News

በኢትዮጵያ ያለው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ በእጅጉ እንዳሳሰበው የመንግሥታቱ ድርጅት ገለጸ

በደብዛዘው የሚታዩ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት,AFP

በኢትዮጵያ በተጨባጭ እየተባባሱ የሚሄዱ የደኅንነት ስጋቶች እና የመብት ጥሰቶች መቀጠላቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች የባለሙያዎች ቡድን ባወጣው አዲስ ሪፖርት አመለከተ።

በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያለውን ሁኔታ የመረመረው በተባበሩት መንግሥታት ድርጀት የሚደገፈው የመብቶች ኮሚሽን አዲስ ባወጣው ሪፖርት፤ በተለይ በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በአፋር ክልሎች ያለው ሁኔታ እንዳሰሰበው አመልክቷል።

ጨምሮም በኢትዮጵያ አሁን ያለው ሁኔታ በአሳሳቢነቱ ሊቀጥል የሚችል “በከፍተኛ ደረጃ አስጊ” የሚባል መሆኑን የሰብአዊ መብቶች መርማሪ የባለሙያች ቡድን ማክሰኞ መስከረም 22/2016 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት ገልጿል።

በአገሪተው ውስጥ “በሰብአዊ መብቶች ላይ የሚፈጸሙ ከባድ ወንጀሎች ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ከፍተኛ ስጋቶች አሉ” በማለት የባለሙያዎቹ ሪፖርት አስጠንቅቋል።

ከባድ ወንጀሎች የሚባሉት በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸሙ አስከፊ ወንጀሎች ሲሆኑ፣ እነዚህም የዘር ማጥፋት፣ የጦር ወንጀሎች እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች መሆናቸውን ጠቅሷል።

መርማሪ ኮሚሽኑ እንዳለው ለእነዚህ ወንጀሎች ሊያጋልጡ የሚችሉ ሁሉም ሁኔታዎች በኢትዮጵያ ውስጥ እየተስተዋሉ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ከእነዚህም ውስጥ ቀጣይነት ያላቸው ከባድ የመብት ጥሰቶች፣ መጠነ ሰፊ ጥቃቶች፣ አለመረጋጋት እና ተጠያቂነት አለመኖር ተጠቃሽ የሆኑት ስጋቶች ናቸው ብሏል።

የባለሙያዎቹ ኮሚሽን ሊቀመንበር የሆኑት ሞሐመድ ቻንዴ ኦትማን “በኢትዮጵያ ባለው ሁኔታ እና ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ከባድ ወንጀሎች በጽኑ ያሳስቡናል” ብለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ባለሙያዎች ማክሰኞ ዕለት ባወጡት ሪፖርት ላይ እንዳመለከቱት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ “ከባድ የሚባሉ ወንጀሎችን ሊያስከትሉ የሚችሉ አስጊ ሁኔታዎች” በከፍተኛ ሁኔታ በአገሪቱ ውስጥ የሚታዩ መሆናቸውን አመልክቷል።

ለሁለት ዓመታት በተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ምክንያት የተቋቋመው ይህ የባለሙያዎች ቡድን፣ ባለፈው ነሐሴ ወር ባወጣው ሪፖርት የትግራይ ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ የጦር ወንጀሎች መፈጸማቸውን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

አሁንም በአገሪቱ እየተካሄዱ ያሉ ከባድ የመብት ጥሰቶች፣ መጠነ ሰፊ ጥቃቶች እና ለተፈጸሙ ወንጀሎች ተጠያቂነት ያለመኖር “ተጨማሪ ወንጀሎች እንዲፈጸሙ የሚያደርግ ከፍተኛ አደጋን የደቀነ ነው” ብሏል ኮሚሽኑ ባወጣው ግምገማ።

ሪፖርቱ እንዳመለከተው ምንም እንኳን በትግራይ የተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላም ስምምነት የቆመ ቢሆንም፣ “ከባድ የመብት ጥሰቶች” በትግራይ ክልል ውስጥ እየተፈጸሙ መሆናቸውን ጠቅሷል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች የባለሙያዎች ቡድን ጨምሮም በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ውስጥ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና ዓለም አቀፍ ወንጀሎች መፈጸማቸውን መመዝገቡን ገልጿል።

እንዲሁም በአማራ ክልል ከሕግ ውጪ የሚፈጸሙ ግድያዎችን እና የጅምላ አስሮችን በሚመለከት በቅርቡ የወጡ ሪፖርቶች እንዳሰሳቡትም አመልክቷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ሪፖርቱ ላይ እስካሁን ያለው ነገር የሌለ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት መርማሪ ኮሚሽኑ ያቀረበውን ሪፖርት ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል።

በትግራይ ጦርነት ወቅት ለተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች መንግሥት በሽግግር ፍትሕ ሂደት አማካይነት መፍትሄ እንደሚሰጥ በመጥቀስ፣ በኮሚሽኑ አስፈላጊነት ላይ ተቃውሞውን ሲያሰማ መቆየቱ ይታወቃል።

በተጨማሪም ይህ የተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መርማሪ የባለሙያዎች ቡድን የሥራ ጊዜው ሊጠናቀቅ የተቃረበ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የቡድኑ አስፈላጊነት እንዲያበቃ ግፊት ስታደርግ ቆይታለች።

ነገር ግን የተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ተከራካሪ ቡድኖች የኮሚሽኑ የሥራ ጊዜ እንዲራዘም በተደጋጋሚ ጥሪ እያረቡ ይገኛሉ።

Source: BBC Amharic

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *