News

ካርቱም በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ የከባድ መሣሪያ ጥቃት ተፈጸመበት

ካርቱም

የፎቶው ባለመብት,GETTY IMAGES

የምስሉ መግለጫ,ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ በካርቱም ውስጥ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ቆይተዋል (ፎቶ ከፋይል)

ሱዳን ካርቱም ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ በተፈጸመ የከባድ መሣሪያ ጥቃት ጉዳት መድረሱን የቢቢሲ ዲፕሎማቲክ ምንጭ ተናገሩ።

ለወራት በጦርነት ውስጥ በቆየችው ሱዳን ዋና ከተማ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ የከባድ መሣሪያ ጥቃቱ የደረሰው ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 22/2016 ዓ.ም. ጠዋት ላይ ነው።

የከባድ መሣሪያ ጥቃቱ በኤምባሲው ሕንጻ እና ንብረት ላይ ውድመት ያደረሰ ሲሆን፣ በሰው ላይ ግን ምንም ዓይነት ጉዳት አለመድረሱን ዲፕሎማቱ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ይበልጣል አእምሮ የከባድ መሳሪያ ጥቃት በኤምባሲው ላይ መፈጸሙን ለቢቢሲ አረጋግጠው፣ በሕንጻው ላይ መለስተኛ ጉዳት እንደደረሰ እና ዝርዝሩን ለማጣራት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በካርቱም አል-አማራት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ባለፉት ወራት በተለያዩ ኃይሎች ተደጋጋሚ ጥቃት እና ዘረፋ እንዳጋጠመው ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ዲፕሎማት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአገሪቱ እየተካሄደ ባለው ጦርነት አንደኛው ተፋላሚ ወገን የሆነው በጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል በኤክስ (ትዊተር) ገጹ ላይ ዛሬ ጠዋት በኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ ጥቃት መድረሱን ገልጿል።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ለጥቃቱ ተቀናቃኙን በጄኔራል አብደል ፋታህ አልቡርሐን የሚመራውን የሱዳን ጦር ሠራዊትን ተጠያቂ ያደረገ ሲሆን፣ በኤምባሲው ላይ በተፈጸመው ጥቃት “በሕንጻው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል” ብሏል።

በኤምባሲው ላይ ጥቃቱ ለምን እንደተፈጸመ እስካሁን የታወቀ ነገር የሌለ ሲሆን፣ ስለክስተቱ በኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ በጄኔራል አልቡርሐን ኃይሎች በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም።

በዛሬው ዕለት ጠዋት ላይ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ በተጨማሪ በዩናይትድ አረብ ኤምሬት፣ በሩሲያ እና በደቡብ አፍሪካ ኤምባሲዎችም ላይ ጥቃት መፈጸሙን ዲፕሎማቱ ተናግረዋል።

በሱዳን የጦርነቱን መቀስቀስ ተከትሎ የኢትዮጵያን ጨምሮ የበርካታ አገራት ኤምባሲዎች ካርቱምን ለቀው የወጡ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ኤምባሲም መቀመጫውን ገዳሪፍ ወደሚገኘው ቆንስላ በማዘዋወር የዲፕሎማቲክ ሥራውን እያከናወነ ይገኛል።

ካርቱም የሚገኘው ኤምባሲ ውስጥ የተወሰኑ የጥበቃ እና ሌሎች ሠራተኞች የሚገኙ ሲሆን፣ በተፈጸሙ ጥቃቶች እና ዝርፊያዎች ለተደጋጋሚ ጉዳት እና ችግር በመጋለጣቸው ሁሉንም ከከተማዋ ለማስጣት የኢትዮጵያ መንግሥት ጥረት እያደረገ መሆኑን ዲፕሎማቱ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ከሳምንታት በፊት በኤምባሲው ላይ በተፈጸመ ጥቃት አንድ ሠራተኛ ላይ የመቁሰል ጉዳት የደረሰበት ሲሆን፣ ከቀናት በፊት በኤምባሲው ላይ ከተፈጸመው ዘረፋ ጋር በተያያዘ ሠራተኞቹ ላይ እንግልት እንደተፈጸመባቸው ዲፕሎማቱ ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ በተቀሰቀሰው ጦርነት ተፋላሚ ኃይሎቹ ዋና ከተማዋን ሱዳንን ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥራቸው ሥር ለማስገባት ከባድ ፍልሚያ ሲያካሂዱ ቆይተዋል።

ኃይሎቹ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የከተማዋ ክፍሎችን ተቆጣጥረው ይገኛሉ።

በሁለቱ ጄኔራሎች በሚመሩት ኃይሎች መካከል ከሚደረገው ፍልሚያ በተጨማሪ በካርቱም ውስጥ ሥርዓት አልበኝነት እና ዘረፋ ከተቋማት ባሻገር በነዋሪዎች ቤት ላይ እንደሚፈጸም ዲፕሎማቱ ተናግረዋል።

ስድስት ወራትን ባስቆጠረው የሱዳን ጦርነት ምክንያት የተለያዩ አገራት ኤምባሲዎቻቸውን ዘግተው ከካርቱም የወጡ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ሠራተኞቻቸውን ከካርቱም ማስወጣታቸው ይታወቃል።

Source: BBC Amharic

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *