥት የከፈተው ዘመቻ አደገኛ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

መንግሥት የአማራ አርሶ አደርን ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በመንፈግ ህዝባችን ወደ አሰቃቂ ረሃብ እንዲያመራ ፈርዶበታል፡፡ ባለንበት በዚህ የሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን አርሶ አደሩን ተብከንካኝ ሆኖ ከማየት በላይ የሚያሳዝን ነገር የለም፡፡ ባለፉት ሶስት አስርት አመታት ከማዳበሪያ ውጭ እንዳያርስ በመዋቅራዊ አሰራር የተፈረደበት አርሶ አደር መሬቱን የባህር ማዶ ማዳበሪያ ጥገኛ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ጉዳዩ በዚህ ደረጃ እየታወቀ አርሶ አደሩን ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ መከልከል አደገኛ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን የከተሜው ህልውነት የሚረጋገጠው በአርሶ አደሩ ስኬት በመሆኑ መንግሥት አፋጣኝ መፍትሔ ሊፈልግ  ይገባል ብለን እናምናለን፡፡ በስሑታዊ የጎሳ ትርክት ምክንያት መከራ እየተቀበለ የሚገኘውን የአማራ ህዝብ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በመከልከል ሁለንተናዊ የዘር ፍጅት እንዲፈፀምበት መስራት ኃላፊነት የጎደለው የሚለው ቃል የማይገልጸው ተግባር ነው፡፡ እናት ፓርቲ፣ ኢሕአፓ እና መኢአድ  በተደጋጋሚ መንግሥት ከሚሰራቸው ያፈጠጡ ጥፋቶች እንዲታረም ማሳሰባችን ይታወሳል፡፡ አሁንም አስተዋይ ልቡና እና አዕምሮ ካለ ሀገር በሕግና ሥርዓት እንጂ በጉልበት እንደማትመራ በድጋሜ ልናስታውስ እንወዳለን፡፡ ስለሆነም፡-

፩. በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ኢትዮጵያዊ ጨዋነትና ሰብዓዊነት በጎደለው መልኩ በደብረ ኤሊያስ ቅድስት ሥላሴ ገዳም እንዲሁም በታላቁ አንዋር መስጂድ ለጁመዓ ሰላት በተሰበሰቡ ምዕመናን ላይ የተወሰደው አሳፋሪ እርምጃ በገለልተኛ ወገን  በአስቸካይ እንዲጣራ እስከዚያው ጉዳዩን አስመልክቶ በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ እናሳስባለን፡፡  ጉዳት ለደረሰባቸው አካላት አስፈላጊውን መረጃ አጠናቅሮ ካሳ እንዲከፍል፤ በሚደርገው የምርመራ ውጤት ላይ ተንተርሶ  ድርጊቱን የፈፀሙ አካላት በህግ እንዲጠየቁ እንዲያደርግ እንጠይቃለን፡፡

፪. መንግሥት በአፋጣኝ ለአማራ አርሶ አደሮች  ማዳበሪያና ምርጥ ዘር እንዲያቀርብ እየጠየቅን፤ በአካባቢው እየጎሰመ የሚገኘውን የጦርነት ነጋሪት ከመንፋትም እንዲታቀብ እናሳስባለን፡፡

፫. መንግሥት ሃይማኖታዊ ተቋማት አይነኬ የኢትዮጵያ ህዝብ እሴቶች መሆናቸውን ተገንዝቦ አስፈላጊውን ክብር በመስጠት በልማት ሰበብና በጦር ዘመቻ ያፈረሳቸውን መስጂዶችና ቤተ-ክርስቲያናት በፍጥነት እንዲገነባ እንዲሁም አስፈላጊውንም ካሳ እንዲከፍል እናሳስባለን፡፡

 

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ይጠብቅ!

ግንቦት ፳፮ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
መኢአድ፣ ኢሕአፓ እና እናት ፓርቲ

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *