ዕለቱ ሰኞ ነሐሴ 01/ 2015 ዓ.ም ነው።
የአማራ ክልል መዲና ባሕር ዳር በፋኖ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል በተፈጠረ ግጭት አዳሯን በከባድ መሣሪያ ተኩስ ስትናወጥ ነው ያደረችው።
ነዋሪዎች እንዳሉት ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ከተማዋ የሚተኮሱት የከባድ መሣሪያ ድምጽ ሌሊቱን የሚነጋ አላስመሰሉትም ነበር።
እየነጋ ሲሄድ የተኩስ ሩምታው በትንሹም ቢሆን ጋብ አለ።
ዕለቱ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ ልዩ ቦታ የሚሰጠው የፍልሰታ ጾም የሚጀምርበት በመሆኑ አንዳንዶች የተኩሱን ጋብ ማለት ተጠቅመው ጸሎት ለማድረስ በአቅራቢያቸው ወዳለ ቤተክርስቲያን ተጣደፉ።
በከተማው የትራንስፖርትም ሆነ ሌላ እንቅስቃሴ ባይኖርም ወደ ቤተክርስቲያን የሚሄዱ ሰዎች አልፎ አልፎ ይታዩ ነበር።
በከተማዋ ቀበሌ 14 ነዋሪ የሆኑት አቶ አየነው ደፈርሽም በአቅራቢያቸው ወደሚገኘው አቡነ ሐራ ቤተክርስቲያን ለመሄድ ከሁለት ወንድ ልጆቻቸው ጋር ከቤት የወጡት ማክሰኞ ነሐሴ 02/ 2015 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት አካባቢ ነበር።
“እኔም ቤተክርስቲያን ልሄድ ተነስቼ ነበር ‘እናንተ ቤት ቆዩ’ ብሎ ታላላቆቹን ልጆች ይዞ ወጣ” ይላሉ የአቶ አየነው ባለቤት አበባ ጎሹ።
ሲዘገዩብኝ ትልቁ ልጄ ጋር ስልክ ደወልኩ የሚሉት ወ/ሮ አበባ፤ ስልኩን እንግዳ የሆነ ግለሰብ አንስቶ “እዚህ ወድቀውልሻል። አንሺ!” አለኝ” ይላሉ።
ወ/ሮ አበባ እንደሚሉት ባለቤታቸው አቶ አየነው እና ሁለት ልጆቻቸው የተገደሉት ከመኖሪያ ቤታቸው ብዙም ሳይርቅ ነው።
“ተሳልመን እንምጣ ብለው ተያይዘው በዚያው ቀሩብኝ። የመጀመሪያው ልጄ ባለትዳር እና የአንድ ልጅ አባት ነው። ሁለተኛው ልጄም ትዳር ከመሠረተ ገና አንድ ዓመቱ ነው። አንድ ግቢ ውስጥ ነበር ሁላችንም የምኖረው” ይላሉ በማያቋርጥ ለቅሷቸው ታጅበው።
አቶ ሙሉ ሃሳቡ የሟች አቶ አየነው ታናሽ ወንድም ናቸው። በእናት ነው የሚገናኙት። እርሳቸውም እዚያው አካባቢ ነው የሚኖሩት።
ሌሊቱን ሲሰማ በነበረው ተኩስ ምክንያት ወንድማቸው እና ቤተሰባቸው እንዴት እንዳደሩ ለማወቅ ደጋግመው ሲደዋወሉ እንደነበር ይናገራሉ። መጨረሻ ላይ ስደውልላቸው ቤት ውስጥ ነበሩ ይላሉ።
ትንሽ ቆይቶ ጋብ ያለው ተኩስ እንደገና በረታ። ወደ ወንድማቸው ስልክ ደወሉ። ስልኩን ያነሳው ወታደር ነበር ይላሉ።
“እዚህ ወድቆልሃል አንሳ” እንዳላቸው አቶ ሙሉ ይናገራሉ።
“እኔም ብወጣ ይገድሉኛል ብዬ እያለቀስኩ ቆየሁ” የሚሉት አቶ ሙሉ፣ በኋላ ላይ ከእህታቸው ልጅ ጋር ተገደሉ ወደተባለበት ቦታ ሄደው አስክሬናቸውን እንዳገኙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ወንድሜ ከእነ ልጆቹ እና ከእነ ጓደኞቹ ለምን እንደተገደለ አላውቅም። በርበሬ ነጋዴ ነበር። መሳሪያ እንኳን ነክቶ አያውቅም። የሥራ ሰው ነበር። ታታሪ ነበር” ይላሉ።
ወንድማቸውን እንዲሁም ካሳሁን እና አብርሃም የተባሉ የወንድማቸውን ልጆች ጨምሮ የአምስት ሰዎችን አስክሬን በአንድ ቦታ ላይ እንዳገኙ፤ ሌላ አብሯቸው የነበረ ጓደኛቸው ደግሞ አንገቱ ላይ ተመትቶ ሕይወቱ መትረፉን አቶ ሙሉ ተናግረዋል።
“ሁሉም ጭንቅላታቸው አካባቢ ነው የተመቱት። ወንድሜ ከኋላ ነው የተመታው፣ የ30 ዓመቱ የወንድሜ ልጅ ከኋላ በአሰቃቂ ሁኔታ በጥይት ተመትቶ ነው የሞተው። የ27 ዓመቱ የወንድሜ ልጅ ደግሞ ከኋላ በጎን በኩል ጭንቅላቱን ነው የተመታው” ብለዋል።
የሁሉም የቀብር ሥነ ሥርዓት እዚያው አቡነ ሐራ ቤተክርስቲያን የዚያኑ ዕለት መፈፀሙን የሚናገሩት አቶ ሙሉ፣ ከአቡነ ሐራ አካባቢ ብቻ የ32 ሰላማዊ ሰዎች አስክሬን መገኘቱን ገልጸዋል።
“ስለጨነቀን የዚያኑ ቀን እዚያ ጣልናቸው። ሰው ተቀብሮበት የማያውቅ ቦታ ነው የጣልናቸው” ሲሉ በነበረው ሁኔታ ምክንያት በአግባቡ መቅበር እንዳልቻሉ ተናግረዋል።
አቶ ሙሉ ጨምረውም ልጇን ለመፈለግ የወጣች ነፍሰጡር ሴት፣ እንዲሁም አባይ ማዶ በሚባል አካባቢ ለወሊድ በቃሬዛ በሰዎች ሸክም ወደ ሆስፒታል እየሄደች የነበረች እናት እና ቃሬዛውን የተሸከሙትም መገደላቸውን ለቅሶ ሊደርሱ ከመጡ ሰዎች መስማታቸውን ገልጸዋል።
በአካባቢው በከባድ መሳሪያ ተመትተው የፈራረሱ ቤቶች፣ መስታወታቸው የረገፉ እና የተበሳሱ ቤቶች በርካታ መሆናቸውን ገልጸው፣ የእነርሱም ቤት ጉዳት እንደደረሰበት ተናግረዋል።
በርካታ ነዋሪዎቿን ያጣችው ባሕር ዳር ከተማም ሐዘን ወርሷታል።
ባለፉት ጥቂት ቀናት በከተማዋ ውስጥ የተፈጠረው ግጭት የቆመ ሲሆን፣ የተኩስ ድምጽም አይሰማም። በከተማዋ የመከላከያ ሠራዊትም ተሰማርቷል። ሆኖም ሙሉ ለሙሉ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴዋ አለመመለሷን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በአማራ ክልል መዲና ባሕር ዳር በፋኖ ታጣቂዎች እና በመከላከያ ሠራዊት መካከል ከባድ ግጭት የተከሰተው ካለፈው ሳምንት አርብ ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም ጀምሮ ነበር።
ይህ ግጭት ተባብሶ በተለይ በከተማዋ ውስጥ ሰኞ ለማክሰኞ ሌሊት ከተማዋ በከባድ መሳሪያ ስትናወጥ እንደነበር ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የከባድ መሣሪያ ተኩሱ በከተማዋ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የነበረ ቢሆንም፣ በተለይ በቀበሌ 14 በተለምዶ ሙለር ሪል ስቴት ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ፣ በቀበሌ 13 እና በቀበሌ 16 ግጭቱ የተባባሰ ነበር።
በዚህም ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች እና የሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በባሕር ዳር ፈለገ ሕይወት ሪፈራል ሆስፒታል ዶክተሮች፣ የ5 ወር ሕጻን እና አረጋውያንን ጨምሮ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች በጥይት ተመትተው ወደ ሆስፒታሉ መግባታቸውን፣ አንዳንዶቹም ለሕክምና ሳይደርሱ ሕይወታቸው ማለፉን እና አስክሬኖች ሆስፒታሉ መግባታቸውን ገልጸዋል።
ግጭቱ በተከሰተባቸው በታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ እና የኢንደስትሪ ከተማዋ ደብረ ብርሃንም በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ተሰምቷል።
በጎንደር እና በዙሪያዋ ለቀናት በነበረው ግጭት አብዛኞቹ ሰላማዊ የሆኑ ወደ 20 የሚደርሱ ሰዎች እንደሞቱ እና ከ200 በላይ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ጎንደር ሆስፒታል መምጣታቸውን የሆስፒታሉ የሕክምና ባለሙያዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ወደ ጎንደር ሆስፒታል በጥይት ተመትተው ከመጡ ሰዎች መካከል የ16 ዓመት ታዳጊ እንደሚገኝበት እና ተጎድተው ከመጡት መካከል በእድሜ ትልቅ የሆኑት ደግሞ የ50 ዓመት ሴት መሆናቸውን አንድ ዶክተር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ግጭቱ በተለያዩ አነስተኛ የክልሉ ከተሞችና የገጠር መንደሮችም ስለተከሰተ የተገደሉ ሰላማዊ ሰዎች ቁጥር በርካታ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ አርብ አመሻሽ ነሐሴ 5/2015 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫም በአማራ ክልል በተከሰተው ግጭት የንጹሃን ሕይወት መጥፋቱን፣ ንብረት መውደሙን እና ዘረፋ መፈጸሙን ገልጿል።
የፌደራል መንግሥቱ የክልል ልዩ ኃይሎች ህልውና አብቅቶ ወደ ተለያዩ የፀጥታ እና የመከላከያ መዋቅሮች እንዲካተቱ መወሰኑን ተከትሎ፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን መፍረስን በመቃውም የተቀሰቀሰው ተቃውሞ እና ግጭት ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ክልሉን ቀውስ ውስጥ ከትቶታል።
በፀጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ሲካሄድ የቆየው ግጭት እና የተኩስ ልውውጥ ከክልሉ አቅም በላይ ሆኖ የፌደራል መንግሥቱን ድጋፍ በመጠየቁ፣ ባለፈው ሳምንት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል።
ረቡዕ ዕለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ በሰጠው መግለጫ መንግሥት በወሰደው እርምጃ ስድስት የአማራ ክልል ከተሞችን ከታጣቂዎች ነጻ የማድረጉ ተግባር እየተጠናቀቀ መሆኑ የገለጸ ሲሆን፣ በከተሞቹ ላይ ሠዓት እላፊ ገደብ መጣሉን አስታውቋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሰላማዊ ሰዎችን ግድያ እና የጅምላ እስርን ጨምሮ የሚፈፀመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ሊያባብስ ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄም ( አብን) ግጭቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አተገባበር በከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲመራ እና በአጭር ጊዜ እንዲያበቃ ጠይቋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ቡድንም ከዚህ ቀደም ተፈጻሚ ሆነው በነበሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ወቅት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይፈጸሙ እንደነበሩ አስታውሶ፣ መንግሥት በአማራ ክልል የሚወስደው እርምጃ ተመጣጣኝ እንዲሆን አሳስቧል።
ቡድኑ በዚህ ግጭት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ አካላት በሙሉ የሰብዓዊ መብቶችን እንዲያከብሩ እና ግጭት አቁመው ልዩነቶቻቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እንዲሰሩም ጠይቋል።
Source: BBC Amharic